ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በእግዚአብሔር የታቀደ ፍትሐዊ ሕይወትን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ኅዳር /2014 ዓ. ም. ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ትናንት በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ባቀረቡት ሳምንታዊ አስተምህሮአቸው፣ በእግዚአብሔር የታቀደ ፍትሐዊ ሕይወትን ማዳበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ክብራትና ክቡራን አድማጮቻችን፣ የቅዱስነታቸውን አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን ከዚህ በታች እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ!

የቅዱስ ዮሴፍን ማንነት ለማወቅ የምናደርገውን አስተንትኖ ዛሬም እንቀጥላለን። በዛሬው አስተምሮ የቅዱስ ዮሴፍን ፍትሃዊ ማንነት እና የማርያም እጮኛነት የሚገልጹ ሃሳቦችን ይበልጥ ማጠናከር እፈልጋለሁ። ይህም እጮኛሞች እና አዲስ ተጋቢዎች መልዕክት እንዲሆናቸው በማለት ነው። ከዮሴፍ ሕይወት ጋር የተያያዙ፣ ነገር ግን ቀኖናዊ ያልሆኑ፣ በሥነ-ጥበብና በተለያዩ የአምልኮ ቦታዎች ላይ ተጽዕኖን የሚያሳድሩ ብዙ ታሪኮች አሉ። በሥነ ጥበብ በኩል የምናገኛቸው ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚጎድሉትን የቅዱስ ዮሴፍ ታሪኮች በመሙላት ለእምነት እና ለክርስቲያናዊ ሕይወት አስፈላጊ መልሶችን ይሰጣሉ።

ለወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ይህ እጅግ አስፈላጊ ነው። ለመሆኑ ቅዱስ ወንጌል ስለ ዮሴፍ ሕይወት ምን ይነግረናል? መንፈሳዊነት ያላቸው የሥነ-ጥበብ ሥራዎች በቀዳሚነት የሚመረጡ ባይሆኑም የሚናቁ አይደሉም። በእርግጥም መልካም ናቸው፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል አይደሉም።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ወንጌላት የእግዚአብሔር ቃል ናቸው። የዮሴፍን “ጻድቅነት” ከሚገልጹ መጽሐፍት መካከል አንዱ ወንጌላዊው ማቴዎስ የጻፈው ይገኝበታል። እርሱ የጻፈውን እንመልከት። በማቴ. 1፡18-19 እንዲህ የሚለውን እናገኛለን፥ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ሁኔታ እንዲህ ነው ፥ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ደግ ሰው ስለነበረ ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት አልፈለገም። ስለዚህ በስውር ሊተዋት አሰበ።’ ምክንያቱም አንድ የታጨች ልጅ ለእጮኛዋ ታማኝ ሆና ሳትገኝ ቀርታ ፀንሳ ብትገኝ ልትከሰስ እና በድንጋይም ልትወገር ትችላለች። ነገር ግን ዮሴፍ ፍትሃዊ ሰው ስለ ነበር ‘እኔ ይህን አላደርግባትም’ በማለት በዝምታ ማለፍን መረጠ።

ዮሴፍ ለማርያም የነበረውን አስተያየት ለመረዳት ጥንታዊውን የእስራኤል የጋብቻ ልማዶች ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ጋብቻ በደንብ የተገለጹ ሁለት ደረጃዎችን ያጠቃልላል። የመጀመሪያው አዲስ ምዕራፍ የሚታይበት ግልጽ የእጮኝነት ደረጃ ነው። በተለይም የታጨች ልጅ ከወላጆቿ ጋር ለአንድ ዓመት ያህል ስትኖር የትዳር ጓደኛው "ሚስት" ተደርጋ ትወሰዳለች። እጮኛሞቹ አብረው ባይኖሩም ሴቷ ቀድሞውኑ የአንድ ሰው ሚስት እንደሆነች ትቆጠራለች። ሁለተኛው ምዕራፍ ሙሽሪት ከወላጆቿ ቤት ወጥታ ወደ ትዳር ጓደኛዋ ቤት የምትሸጋገርበት ነው። ይህም በዓል ተዘጋጅቶ ጋብቻ የሚፈጸምበት ሥነ-ሥርዓት ነው።

