ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን ከሮም ኩሪያ አባላት ጋር በተገኛኙበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን ከሮም ኩሪያ አባላት ጋር በተገኛኙበት ወቅት 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትህትናን ያስተምረናል አሉ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ክርስቲያኖች ዘንድ በቅርቡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሚከበር ሲሆን ከዚያም በመቀጠል ከሳምንት በኋላ ደግሞ አዲስ አመት እንደ ሚከበር ይታወቃል። ይህንን መንፈሳዊ የሆነውን የገና በዓል እና እንዲሁም የጎርጎሮሳዊያኑን አዲስ አመት አስመልክቶ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅድስት መንበር በቫቲካን ለሚገኙ የእርሳቸው የሥራ ቧለሟሎች እና በቅድስት መንበር ሥር ለሚተዳደሩ የተለያዩ መስሪያ ቤት ሰራተኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት እንደ ሚያስተላልፉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 14/2014 ዓ.ም “እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ” መልእክታቸው እንደ ገለጹት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ትህትናን ያስተምረናል” ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

በየአመቱ እንደሚደረገው የገና በዓል ከመከበሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የመገናኘት እድል ዛሬ አግኝተናል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሰላምታ በመለዋወጥ ወንድማማችነታችንን “ጮክ” ብለን የምንገልጽበት መንገድ ነው። ነገር ግን ቃል ሥጋን ለብሶ በሰው የሰራው የቃሉ ብርሃን ማንነታችንን እና ተልእኳችን ምን እንደሆነ የበለጠ እንዲያሳየን ለእያንዳንዳችን የማሰላሰያ እና የምዘና ጊዜ ነው።

የገና ምሥጢር በትሕትና መንገድ ወደ ዓለም የገባ የእግዚአብሔር ምሥጢር ነው። ዘመናችን ትሕትናን የረሳ ወይም ወደ ሥነ ምግባራዊ መልክ ያወረደ፣ የትህትናን ታላቅ ኃይሉን ባዶ ያደረገ ይመስላል።

ሆኖም የገናን ምስጢራት በሙሉ በቃላት መግለጽ ካለብን፣ ከሁሉ የሚበልጠው ትህትና እንደሆነ ሳስብ ይገርመኛል። ቅዱሳን ወንጌላዊያን አንዲት ሴት ልትወልድ ስትል ማጣቷን፣ድህነት የተጠናወታት እና ያልተገባች እንደ ሆንች የሚያመልክት ትዕይንት ያሳያሉ። ሆኖም የነገሥታት ንጉሥ ወደ ዓለም የገባው ትኩረትን በመሳብ አይደለም፣ ነገር ግን ፍጹም የሆነ አዲስ ነገር፣ ታሪክን ለመለወጥ በቋፍ ላይ ያለውን ነገር በሚሰማቸው ሰዎች ልብ ውስጥ እንቆቅልሽን የሚመስሉ ነገሮች እንዲፈጠር በማድረግ እና ቀልባቸውን በመሳብ ነው። ትህትና የመግቢያ በሩ ነበር፣ እናም በዚህ በር እንድንገባ ይጋብዘናል።

ትህትና ምን እንደሆነ ለመረዳት ቀላል አይደለም። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ መንፈስ ራሱ በእኛ ውስጥ የሚያመጣው የለውጥ ውጤት ነው። ለምሳሌ የሶርያዊው ንዕማን ሁኔታ እንደዚህ ነበር (2 ነገ. 5)። በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን ይህ ሰው ታላቅ ስም ነበረው። በብዙ አጋጣሚዎች ጀግንነቱንና ጥንካሬውን በተግባር ያሳየ ጀግና የሶሪያ ጦር ጀኔራል ነበር። ንዕማን ከዝና፣ ከሥልጣን፣ ከበሬታ፣ በራስ ከመተማመን፣ ከታላቅ ክብሩ ጋር በአንድነት ከአሳዛኝ ሁኔታ ጋር ለመኖር ተገደደ፡ የሥጋ ደዌ ወይም የለምጽ በሽተኛ ነበር። ለእሱ ክብር ያበቃው የጦር ትጥቅ፣ በእውነቱ ደካማ፣ የቆሰለ እና የታመመ የሰው ልጅን ሸፍኗል። ብዙ ጊዜ ይህንን ተቃርኖ በህይወታችን ውስጥ እናገኘዋለን፣ አንዳንድ ጊዜ ታላቅ ስጦታዎች ታላላቅ ድክመቶችን የሚሸፍኑ ጋሻዎች ናቸው።

