ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በመካከላችን መኖርን ለሚወድ አምላክ ልባችንን መክፈት ይኖርብናል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 24/2014 ዓ.ም ያደርጉት አስተንትኖ ከዮሐንስ ወንጌል 1፡1-18 ላይ ተወስዶ በተነበበውና “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ።ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በመካከላችን መኖርን ለሚወድ አምላክ ልባችንን መክፈት ይኖርብናል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት ይዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው ስርዓተ አምልኮ ውብ የሆነ ሀረግ ይሰጠናል፣ ሁልጊዜም በመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ውስጥ እንደምንጸልየው በራሱ የገናን ትርጉም ይገልጥልናል። “ቃልም ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” (ዮሐ 1፡14) ይላል። ቃልም ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ። እነዚህ ቃላት ስለእነሱ ካሰብን እርስ በእርሳቸው የሚጣረዙ ቃላትን የያዙ ይመስላሉ። ሁለት ተቃርኖዎችን ያመጣሉ፡- ቃልና ሥጋ። “ቃል” የሚያመለክተው ኢየሱስ ዘላለማዊ የአብ ቃል፣ ወሰን የሌለው፣ ከጥንት ጀምሮ ያለ፣ ከፍጥረታት ሁሉ በፊት ያለ፣ በሌላ በኩል “ሥጋ” የኛን የተፈጥሮ እውነታ፣ ደካማ፣ ውስን፣ ሟች የሚሉትን በትክክል ያመለክታል። ከኢየሱስ በፊት ሁለት የተለያዩ ዓለማት ነበሩ፡ ሰማይ ምድርን ትቃወማለች፣ ወሰን የሌለው ውሱን የሆነውን ተቃራኒውን፣ መንፈስ ቁስን ይቃወማል። በዮሐንስ ወንጌል የመጀመሪያው ክፍል ላይ ሌላ ተቃውሞ አለ፣ ሌላ ሁለትዮሽ ያለ ሲሆን እነዚህም ቃልና ሥጋ የሚሉት ናቸው። ሌላኛው ሁለትዮሽ ብርሃን እና ጨለማ ናቸው (ዮሐንስ 1፡5)። ኢየሱስ ወደ ዓለም ጨለማ የገባ የእግዚአብሔር ብርሃን ነው። ብርሃን እና ጨለማ። እግዚአብሔር ብርሃን ነው፣ በእርሱ ውስጥ ጨለማ የለም፣ በእኛ ውስጥ በሌላ በኩል ብዙ ጨለማ አለ። አሁን ከኢየሱስ ጋር፣ ብርሃንና ጨለማ ተገናኙ፡ ቅድስና እና ኃጢአት፣ ጸጋ እና ኃጢአት። ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ መገለጡ፣ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል፣ በጸጋና በኃጢአት መካከል የሚደረግ ግንኙነት ያመለክታል።

