ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት ከነባራዊ በረሃማ ስፍራዎች እንድንሻገር ይረዳናል አሉ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ትላንት እሁድ ኅዳር 26/2014 ዓ.ም በአቴንስ ግሪክ ከሚገኙት የካቶሊክ ማኅበረሰብ አባላት በተገናኙበት ወቅት ቅዱስነታቸው መስዋዕተ ቅዳሴ ያሳረጉ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ በእለቱ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተጀመረውን ሁለተኛ የስብከተ ገና ሳምንት ከግምት ያስገባ ስብከት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን በሕይወታችን ውስጥ “ነባራዊ ምድረ በዳዎች” ቢኖሩም ጌታ ሁል ጊዜ እርሱን ከፈለግን ባዶነታችንን ሊሞላልን ስለሚመጣ በተስፋ እንድንጠብቅ” ቅዱስነታቸው አበረታተዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ ግሪክ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሁለተኛው ቀን እሁድ ከሰአት በኋላ በአቴንስ በሚገኘው ሜጋሮን ኮንሰርት አዳራሽ ከአካባቢው የካቶሊክ ማህበረሰብ ጋር ተገናኝተው መስዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል።

የኮቪድ-19 ቫይረስን ለመከላከል በወጡት ሕጎች መሠረት ወደ 2,000 የሚጠጉ አማኞች ብቻ በሁለት የተለያዩ አዳራሾች እንዲገኙ ተደርገዋል። ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አቴንስ የተመለሱት በግሪክ ሌስቦስ ደሴት ካደረጉት ጉብኝት በኋላ እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪዎች እና ከግሪክ ፕሬዝዳንት እና ባለስልጣናት ጋር በመሆን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚገኙበትን ሥፍራ በመጎብኘት አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሁለተኛው የስብከተ ገና ሳምንት መግቢያ እሑድ እለት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በእለቱ የቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 3) ንባብ ላይ አስተንትኖ ያደረጉ ሲሆን ይህም መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ በምድረ በዳ ሰዎችን ወደ ክርስትና ሕይወት መጥራቱን ይናገራል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት የበረሃው ምስል የመቤዠት መንገድ ከዓለማዊ የስልጣን ቦታዎች አንፃር እንዴት እንዳልተጀመረ እንድንገነዘብ ያደርገናል፣ ይህም እኛ የምንጠብቀው ነገር ነው፣ የተጀመረው እጅግ በጣም ድሃ እና ቀላል ከሆነ ስፍራ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ የማይደረስበት እና አደገኛ ቦታ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ልክ በበረሃው ሰፊና በረሃማ ስፍራ "የእግዚአብሔር ክብር ተገለጠ"። ይህ በሰው ልጆች እይታ ስንመልከተው እጅግ በጣም የሚያስደንቅ ነገር ነው፣ ነገር ግን ልናደንቀው የሚገባ ውብ መልእክት ነው ምክንያቱም ጌታ የሚገለጠው በትሁት እና ትናንሽ በሚመስሉ ነገሮች ነው፣ በምድረ በዳ የተመሰሉት ድሆች እንደሆነ ሁሉ" ያለ ኩራት በውስጣችን ድሆች መሆን አለብን ብለዋል።

ጌታ የእኛን ነባራዊ በረሃዎች ጎበኘ

መጥምቁ ዮሐንስ የክርስቶስን መምጣት አስፈላጊነት በመስበክ በምድረ በዳ መንገዱን ያዘጋጃል በማለት የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሁንም እንደዚያው፣ ፈተና ወይም ሀዘን በሚያጋጥመን ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር ዓይኑን ወደ እኛ ያዞራል፣ እንዲሞላልን ከፈቀድንለት ሊደርስልን ይችላል ያሉ ሲሆን "ነባራዊ በረሃማ ስፍራዎቻችንን" በመጎብኘት የውስጣችን ባዶነት በመንፈሱ ይሞላል ብለዋል።

በህይወታችን ውስጥ ብዙ ጊዜ በምድረ በዳ ውስጥ እንደጠፋን የሚሰማን ጊዜ አለ “በትክክል በዚያን ጊዜ ነው ጌታ መገኘቱ የሚሰማን” ትዕቢቶቻችንን ወደ እርሱ ማቅረብ እርሱን እንዳንገናኝ አያግደንም፣ ምክንያቱም እርሱ ትዕቢቶቻችንን በሙሉ የማስወገድ ችሎታ አለውና ነው ብለዋል።

ጌታ “በቅርብ፣ በርኅራኄና በምሕረት ቃል ይጎበኘናል፣ መጥመቁ ዮሐንስ በምድረ በዳ መስበክ፣ እግዚአብሔር በየትኛውም ቦታ እንደሚጎበኘን፣ በፍቅሩ ትንንሽ መሆናችንን ተገንዝቦ የደረቁ መንፈሳችንን ያድሳል” የሚለውን መልእክት ያስተላልፋል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተለይ ምዕመናን ትናንሽ መሆንን በፍጹም መፍራት የለብንም፣ ነገር ግን በይበልጥ "ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ክፍት መሆን" ይኖርብናል ብለዋል።

መለወጥ ማለት "ከዚህ ባሻገር ማሰብ" ማለት ነው

የመጥምቁ ዮሐንስ አጽንዖት “መለወጥን” በመስበክ ላይ የሰጠው ትኩረት መጀመሪያ ላይ ግራ እንድንጋባ ያደርገናል ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አስገንዝበዋል። መንገዳችንን መለወጥ እንዴት እንደሚያሳዝን ስለምንገነዘብ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንፈራለን ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ ግን ብዙውን ጊዜ የምንመለከተው በሥነ ምግባር ላይ ከመድረስ አንጻር ብቻ ስለሆነ ነው፣ ፍጹምነት፣ በራሳችን ልናሳካው የማንችለው ነገር ስለሆነ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የኖርብናል ብለዋል።

ችግራችን ሁሉም ነገር በእኛ ብቻ የሚወሰን ነው ብሎ በማሰብ ላይ የተመረኮዘ ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እናም በወንጌል ውስጥ ለእሱ ጥቅም ላይ የዋለውን የግሪኩን ቃል"metanoeίn” (መለወጥ) የሚለውን ቃል ሙሉ ፍቺ መመልከት አለብን ብለዋል። የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉሙ "ከዚህ ባሻገር ማሰብ" ማለት እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህም ማለት ከተለመዱት የአስተሳሰብ መንገዳችን አልፈን ከልማዳዊ የዓለም አተያይ መውጣት ማለት ነው ብለዋል።

ራሳችንን መቻል ላይ ያለንን እምነት መተው ወይም ስለ ራሳችን እና ነገሮችን ስለምናደርግበት መንገድ ብቻ ማሰብ ማለት እንደሆነ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው "ወደ መንፈሳዊ ለውጥ እኛን በመጥራት መጥመቁ ዮሐንስ አሁን ካለንበት የሕይወት ዘይቤ 'ባሻገር' እንድንሄድ አጥብቆ ያሳስበናል" ምክንያቱም "እውነታው እግዚአብሔር ታላቅ መሆኑን ስለሚያስ ነው" ብለዋል።

እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ከአጠገባችን አለ።

መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት ማለት "እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር አለ" ብለን በእርሱ መታመን እንዳለብን ማወቅ ማለት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው "እርሱ ከአቅማችን በላይ ነውና ኃይላችን ነው፣ ለክርስቶስን በር መክፈት ብቻ ያስፈልገናል፣ ገብቶ ተአምራቱን እንዲያደርግ ልንፈቅድለት የገባል" ብለዋል። በእኛ ውስጥ "ክርስቶስ ወደ ዓለም ይመጣ ዘንድ የሚያስፈልገው ምድረ በዳና የመጥመቁ ዮሐንስ ስብከት ብቻ ነው" በማለት አክለው ገለጸዋል።

በእግዚአብሔር ዘንድ ነገሮች በእርግጥ ይለወጣሉ።

በማጠቃለያም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁላችንም እንድናምን ጸጋን እንዲሰጠን መጸለይ እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን "በእግዚአብሔር ዘንድ ነገሮች በእውነት እንደሚለወጡ" ፍርሃታችንን እንደሚያስወግድ፣ ቁስላችንን እንደሚፈውስ እና "ደረቃማ ቦታዎቻችንን ወደ ውኃ ምንጭነት እንዲለውጥ" መጸለይ ይኖርብናል ብለዋል።

እርስ በርሳችን ለመረዳዳት እምነታችንን መንከባከብ እንችል ዘንድ የተስፋ ጸጋን እንጠይቃለን፣ የዛሬው ዓለም በረሃዎች የተጠሙት ብዙ ነገሮች ስላሉ ጌታ በመንፈሳዊ ውሃ ያረሰርሳቸው ዘንድ ተግተን መጸልይ ይኖርብናል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

05 December 2021, 14:35