ንዕማን አንድ መሠረታዊ እውነት ተረዳ፣ ሕይወታችንን ከትጥቅ፣ ከምንጫወተው ሚና ወይም ከማኅበራዊ እውቅና ጋር ሕይወታችንን ደብቀን ማሳለፍ አንችልም። በእያንዳንዱ ሰው ህይወት ውስጥ የዚህን አለም ክብር ብልጭልጭ እንደ ሆነና ለትክክለኛ ህይወት ሙላት ወደጎን ለመተው የሚፈልግበት ጊዜ ይመጣል፣ ምንም ተጨማሪ የጦር ትጥቅ ወይም ጭንብል አያስፈልግም። ይህ ፍላጎት ጀግናው ጄኔራል ንዕማን የሚረዳውን ሰው ለመፈለግ ወደ ጉዞ እንዲሄድ አነሳሳው፤ ይህንንም ያደረገው በጦርነት እስረኛ የሆነች አይሁዳዊት ባሪያ ሴት ባቀረበችው ሐሳብ መሰረት ሲሆን ፈውስን የሚያመጣ አምላክ እንዳለ ነገረችው፣ እርሱ ግን ተስፋ በሌላቸው ሁኔታዎች ውስጥ ነበር።

ንዕማን ብርና ወርቅ ተሸክሞ ጉዞውን ቀጠለ እና ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መጣ፣ እሱም ለፈውሱ ብቸኛ ቅድመ ሁኔታ የሆነው፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሰባት ጊዜ በመጠመቅ እና በመታጠብ ሊፈወስ እንደ ሚችል ቀላል ምልክት አድርጎ አስቀመጠው። ከታዋቂ ሰው፣ ከክብር፣ ከወርቅና ከብር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም! የሚያድነው ጸጋ ነጻ ነው፣ በዚህ ዓለም ቁሳቁሶች የተነሳ ዋጋ ሊቀንስ የማይችል በነጻ የሚሰጥ ፀጋ ነው፣ ዋጋውም እጅግ ታላቅ ነው።

ንዕማን ግን ይህንን ሐሳብ ተቃወመ፣ የነቢዩ ጥያቄ ለእሱ ተራ፣ በጣም ቀላል፣ በቀላሉ ሊደረስበት የሚችል ይመስላል። የቀላልነት ኃይሉ በምናቡ ውስጥ ምንም ቦታ ያላገኘ ይመስላል። ሆኖም አገልጋዮቹ የተናገሩት ሐሳብ ሐሳቡን እንዲለውጥ አድርጎታል:- “የንዕማን አገልጋዮች ግን ወደ እርሱ ቀርበው፣ “አባት ሆይ፤ ነቢዩ ከዚህ ከበድ ያለ ነገር እንድታደርግ ቢነግርህ ኖሮ አታደርገውም ነበርን? ታዲያ፣ ‘ታጠብና ንጻ’ ቢልህ ምኑ አስቸገረህ?” አሉት። ስለዚህ ንዕማን ወረደ፤ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገረውም በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ትንሽ ልጅ ሥጋ ሆነ፤ ነጻም (2ኛ ነገ 5;13-14)። በጣም ጥሩ የሆነ ትምህርት ነው! በጌታ ቃል መሰረት የራሱን ሰብዓዊነት በትሕትና በማጋለጡ የተነሳ ንዕማን ፈውስ አገኘ።

የንዕማን ታሪክ የሚያስገነዝበን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሚከብርበት የገና በዓል እያንዳንዳችን ጋሻችንን ለማውለቅ ድፍረት አግኝተን የተግባራችንን ወጥመድ ጥለን ህብረተሰባዊ እውቅናን እና የዚህ አለምን ብልጭልጭ ነገር ጥለን የንዕማንን ትህትና የምንቀበልበት ወቅት ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው ከኃይለኛ፣ የበለጠ አሳማኝ እና የበለጠ ስልጣን ካለው ምሳሌ በመነሳት ነው፡-  በትህትና ወደታች መወረድ ያላፍረው የእግዚአብሔር ልጅ ሰው በመሆን፣ ልጅ በመሆን፣ አቅመ ደካማ በመሆን፣ በመጠቅለያ ተጠቅልሎ ልብስ ሳይኖረው በግርግም መወለዱ ታላቅ የትህትና ምልክት ነው (ሉቃ. 2፡16)። ልብሳችንን፣ መብታችንን፣ ማዕረጎቻችንን እና ክብራችንን ካነሳን ሁላችንም ፈውስ የምንፈልግ ለምጻሞች እንሆናለን ማለት ነው። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሚከበርበት የገና በዓል የዚህ ግንዛቤ ሕያው ማስታወሻ ነው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሰብአዊነታችንን ከረሳን ከመሳሪያችን ብልጭልጭ ከሆነ ኃይል ወጥተናል ማለት ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ዓለምን ሁሉ ብታተርፍ ሕይወትህንም ብታጣ ምን ይጠቅመሃል?” የሚለውን የማይመችና የማያረጋጋ እውነት አስታውሶናል (ማር. 8፡36)።