በእነዚህ ዋልታዎች ቅዱስ ወንጌል ምን ሊያበስር አስቧል? አንድ የሚያምር ነገር ሊነግረን ያሰበ ሲሆን ይህም የእግዚአብሔር አሰራር የሚገልጽ ነው። ከድክመታችን ጋር ስንጋፈጥ፣ ጌታ ወደ ኋላ አይመለስም። በተባረከ ዘላለማዊነቱ እና በማያልቀው ብርሃኑ ውስጥ ሆኖ ብቻ አይመለከተንም፣ ይልቁንም ወደ እኛ ይቀርባል፣  እራሱን ወደ ስጋ እያስገባ ወደ ጨለማው ይወርዳል፣ ለእርሱ ባዕድ በሆኑ አገሮች ውስጥ ይኖራል። እግዚአብሔርስ ለምን ይህን ያደርጋል? ለምን ወደ እኛ ይወርዳል? ይህን የሚያደርገው ከእርሱ ርቀን፣ ከዘላለማዊ ሕይወት ርቀን፣ ከብርሃን ርቀን እንድንሳሳት ሰላማይፈቅ ነው። በመካከላችን መኖሩ የሚያሳየው የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ መሆኑን ነው። እራሳችን ብቁ እንዳልሆንን የምንቆጥር ከሆነ ያ አያግደውም፤ ይመጣል። እርሱን የምንቃወም ብንሆንም እንኳን እኛን ከመፈለግ እንዲታክት አያደርገውም። እሱን ለመቀበል ዝግጁ ካልሆንን እንኳን እርሱ ወደ እኛ መምጣቱን አያቋርጥም። እናም በፊቱ ላይ በሩን ከዘጋን እንኳን እርሱ የእኛን ጥሪ ቆሞ ይጠባበቃል። እርሱ በእውነት መልካም እረኛ ነው። በጣም ቆንጆ የሆነ የመልካም እረኛ ምስል ነው።  በሕይወታችን የምንካፈለው ሥጋ የሚሆን ቃል። ኢየሱስ ባለንበት ሊፈልገን የሚመጣ መልካም እረኛ ነው፡ በችግራችን፣ በመከራችን… ሁልጊዜ ወደ እኛ ይመጣል።

ውድ ወንድሞችና እህቶቼ ብዙውን ጊዜ ከአምላክ የምንርቀው በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ለእሱ ብቁ ሆነን ስለማይሰማን ነው። እናም ይህ እውነት ነው። የገና በዓል ግን ነገሮችን በእሱ እይታ እንድንመለከት ይጋብዘናል። እግዚአብሔር በሥጋ መገለጥ ይፈልጋል። ልብህ በክፋት የተበከለ መስሎ ከታየ፣ የተዘበራረቀ ከመሰለ፣ እባክህን ራስህን አትዝጋ፣ አትፍራ፤ እርሱ ይመጣል። በቤተልሔም ያለውን በረት አስብ። ኢየሱስ የተወለደው በዚያ በድህነት ውስጥ ነው፣ በእርግጠኝነት ልብህን ለመጎብኘት፣ በአስጨናቂ ህይወት ውስጥ ለመኖር እንደማይፈራ ሊነግረን ነው ይህንን ያደርገው። በመካከላችን አደረ የሚለው ቃል የሚያመለክተው ይህንን ነው። በመካከላችን አደረ የሚለው ሐረግ ዛሬ በወንጌል ውስጥ ይህንን እውነታ ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለው ሐረግ ነው፤ በአጠቃላይ መጋራትን፣ ታላቅ መቀራረብን ይገልጻል። እግዚአብሔር የሚፈልገውም ይህ ነው፤ ከእኛ ጋር ሊኖር፣ በእኛ ውስጥ ሊኖር እንጂ መራቅን አይፈልግም።

እናም ራሴን እጠይቃለሁ ፣ እናንተም ሁላችሁም ራሳችሁን ጠይቁ፣ ለእሱ ቦታ ልንሰጠው እንፈልጋለን ወይ? በቃላት አዎን የሚል መልስ የምንሰጥ ሲሆን ማንም ሰው "እኔ አላደርግም!" ብሎ ሊመልስ አይፈልግም።  አዎ በተግባር ግን? ምናልባት ለራሳችን የምናስቀምጣቸው፣ ብቸኛ የሆኑ ወይም ወንጌሉ እንዳይገባ የምንሰጋባቸው ውስጣዊ ክፍተቶች ሊኖሩ የሚችሉ ሲሆን እግዚአብሔር እንዲሳተፍ የማንፈልግበት የሕይወት ገጽታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ዛሬ ልዩ እንድትሆኑ እጋብዛችኋለሁ። እግዚአብሔር የማይወደውን የማምንባቸው ውስጣዊ ነገሮች ምንድናቸው? እግዚአብሔር እንዲመጣ የማልፈልገው ለእኔ ብቻ ነው ብዬ የማምንበት ቦታ ምንድን ነው? እያንዳንዳችን ልዩ እንሁን እና ይህን መልስ እንስጥ። "አዎ ኢየሱስ እንዲመጣ እፈልጋለሁ፣ ነገር ግን ይህ እሱ መንካት የለበትም፤ እናም ይሄ አይሆንም .. . . ወዘተ እያልን ምክንያት እንደረድራለን። እያንዳንዱ ሰው የራሱ ኃጢአት አለው - በስም ልንጠራው እንችላለን። ኃጢአታችንንም አይፈራም፤ ሊፈውሰን መጣ። ቢያንስ እርሱን እንመልከተው ኃጢአታችንንም እንመልከት። ደፋር እንሁን፣ እንዲህም እንበል፡- “ነገር ግን ጌታ ሆይ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነኝ መለወጥ አልፈልግም። አንተ ግን እባክህ በጣም ርቀህ እትድሂድብኝ" የሚለው ጥሩ ጸሎት ነው። ዛሬ ቅን እንሁን።