የሙሽሪት ወዳጆች ወደሙሽራው ቤት ይሸኟታል። በእነዚህ ልማዶች መሠረት ‘አንድ ላይ ለመኖር ከመምጣታቸው በፊት ማርያም ፀንሳ ተገኘች’ የሚለው እውነታ ማርያምን ለክስ አጋልጧት ነበር። በጥንት ህግ መሠረት ማርያም በድንጋይ እንድትወገር ያደርጋት ነበር። በኦሪት ዘዳ. 22፡20-21 እንዲህ ተብሎ የተጻፈውን እናገኘዋለን፥ ነገሩ ግን እውነት ቢሆን፥ የብላቴይናዪቱም ድንግላናዋ ባይገኝ፥ ብላቴናዪቱን ወደ አባቷ ቤት ያውጧት፤ በእስራኤልም ዘንድ ስንፍናን አድርጋለችና፥ የአባቷን ቤት አስነውራለችና የከተማው ሰዎች በድንጋይ ወግረው ይግደሏት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ። ቢሆንም፣ በኋለኞቹ የአይሁድ ልማዶች ላይ መጠነኛ ትርጉም ተሰጥቶት በሴቷ ላይ የወንጀል ክስ በማቅረብ እስከ መለያየት ድረስ ይደርሳል እንጂ በድንጋይ መውገርን አያስከትልም።

ቅዱስ ወንጌል፣ ዮሴፍ እንደ ማንኛውም እስራኤላዊ ለሕግ የሚገዛ ስለነበር “ጻድቅ” እና ደግ ሰው እንደነበር ይነግረናል። ነገር ግን በእርሱ ውስጥ ለማርያም ያለው ፍቅር እና በእርሷ ላይ ያለው እምነት፣ ሕግን በማክበር የሚቀጥልበትን እና የሙሽራነት ክብር የሚታደግበትን መንገድ ይጠቁማል። ስለዚህ ለሕዝብ ተናግሮ ቅጣት እንዲከተላት ሳያደርግ ድብቆ ለማለፍ ወሰነ። ወደ ፍርድ ሳይሄድ ወይም የበቀል እርምጃን ሳይወስድ በምስጢር የሚያልፍበትን መንገድ መረጠ። ዮሴፍ ምንኛ ቅዱስ ነበር! ሰውን የሚያስከፋ ትንሽ ወሬ ቢናገኝ ወዲያው ዞር ብለን እናወራለን! ሰውንም እናስቀይማለን። ነገር ግን ዮሴፍ ዝምታን መረጠ።

ወንጌላዊው ማቴዎስ ግን ወዲያው እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፥ ይህን ሲያስብ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ በሕልሙ ተገልጦለት እንዲህ አለው፥ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! እጮኛህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ። እርሷ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፥ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ስለሚያድን ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።’ “ማቴ. 1:20-21) በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ድምፅ ለዮሴፍ ማስተዋልን ሰጠ። ከራሱ ፍትሃዊ አስተሳሰብ ይልቅ ሌላ ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር መኖሩን እግዚአብሔር በሕልም ገለጠለት። ለእያንዳንዳችን ፍትሃዊ ሕይወትን ማዳበር ጠቃሚ እንደሆነ፣ የአስተሳሰብ አድማሳችንን በማስፋት ሕይወትን ሰፋ ባለ እይታ መመልከት እና ሁል ጊዜ የእግዚአብሔር እርዳታ እንደሚያስፈልገን የምንረዳ ስንቶቻችን ነን? ብዙ ጊዜ በደረሰብን ነገር የታሰርን እንደሆነ ይሰማናል። በመሆኑም በደረሰብን መጥፎ ነገር ታስረን እንቆያለን። በተለይም መጀመሪያ ላይ አስገራሚ በሆኑ አንዳንድ የሕይወት ገጠመኞች ፊት ልንገኝ እንችላለን። ፈተና የሚመጣው በህመም ውስጥ ተዘግተን መቆየት ስንጀምር ነው፣ መልካም ነገር እንደማያጋጥመን ማሰብ ስንጀምር ነው። ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ለሐዘን እና ለምሬት ስለሚዳርገን ለእኛ ጥሩ አይደለም፤ መራራ ልብ ሲኖረን ጥሩ አይደለም።

በወንጌል ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነገረውን የዚህን ታሪክ ዝርዝር ሁኔታ ቆም ብለን ልናሰላስለው ያስፈልጋል። ማርያም እና ዮሴፍ አንዱ ለሌላው የሚጨነቁ እና የሚያስቡ እጮኛሞች ነበሩ። ምናልባትም ስለወደፊቱ ሕይወታቸው በማለም ተስፋ አድርገው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ሆኖ ቢታያቸውም፣ ሁለቱም በፊታቸው ለተቀመጠው እውነታ ልባቸውን በሰፊው ከፍተዋል።