ይህ አደገኛው ፈተና ነው - በሌሎች አጋጣሚዎች እንዳልኩት - ከሌሎቹ ፈተናዎች በተለየ መልኩ ጭምብል ለመግለጥ የሚከብድ የመንፈሳዊ ዓለማዊነት ፈተና ነው፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ እኛን በሚያረጋግጡልን ነገሮች ሁሉ የተደበቀ ነው፣ የእኛ ሚና፣ ሥርዓተ ቅዳሴ፣ አስተምህሮ፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን መሰጠት በመሳሰሉ ነገሮች ውስጥ የተረጋገጠ ነው። በላቲን ቋንቋ “ኢቫንጄሊ ጋውዲየም” (የወንጌል ደስታ) በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት ላይ እንደጻፍኩት፣ እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ዓለማዊነት “በተጨማሪም በጦርነቱ በሚቀጥል ሕብረት ውስጥ በግል ከሚገኝ የተሸናፊ ሠራዊት ጄኔራል ለመሆን የሚረኩ ሰዎችን ከንቱ ውዳሴ ይመገባል። ግዙፍ ሐዋርያዊ ፕሮጄክቶችን፣ በጥንቃቄ የታቀዱ፣ ልክ እንደተሸነፉ ጄኔራሎች እነዚህን ነገር ምን ያህል ጊዜ እናልማቸዋለን! ይህ ግን የመስዋዕትነት፣ የተስፋና የዕለት ተዕለት ተጋድሎ፣ ለአገልግሎት እና ለሥራ ታማኝነት ያሳለፍን የሕይወት ታሪክ ስለሆነች፣ ምንም ያህል አድካሚ የሆነች፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን ታሪካችን ክብር የሆነችውን ታሪካችንን መካድ ነው፣ ሥራ ሁሉ ሥራ ነውና።  ይልቁንስ ስለ ‘ምን መደረግ እንዳለበት’ ለመነጋገር ጊዜን እናጠፋለን - በስፓኒሽ ቋንቋ ይህንን የሃቢሪያኬስሞ (ከዚህ ቀደም እንዲህ ነበረ) የሚለው ኃጢአት ብለን እንጠራታለን - እንደ መንፈሳዊ ሊቃውንት እና የሐዋርያዊ አገልግሎት ሊቃውንት ከአርያም መመሪያ እንደሚሰጡ አድርገን እንቆጥራቸዋለን። ማለቂያ በሌለው ቅዠቶች ውስጥ እንገባለን እና ከህዝባችን እውነተኛ ህይወት እና ችግሮች ጋር ግንኙነት እናጣለን"።

ትህትና በጌታ የተወደደውን እና የተባረከውን ሰብአዊነታችንን እንዴት "እንደሚኖር" የማወቅ ችሎታ ነው፣ እናም ያለ ተስፋ መቁረጥ፣ ነገር ግን በእውነታ፣ በደስታ እና በተስፋ የመኖር ዝይቤ ነው። ትህትና ማለት በድክመታችን ማፈር እንደሌለብን ማወቅ ማለት ነው። ኢየሱስ ድህነታችንን በተመሳሳይ ፍቅር እና ርኅራኄ እንድንመለከት ያስተምረናል፣ ይህም አንድ ትንሽ ልጅን በምንመለከትበት መልኩ ራሳችንን መመልከት የሚኖርብን ሲሆን ተጋላጭ እና ሁሉም ነገር የጎደሉብን ሰዎች አድርገን ራሳችንን መመልከት ያስፈልጋል። ትሕትና ስለሌለን፣ ለሕይወታችን ዋስትና የሚሰጡ እና ይህንን የሚያረጋግጡ ቁሳዊ  ነገሮች እንፈልጋለን ምናልባትም እናገኛቸዋለን፣ ነገር ግን የሚያድነን፣ የሚፈውሰንን አናገኝም። እነዚያን የማረጋገጫ ዓይነቶች መፈለግ የመንፈሳዊ ዓለማዊነት በጣም ጠማማ ፍሬ ነው፣ ምክንያቱም እምነትን፣ ተስፋን እና ፍቅርን ማጣት ያሳያል። የነገሮችን እውነተኝነት ወደ አለመቻል ያመራል። ንዕማን ጋሻውን ለማስጌጥ ሜዳሊያዎችን ማከማቸቱን ብቻ ቢቀጥል ኖሮ በመጨረሻ በሥጋ ደዌው ተበልቶ ይሞት ነበር፤ ሕያው ሆኖ የሚኖር የሚመስል፣ ነገር ግን በበሽታው የተያዘ እና የተገለለ ሰው ሆኖ ይኖር ነበር። ይልቁንም ንዕማን ሊያድነው የሚችለውን ነገር ለመፈለግ ድፍረቱ ነበረው እንጂ በአጭር ጊዜ ውስጥ እርካታን የሚያመጣውን ነገር አልመረጠም ነበር።