በእነዚህ የገና ቀናት ጌታን እዚያ በትክክል መቀበላችን ይጠቅመናል። እንዴት? ለምሳሌ ያህል፣ የልደቱን ትዕይንት በሚገልጸው ምስል ፊት ለፊት መቆም፣ በእውነተኛው፣ ተራ ሕይወታችን ውስጥ ለመኖር የመጣውን ኢየሱስን ስለሚያሳይ፣ ሁሉም ነገር ጥሩ በማይሆንበት፣ ብዙ ችግሮች ባሉበት ሁኔታዎች ውስጥ በመግባት ለአንዳንዶቹ ችግሮቻችን ተጠያቂዎች መሆናችንን ማመን ይኖርብናል። ሌሎች የሌሎች ሰዎች ጥፋት ናቸው። ኢየሱስም መጣ፣ ጠንክረው የሚሠሩ እረኞች፣ እረኞችን እዚያ እናያቸዋለን፣ ሄሮድስ ንፁሃንን የሚገድል፣ ታላቅ ድህነትን የሚገልጸውን ምስል እነዚህን እና እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ችግሮች መሃል እና በችግሮቻችን መካከል እንኳን - እግዚአብሔር አለ፤ ከእኛ ጋር ሊኖር የሚፈልግ እግዚአብሔር አለ እናም ሁኔታዎቻችንን፣ እየኖርን ያለነውን ለእሱ እንድናቀርብ ይጠብቀናል። እንግዲያው ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ስለ እውነተኛ ሁኔታችን ከኢየሱስ ጋር እንነጋገር። በህይወታችን ውስጥ በተለይም በጨለማ ቦታዎች ውስጥ በይፋ እንጋብዘው፡- “እነሆ ጌታ ሆይ፣ እዚያ ብርሃን የለም፣ ኤሌክትሪኩ እዚያ አይደርስም፣ ነገር ግን እባክህ አንተ መጥተህ ሕይወቴን አብራ፣ ምክንያቱም የአንተ ብርሃን ሕይወት ይቀይራልና፣ በማለት ስለሁኔታችን በግልጽ እና በግልጽ መናገር ይኖርብናል። ጨለማ ቦታዎች፤ በእኛ ውስጥ የሚገኝ በረት፣ እያንዳንዳችን ውስጥ አለ። እግዚአብሔርም በመካከላችን ማደር ስለሚወድ ስለ ዘመናችን ስለ ማኅበራዊ ችግሮች እና ስለ ቤተ ክህነት ችግሮች፣ ሌላው ቀርቶ በጣም የከፋውን፣ ያለ ፍርሃት እንንገረው።

ቃል ሥጋ የሆነባት ወላዲተ አምላክ ይህንን በሕይወታችን መተግበር እንችል ዘንድ እና ከጌታ ጋር የበለጠ በመቀራረብ መኖር እንችል ዘንድ እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን።

02 January 2022, 11:01

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >