ፈልግ

ቃለ መጠይቅ ቃለ መጠይቅ 

በመረጃ ልውውጥ ሂደት መደማመጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ግንቦት 21/2014 ዓ. ም. ለ56ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላለፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማኅበራዊ መገናኛዎች ከወገንተኝነት እና ከግል ጥቅም ወጥተው ለሰው ልጅ አገልግሎት መዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው መልካም ማኅበራዊ ግንኙነትን ለማሳደግ በሁሉም ደረጃዎች የእርስ በእርስ መደማመጥ ሊኖር እንደሚገባ በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከፍተኛ የጤና ቀውስ እያስከተለ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ ሰዎች ለመደመጥ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሁለት ጆሮ እና አንድ አፍ ተሰጥቶናል ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ይህም ከመናገር ይልቅ የማድመጥ አስፈላጊነትን ይገልጻል” በማለት ያቀረቡት የዘንድሮ መልዕክታቸው፣ ሰኞ ጥር 16/2014 ዓ. ም. በተከበረው የማኅበራዊ መገናኛ ባልደረባ፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዴ ሳለስ በዓል ዕለት ይፋ መሆኑ ታውቋል። ማድመጥ በማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ለተሰማሩት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሚገባ ቅዱስነታቸው አሳስበው፣ በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ደንብ በሚጠይቀው ማኅበራዊ ርቀት እና ከሰው ተለይቶ መቆየት የእርስ በእርስ መደማመጥ አስፈላጊነት ማደጉን አስረድተዋል። መደማመጥ ጸጥታንም እንደሚፈልግ፣ ጸጥታ ከሌለ ሌላውን ማድመጥ እንደሚቸግር በቫቲካን ከሚገኝ ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት እ. አ. አ ሚያዝያ 21/2020 ዓ. ም. ባተላለፉት መልዕክት መግለጻቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላልፉት መልዕክት በሁሉም አካባቢ ጸጥታ መስፈኑን ገልጸው፣ “ይህ አዲስ የዝምታ ልማድ የማድመጥ አቅማችንን ሊያሳድግልን ይገባል” ማለታቸው ይታወሳል።

በዘዳ. 6:4 ‘እስራኤል ሆይ ስማ’ የሚል ተጽፎ እናገኛለን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ከኦሪት የመጀመሪያ ትእዛዝ መክፈቻ ቃላት ጀምሮ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በላከው መልዕክቱ በምዕ. 10:17 ላይም ‘ማመን ከመስማት ነው’ የሚለውን ጥቅስ አስታውሰው፣ እግዚአብሔርን በማድመጥ ምላሽ የምንሰጥበትን ተነሳሽነት የሚናገኘው ከእግዚአብሔር እንደሆንም አስረድተዋል። በመሆኑም ማድመጥ የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማሳደግ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው የዲጂታል ሚዲያ ጣልቃ ገብነት እና ሰው ሠራሽ ልህቀት ውስብስብ የሆኑ መልዕክቶችን ለመተርጎም እና ማኅበራዊ ዕድገቶችን ለማምጣት የረዳ መሆኑን ገልጸዋል።

“የመገናኛ ብዙኃን ወይም በመረጃው ዓለም የተሰማሩት ባለሞያዎች የመደማመጥን “ተግዳሮት” ለማቃለል ምን ማድረግ ይችላሉ?” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ መፍትሄው በሰዎች ዘንድ እንደሚገኝ ገልጸው፣ አምና በተከበረው ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን መልዕክታቸው እውነተኛ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ከተፈለገ ጋዜጠኞች ወደ ሥፍራው እንዲሄዱ አበረታተው፣ በዘንድሮ መልዕክታቸውም፣ ጠንካራ፣ ሚዛናዊ እና የተሟላ መረጃ ለማቅረብ ለረጅም ጊዜ ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

እውነተኛ ሳይሆን ሐሰተኛ የማዳመጥ ችሎታ እንዳለ የገለጹት ቅዱስነታቸው፤ በዚህ ዓይነት መንገድ ሰዎችን ማዳመጥ ለግል ጥቅም እንጂ ሌሎችን ለመጥቀም ወይም ለማገልገል እንደሆነ ገልጸው፣ ማኅበራዊ ግንኙነት መልካም እና ፍጹም ሰብዓዊ የሚሆነው ፊት ለፊት ያለውን ሰው በፍትሃዊነት፣ በራስ መተማመን፣ በታማኝነት እና ግልጽነት ባለው መንገድ ማዳመጥ ሲቻል እንደሆነ አስረድተው፣ አንድን ክስተት ለመዘገብ እና በዘገባ አሰባሰብ ላይ ያለውን ልምድ ለመግለጽ በሚገባ ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ፣ ከግል ስሜት መውጣት እና ግምታዊነትን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የአውሮፓ አገሮች ሚዲያ ስርጭት ኅብረት ዋና ሃላፊ ክቡር አቶ ኖኤል ኩራን ከቫቲካን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሕዝብን ለማገልገል የቆሙለት ዓላማ በሕግ እውቅናን የሚያገኘው የግለሰቦችን እና ማኅበረሰቦችን ፍላጎት በሚገባ ሲያዳምጥ እንደሆነ ተናግረዋል። የኅብረቱ ኃላፊ አቶ ኖኤል ኩራን አክለውም፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለማችን በተስፋፋበት በዚህ ወቅት “የሕዝብ ሚዲያ ከፍተኛ የመረጃ ምንጭ ሆኗል” በማለት ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ ሁላችንም በማኅበራዊ መገናኛው ዘርፍ የምንሳተፍ በመሆናችን፣ ማኅበራዊ ግንኙነታችን ለሰው ልጅ ዕድገት ቅድሚያን የሚሰጥ መሆን አለበት በማለት አሳስበዋል። ሁልጊዜም ማኅበራዊ ግንኙነት የሚጀመረው እርስ በእርስ ስንቀራረብ እና ከልብ ስንደማድመጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

29 January 2022, 15:41