የትህትና ተቃራኒ ኩራት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። የነቢዩ ሚልክያስ ጥቅስ በትሕትና መንገድና በትዕቢት ጎዳና መካከል ያለውን ልዩነት እንድንገነዘብ ይረዳናል:- “ትምክህተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ገለባ ይሆናሉ። የሚመጣው ቀን ያቃጥላቸዋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም” (ሚክያስ 4፡1) በማለት ይናገራል።

ነብዩ “ገለባ” የሚለውን ስሜት ቀስቃሽ ምስል ይጠቀማል፣ እሱም ኩራትን በግልፅ ቃላት ይገልፃል፣ ምክንያቱም እሳቱ አንድ ጊዜ ገለባውን ከነካው ወዲያው አመድ ይሆናል። ይቃጠላል እና ይጠፋል። ሚልክያስም በትዕቢት የሚኖሩ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ማለትም ሥርና ቅርንጫፎችን እንደሚያጡ ይነግረናል። ስሮች ካለፈው ጋር ያለንን ወሳኝ ግንኙነት ይወክላሉ፣ከዚያም በአሁኑ ጊዜ እንድንኖር የሚያስችለንን እርጥበት በሥሮቻችን መክንያት እንቀዳለን። ቅርንጫፎቹ ከሞት የራቀ፣ ወደ ነገ የሚያድግ እና ወደፊት የሚሆነውን የአሁን ጊዜያችንን ይወክላሉ። ሥር ወይም ቅርንጫፎች በሌለው ስጦታ ውስጥ መቆየት ማለት የመጨረሻ ሰዓታችንን መኖር ማለት ነው። ያ በትንሿ ዓለም ውስጥ ተዘግቶ ያለፈውም ሆነ ወደፊት፣ ሥር ወይም ቅርንጫፎ የሌለው፣ እና በልባቸው ላይ “የዲያብሎስ መጠቀሚያዎች ሁሉ እጅግ የከበረ” ብለው በሚመዝኑት መራራ ጣእም የሚኖሩ የኩሩዎች መንገድ ነው። ትሑታን ግን በሁለት ግሦች እየተመሩ ሕይወታቸውን ያለማቋረጥ ይኖራሉ፡ በማስታወስ እና ሕይወትን ለመስጠት። በዚህ መንገድ ሥሮቻቸውና ቅርንጫፎቻቸው ፍሬ በማፍራት ደስተኛና ፍሬያማ ሕይወት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል።

በጣሊያንኛ ማስታወስ [ሪኮርዳሬ] የሚለው ግስ ሥርወ-ቃል “ወደ ልብ መመለስን” ያመለክታል። የትውፊት፣ የሥሮቻችን ህያው ትዝታ ያለፈውን አምልኮ ሳይሆን ከእኛ በፊት የነበሩትን፣ ታሪካችንን ምልክት ያደረገበት እና ዛሬ ያለንበት ደረጃ ያደረሰንን ሁሉ ዘወትር ወደ ልባችን የምናመጣበት ውስጣዊ እንቅስቃሴ ነው። ማስታወስ ማለት መድገም ማለት አይደለም፣ ነገር ግን እንደ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ልባችንን እንዲያቀጣጥልልን መፍቀድ፣ ማደስ፣ መቀደስ እና ከምስጋና ጋር መፍቀድ ማለት ነው (ሉቃ. 24፡32)።

ሆኖም ማሕደረ ትውስታችን ያለፈው ነገር እስረኞች እንድንሆን እንዲያደርገን የማንፈቅድ ከሆነ ሌላ ግስ ያስፈልገናል፤ ይህም ሕይወት “ማመንጨት” ማለት ነው። ትሑት ሰዎች ያለፈውን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱንም ጭምር የሚጨነቁ ናቸው፤ ወደ ፊት መመልከትን ስለሚያውቁ ቅርንጫፎቻቸውን ይዘረጋሉ፣ ያለፈውን ጊዜ በምስጋና እያሰቡ ይኖራሉ። ትህትና ሕይወትን ይሰጣል፣ ሌሎችን ይስባል እና ወደ ፊት ወደ ሚገኘው ወደማይታወቅ ወደፊት እንድንሄድ የገፋፋናል። ኩሩዎች ደግሞ በቀላሉ ነገሮችን ይደግማሉ፣ ግትር ናቸው እና እራሳቸውን በዚያ ድግግሞሽ ውስጥ ይዘጋሉ፣ ስለሚያውቁት ነገር እርግጠኛ ሆነው እና ማንኛውንም አዲስ ነገር መቆጣጠር ስላልቻሉ ይፈራሉ። የማስታወስ ችሎታቸው ስለጠፋ ድንጉጦች ይሆናሉ።