ውድ ወንድሞች እና ውድ እህቶች! ሕይወታችን ብዙውን ጊዜ እኛ እንደምናስበው አይደለም። በተለይም በፍቅራዊ ግንኙነት ወቅት ከመዋደድ አመክንዮ ወደ በሳል የፍቅር አመክንዮ መሸጋገር አስቸጋሪ ነው። ከተራ ፍቅር ወደ በሳል ፍቅር መሸጋገር አለብን። እናንተ አዲስ ተጋቢዎች፣ ስለዚህ ጉዳይ አስቡበት። የመጀመሪያው የፍቅር ምዕራፍ ሁሌም በእውነታው ላይ ባልተመሠረተ ምናባዊ ነገር ተውጠን እንድንኖር ያደርገናል። በፍቅር መውደቅ ማለት ነው። ነገር ግን በፍቅር መውደቅ የሚያበቃ በሚመስልበት ጊዜ ፣ ያኔ እውነተኛ ፍቅር ይጀምራል ወይም እውነተኛ ፍቅር በእዚያ ውስጥ ሊገባ ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ማፍቀር ማለት የሌላውን ሰው ሕይወት ከምናባችን ጋር ማመሳሰል አይደለም። ይልቁንም እንደአመጣጡ የሕይወት ኃላፊነት ለመውሰድ ሙሉ ነፃነትን መምረጥ ማለት ነው።

ይህን በተመለከተ ዮሴፍ ጠቃሚ ትምህርት የሰጠን ለዚህ ነው። ማርያምን "ዓይኖቹን ከፍቶ" መረጣት። "ሊከተሉት ከሚችሉ አደጋዎች" ጭምር ማለት ነው። እስቲ ይህን አስቡ። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የሕግ መምህራን ለኢየሱስ ክርስቶስ በሰጡት አስተያየት፡- “እኛ እንደነዚያ ልጆች አይደለንም” ሲሉ፣ ዝሙት አዳሪነትን ያመለክታል። ማርያም እንዴት እንዳረገዘች ጠንቅቀው ቢያውቋም በኢየሱስ እናት ላይ ጥላሸት ለመቀባት ፈልገው ያሉት ነው። ይህ አነጋገር በወንጌል ውስጥ እጅግ አስከፊ እንደሆነ ይገባኛል።

ዮሴፍን ያጋጠመው ወይም ሕይወትን እንደ አመጣጡ መውሰዱ ለእኛ ትምህርት ይሆነናል። እግዚአብሔር በሕይወታችን ጣልቃ እንዲገባ እንፈቅድለታለን? ዮሴፍ የእግዚአብሔር መልአክ ያዘዘውን አደረገ። ዮሴፍም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ የእግዚአብሔ መልአክ ባዘዘው መሠረት እጮኛውን ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት፤ ይሁን እንጂ ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ዮሴፍም የተወለደውን ሕጻን ስም ‘ኢየሱስ’ አለው። (ማቴ. 1: 24-25) ለጋብቻ የታጩ ክርስቲያን ጥንዶችም በፍቅር ከመውደቅ አመክንዮ ወደ በሳል ፍቅር የመሸጋገር ድፍረትን እንዲመሰክሩ ተጠርተዋል። ይህም በሕይወት ከመታሰር ይልቅ ፈተናን ተጋፍጦ ፍቅርን ለማጠናከር የሚያስችል ምርጫ ነው። የባልና የሚስት ፍቅር በየቀኑ እያደገ የሚመጣ ነው። በእጮኛነት ወቅት የሚገለጽ ፍቅር ግን ወደ ስሜትታዊነት ያዘነበለ ፍቅር ማለት ይቻላል። ሁላችሁም ፍቅርን የተለማመዳችሁ ቢሆንም ቀስ በቀስ አሳድጋችሁታል። ፍቅር በሕይወት መካከል በየቀኑ የሚያድግ፣ በሥራው ዓለም፣ ልጅ በሚወለድበት ጊዜ የሚገለጽ እና የሚያድግ ነው። በትዳር ሕይወት መካከል እንቅፋቶች የተለያዩ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። እርስ በእርስ መቀያየም ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ሁሌም ማስታወስ የሚገባው፣ ወደ ሰላም ሳይደርሱ ቀኑ ሊመሽ አይገባም። ከስሜታዊ ፍቅር ወደ በሳል ፍቅር የሚደረግ ጉዞ ምርጫን ይጠይቃል። መከተል ወይም መምርጥ የሚገባው መንገድም ይህ መሆን አለበት።

የዛሬውንም አስተምህሮ ወደ ቅዱስ ዮሴፍ በምናቅረበው ጸሎት እናጠቃልላለን፥

ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ!

ማርያምን በነጻነት ወድሃታል፤ ለሆነው ነገር ሁሉ ምክንያት መስጠትን መርጠሃል፤ እያንዳንዳችንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንድንከተል እርዳን፤ ሕይወትን ራሳችንን የምንከላከልበት ሳይሆን እውነተኛ ደስታ የሚገኝበት አድርገን እንድንቀበለው እርዳን፤ ለጋብቻ የሚዘጋጁ ክርስቲያኖች በሙሉ ደስታን የሚያገኙት እና ፍቅራቸውን ዘላቂ ማድረግ የሚችሉት በምሕረት እና በይቅርታ ብቻ መሆኑን ዘወትር እንድናውቅ እርዳን። አሜን።”

02 December 2021, 16:26