ትሑታን ሰው እንዲገዳደራቸው ይፈቅዳሉ። ከፊታቸው ላለው ነገር ዋስትና ስለሚሰማቸው፣ በሥሮቻቸውና በባለቤትነት ስሜታቸው ስለፀኑ ለአዲሱ ነገር ክፍት ናቸው። አሁን ያላቸው ዘመን በተስፋ የተሞላ የወደፊት ሕይወት እንዲኖራቸው የሚከፍት ባለፈው ጊዜ ላይ የተመሰረተ ነው። ከትዕቢተኞች በተቃራኒ ሕልውናቸው በብቃታቸው ወይም "በጥሩ ልማዶቻቸው" ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ ያውቃሉ። እንደዚያው ሊተማመኑ ይችላሉ።

ሁላችንም ለትህትና ተጠርተናል ምክንያቱም ሁላችንም የተጠራነው ለማሰብ እና ህይወትን ለመስጠት ነው። ከሥሮቻችን እና ከቅርንጫፎቻችን ጋር ትክክለኛውን ግንኙነት ለማግኘት ተጠርተናል። እነዚያ ሁለት ነገሮች ከሌሉ እኛ እንታመማለን፣ እንጠፋለን።

በትህትና መንገድ ወደ አለም የመጣው ኢየሱስ መንገድን ከፍቶልናል፣ እርሱ ከሩቅ ሆኖ ይጠቁመናል፣ እናም ግቡን ያሳየናል።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ያለ ትህትና እግዚአብሔርን ማግኘት እና መዳንን ማግኘት አንችልም፣ ነገር ግን ያለ ትህትና ባልንጀሮቻችንን፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንኳን ማግኘት አንችልም።

እ.አ.አ. ባለፈው ጥቅምት 17/2021 ዓ.ም ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚቆይ የሲኖዶስ ጉዞ ጀምረናል። በዚህ ውስጥም ትህትናን ብቻ እንድንገናኝ እና እንድንሰማ፣ እንድንነጋገር እና እንድንረዳዳ ያስችለናል። በእምነታችን እና በተሞክሮዎቻችን ውስጥ ተዘግተን ከቀጠልን፣ የራሳችን አስተሳሰብ እና ስሜት ጠንካራ ቅርፊት አጥረን፣ ለዚያ የመንፈስ ልምምድ ክፍት መሆን አስቸጋሪ ይሆንብናል፣ እሱም ሐዋርያው ​​እንደተናገረው ሁላችንም ነን ከሚል እምነት የተወለደ ነው። ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር የአንድ አምላክ የሁሉም አባት ልጆች ናችሁ ይለናል (ኤፌ 4፡6)።

ያ ቃል - "ሁሉም" - ለተፈጠረው አለመግባባት ምንም ቦታ አይሰጥም! እንደ ፈተና በየእለቱ በመካከላችን የሚስፋፋው የሃይማኖት ትምህርት ለአንዳንዶች ብቻ የሚናገር አምላክን እንድናስብ ያደርገናል ሌሎቹ ደግሞ መስማትና መታዘዝ ብቻ አለባቸው ብለን እንድናምን ያደርገናል። ሲኖዶስ ሁላችንም የአንድ ትልቅ ህዝብ አባላት፣ ቅዱሳን እና ታማኝ የእግዚአብሔር ሰዎች የመሰማት ልምድ ነው፣ እና ስለዚህ ደቀ መዛሙርት የሚሰሙ እና በትክክል በዚህ ማዳመጥም የእግዚአብሔርን ፈቃድ መረዳት የሚችሉ ሲሆን ይህም ሁል ጊዜ በማይገመቱ መንገዶች ይገለጣል። ነገር ግን ሲኖዶስ ከኛ የራቀ እና ረቂቅ ነገር ሆኖ ለቤተክርስቲያን የታሰበ ክስተት ነው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ሲኖዶሳዊነት ወደ እኛ የምንለወጥበት “ዘይ” ነው፣ በተለይም እኛ እዚህ ያለነው እና ሁለንተናዊቷ ቤተ ክርስቲያንን ለምናገለግል ለእኛ አስፈላጊ ነው።

የሮም ኩሪያ (የቅድስት መንበር የመማክርት ጉባሄ) የአለማቀፋዊቷን ቤተክርስቲያን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ ሎጂስቲክስ እና የቢሮክራሲ መሳሪያ ብቻ የምናከናውን ሳይሆን ለመመስከር የተጠራው የመጀመሪያው አካል ነው። በትክክል በዚህ ምክንያት፣ የዚያ ሲኖዶሳዊ ለውጥ ተግዳሮቶችን በመጀመሪያ ሰው ሲቀበል፣ በክብር እና በውጤታማነት ያድጋል። ልንቀበለው የሚገባን ድርጅት የንግድ ሳይሆን የወንጌል ባሕርይ ያለው ሊሆን ይገባል።

በዚህ ምክንያት፣ የእግዚአብሔር ቃል መላውን ዓለም የድህነትን ዋጋ የሚያስታውስ ከሆነ፣ እኛ የኩሪያ አባላት፣ እራሳችንን ወደ ጨዋነት ዘይቤ ለመለወጥ ቀዳሚ መሆን አለብን። ወንጌል ፍትህን ካወጀ፣ ያለ አድሎአዊነትና ያለ ልዩነት በግልፅነት ለመኖር የመጀመሪያው መሆን አለብን። ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሳዊውን መንገድ የምትከተል ከሆነ፣ ወደ ተለየ የሥራ ዘይቤ፣ ወደ ትብብርና ኅብረት ለመለወጥ የመጀመሪያው መሆን አለብን። ይህ ሁሉ የሚቻለው የትህትናን መንገድ በመከተል ብቻ ነው።

የሲኖዶሱ ጉባኤ በተከፈተበት ወቅት ተሳትፎ፣ ህብረት እና ተልእኮ ሶስት ቁልፍ ቃላትን ተጠቅሜ ነበር። እነዚህ ቃላት እዚህ በኩሪያ ውስጥ የምንገኝበት የትህትና ዘይቤ ልጠቁማቸው የምፈልጋቸው ሦስቱ መስፈርቶች ናቸው። የትህትናን መንገድ በተግባር የምንከተልበት ተጨባጭ መንገድ ለማድረግ ሶስት መንገዶች አሉ።

በመጀመሪያ ተሳትፎ የሚለው ነው። ይህ በጋራ ኃላፊነት ዘይቤ መገለጽ አለበት። በእርግጠኛነት፣ በአገልግሎታችን እና በአገልግሎታችን ልዩነት ውስጥ፣ ኃላፊነቶች ይለያያሉ፣ ነገር ግን በሌላ ሰው የተነደፈውን ፕሮግራም የመተግበር ግለኝነትን የሚያጎድል ልምድ ሳይኖረው ሁሉም ሰው እንደተሳተፈ እንዲሰማው፣ ለሥራው አብሮ ኃላፊነት እንዲሰማው ማድረግ አስፈላጊ ነው። በኩሪያ ውስጥ የፈጠራ ችሎታ ባጋጠመኝ ጊዜ ሁል ጊዜ እገረማለሁ። አልፎ አልፎ አይከሰትም፣ ይህ የሚከሰተው በተለይ ክፍሉ በተሰራበት እና ለሁሉም ሰው፣ በተዋረድ ለሚታዩትም ቢሆን፣ የመገለል ቦታን የሚይዝበት ቦታ አለ። ለእነዚህ ምሳሌዎች አመሰግናችኋለሁ እና ሁሉም ሊፈጽሙት ባለው ተልዕኮ ውስጥ ንቁ ሚና እንዳላቸው የሚገነዘቡ ተጨባጭ ለውጦችን ለመፍጠር እንድንችል እንድትሰሩ አበረታታለሁ። ስልጣን አገልግሎት የሚሆነው ሰዎች እንዲያድጉ ሲያካፍል፣ ሲያሳትፍ እና ሲረዳ ነው።

ሁለተኛው ቃል ሕብረት የሚለው ነው። ይህ ከአብዛኞቹ ወይም አናሳዎች ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፣ በመሠረቱ ከክርስቶስ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው። ክርስቶስን ወደ መሃል ካላስቀመጥነው በቀር በየቦታው የወንጌል ዘይቤ ሊኖረን አይችልም። ብዙዎቻችን አብረን እንሰራለን፣ነገር ግን ኅብረትን የሚገነባው አብረን መጸለይ፣የእግዚአብሔርን ቃል በአንድነት ማዳመጥ እና ከስራ ያለፈ ግንኙነት መመስረት እና እርስ በርስ በመረዳዳት ጠቃሚ ግንኙነቶችን በማጠናከር ነው። ያለበለዚያ፣ አንድ ቦታ ላይ የሚሰሩ እንግዶች፣ ወደፊት ለመራመድ ከሚፈልጉ ተወዳዳሪዎች፣ ወይም ይባስ ብሎ በግል ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ከመመሥረት፣ የሚያገናኘንን የጋራ ጉዳይ ከመዘንጋት የዘለለ የመሆን አደጋ አለን። ይህ ልዩነትን፣ መከፋፈልንና ጠላትነትን ሲፈጥር መተባበር ግን የራሳችንን አድልዎ ለመቀበል እና እንደኛ ከማያስቡትም ጋር በቡድን ለመሥራት ክፍት እንድንሆን ትልቅነት ይጠይቃል። በትብብር፣ ሰዎች አብረው የሚሠሩት ለአንድ የተለየ ዓላማ ሳይሆን፣ የሌሎችን መልካም ነገር በልባቸው ስላላቸው እና ስለዚህም እንድናገለግለው የተጠራንለት የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነው። የሰዎችን ትክክለኛ ገጽታ አንርሳ። በእምነት የመጀመሪያዎቹ አስተማሪዎች የነበሩትን ሥሮቻችንን እና ተጨባጭ ፊታችንን አንርሳ።

ነገሮችን ከኅብረት አንፃር ማየት ልዩነታችንን እንደ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መቀበልንም ይጨምራል። ከዚህ ወደ ኋላ ስንመለስ እና ህብረትን እንደ አንድ አይነት ተመሳሳይነት ስንቆጥር በመካከላችን ያለውን የመንፈስ ቅዱስን ሕይወት ሰጪ ኃይል እናዳክማለን። የአገልግሎት አመለካከት በእግዚአብሔር ሕዝብ ውስጥ ያለውን ልዩ ልዩ ብልጽግናን ለማወቅ እና በደስታ ለመለማመድ ጥሩ እና ለጋስ ልብ ይፈልጋል፣ እና ይጠይቃል። ያለ ትህትና ይህ አይሆንም።

ሦስተኛው ቃል ተልዕኮ የሚለው ነው። በራሳችን ላይ ተሰናክለን እንዳንወድቅ የሚያድነን ይህ ነው። በራሳቸው የተመለሱት “ከላይም ከሩቅም ይመለከታሉ፣ የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ትንቢት ይቃወማሉ፣ ጥያቄ የሚያነሱትን ያዋርዳሉ፣ የሌሎችን ስህተት ያለማቋረጥ ይጠቁማሉ እና በመልክ ይጠመዳሉ። ልባቸው የተከፈተው ለራሳቸው እውቀት እና ፍላጎት ውስን አድማስ ብቻ ነው፣ እናም በዚህ ምክንያት ከኃጢአታቸው አይማሩም ወይም ለይቅርታ በእውነት ክፍት አይደሉም። ይህ ትልቅ ሙስና እንደ ጥሩ መስሎ የሚታይ ነው። ቤተክርስቲያኗ ያለማቋረጥ ከራሷ እንድትወጣ በማድረግ፣ ተልእኳዋን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማተኮር እና ለድሆች ያላትን ቁርጠኝነት በማቆየት የዚህ ዓይነት ደካማ አስተሳሰቦቻችንን ልናስወግደው ይገባናል።” ( Evangelii Gaudium፣ 97) የምናደርገውን ነገር ሁሉ፣ ማስታወቂያ ከመስራት ባሻገር ተጨማሪ፣ በጌታ ጥሪ ዳግም የማመንጨት ኃይል ምልክት መደረጉን ለተልዕኮው ክፍት የሆነ ልብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። ተልዕኮ ሁል ጊዜ ለድሆች፣ “ለተቸገሩ”፣ ቁሳዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊ እና ሥነ ምግባራዊ ፍቅርን ያካትታል። እንጀራ የሚራቡና ፍቅር የሚራቡ እኩል ድሆች ናቸው። ቤተክርስቲያን ወደ እያንዳንዱ የድህነት አይነት እንድትደርስ ተጠርታለች። ሁላችንም ድሆች ስለሆንን ቤተክርስቲያን ለሁሉም ወንጌልን እንድትሰብክ ተጠርታለች። ሁላችንም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ችግረኞች ነን። ነገር ግን ቤተክርስቲያን ድሆችን ስለምንፈልጋቸውም ትደርስላቸዋለች፡ ድምፃቸው፣ መገኘት፣ ጥያቄዎቻቸው እና ትችቶች ያስፈልገናል። የሚስዮናዊ ልብ ያለው ሰው ወንድሙ ወይም እህቱ አለመኖራቸው ይሰማዋል። ተልዕኮ ተጋላጭ ያደርገናል። ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እንድናስታውስ ይረዳናል እናም የወንጌልን ደስታ እንደገና እንድናገኝ ያደርገናል።

ተሳትፎ፣ ተልእኮ፣ እና ህብረት የትሁት ቤተክርስቲያን ባህሪያት ናቸው፣ ለመንፈስ ድምጽ ትኩረት የሚሰጥ እና በራስ ላይ ያተኮረ አይደለም። ሄንሪ ዴ ሉባክ እንደጻፈው፡- “እንደ ጌታዋ፣ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዓይን እንደ ባሪያ መልክ ትቆጠራለች። በዚህች ምድር ላይ፣ ‘በባሪያ መልክ’ ትኖራለች… እሷ የተማሩ ልሂቃን ሰዎች የተሰበሰቡባት አካዳሚ ከመሆን ባሻገር የላቁ የመንፈሳዊ ሊቃውንት ወይም የበላይ ሰዎች ስብስብ አይደለችም። በእውነቱ እሷ በጣም ተቃራኒ ነች። ጠማማው፣ አስመሳይ እና ምስኪን በጣም ደግ የሆነው ሕዝብ ሁሉ በአንድነት የሚኖሩባት ሥፍራ ናት” ይለናል።

በማጠቃለያው፣ ለእናንተ እና ለራሴ ያለኝ ፍላጎት፣ የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ዓለም በገባበት ድህነትና ቀላልነት፣ በገና በዓል እና በግርግም ትህትና፣ ወንጌልን እንድንሰብክ እንድንፈቅድ ነው። ከማርያም እና ከዮሴፍ ወይም ከቤተልሔም እረኞች ከፍ ያለ ማሕበራዊ ቦታ የነበሩት ሰብአ ሰገል እንኳ በሕፃኑ ፊት ተንበርክከው ወድቀዋል (ማቴ. 2፡11)። ይህን ማድረግ የውዳሴ ምልክት ብቻ ሳይሆን የትህትናም ምልክት ነው። በባዶ ምድር ላይ ሲወድቁ ሰብአ ሰገል እራሳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ አደረጉ። ይህ መውረድ፣ ኢየሱስ በምድራዊ ህይወቱ የመጨረሻ ምሽት “ከእራት ተነሣ፤ መጐናጸፊያውን አስቀመጠ፤ ወገቡንም በፎጣ ታጠቀ። ከዚያም በመታጠቢያው ውሃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር እያጠበ በታጠቀው ፎጣ ያብስ ጀመር” (ዮሐ 13፡4-5) ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ጴጥሮስ ለዚህ ምልክት የሰጠው ምላሽ በጣም አሳዛኝ ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ ራሱ ደቀ መዛሙርቱን የሚተረጉሙበትን ትክክለኛ መንገድ አሳይቷቸዋል:- “እናንተ፣ ‘መምህርና፣ ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ ትክክል ነው፤ እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ” (ዮሐ 13፡13-15)።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ የራሳችንን ደዌ እያሰብን፣ ከሥሮቻችንና ከቅርንጫፎቻችን ከሚለየንን ዓለማዊ አስተሳሰብ በመራቅ፣ በሕፃኑ በኢየሱስ ትሕትና ወንጌልን እንድንሰብክ እንፍቀድ። በማገልገል ብቻ እና ስራችንን እንደ አገልግሎት በማየት ሁሉንም ሰው በእውነት መርዳት እንችላለን። እኛ እዚህ ነን - እኔ ራሴ ከማንም በፊት - ጌታን በትህትና እንዴት ተንበርክኬ ማምለክ እንዳለብኝ ለመማር እንጂ እንደ ሌሎች ጌቶች ለመሆን አይደለም እዚህ ያለውት። እኛ እንደ እረኞች ነን፣ እኛ እንደ ሰብአ ሰገል ነን። እኛ እንደ ኢየሱስ ነን። ይህ የገና ትምህርት ነው፡ ትህትና ለእምነት፣ ለመንፈሳዊ ህይወት እና ለቅድስና ትልቅ መስፈርት ነው። በውስጣችን ያለው የመንፈስ ህላዌ ምልክት ማለትም ምኞትን በመጀመር ጌታ እንደ ስጦታ ይስጠን። የጎደለን ነገር ቢያንስ መመኘት መጀመር እንችላለን። እናም ያ ፍላጎት መንፈስ በእያንዳንዳችን ውስጥ እየሰራ መሆኑን ያሳያል።

መልካም ገና ለሁሉላችሁም! እባካችሁን ለእኔ መጸለይ እንዳትዘነጉ!

 

23 December 2021, 15:02