ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከእውርነት የምንፈወሰው በሕብረት ስንቆም ብቻ ነው አሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቆጵሮስ እያደርጉት በሚገኘው ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁለተኛ ቀን ላይ በርካታ ምዕመናን በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት የቆጵሮስ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከምንገኝበት ተመሳሳይ ጨለማ ነፃ ለመውጣት ሦስት እርምጃዎችን እንዲከተሉ ለማሳሰብ ከማርቆስ ወንጌል የተወሰደውን የሁለቱ ዓይነ ስውራን ምሳሌ ጠቅሰው ከጨለማ መውጣት የምንችለው በጋራ ስንቆም ብቻ እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቆጵሮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ስብከት በእለቱ ከማርቆስ ወንጌል የተወሰደውን ክፍል በማስታወስ ኢየሱስ ሲያልፍ ሁለት ዓይነ ስውራን “የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን” ብለው መጮኸቸውን አስታውሰዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁለቱ ሰዎች ዓይነ ስውራን ቢሆኑም ኢየሱስ ወደ ዓለም የመጣ መሲሕ መሆኑን ግን ተገንዝበዋል ያሉ ሲሆን በዚህ በስብከተ ገና ሰሞን "ጌታን እንዴት መቀበል እንደ ሚገባን” ሊረዱን ይችላሉ ብለዋል።

 ደረጃ አንድ፡ ወደ ኢየሱስ መሄድ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ የመጀመሪያው እርምጃ ሁለቱ "ለመፈወስ ወደ ኢየሱስ ሄደው ነበር" ብለዋል። ሊያዩት ባይችሉም “ድምፁን ሰምተው ፈለጉን ይከተሉታል” በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ያሉት ሁለቱ ሰዎች በኢየሱስ ታምነዋል፣ ያሉ ሲሆን ስለዚህ ለዓይኖቻቸው ብርሃን ፍለጋ የእርሱን ድምጽ እንደ ተከተሉ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁለቱ በኢየሱስ የታመኑበት ምክንያት “በታሪክ ጨለማ ውስጥ እርሱ የልብንና የዓለምን “ምሽቶች” የሚያበራ ብርሃን መሆኑን ስለሚገነዘቡ ነው ያሉ ሲሆን እኛም በልባችን ውስጥ አንድ ዓይነት “ዕውርነት” እንዳለን አበክረው ገልጿል፣ እናም ልክ እንደ ሁለቱ ዓይነ ስውሮች ብዙውን ጊዜ በሕይወት ጨለማ ውስጥ ገብተን እንገኛለን፣ ብዙ ጊዜ በራሳችን ተዘግተን፣ ብቻችንን በጨለማ ውስጥ፣ ለራሳችን በማዘን እና እንደ ባልንጀራችን ሀዘን እንዲኖረን እንመርጣለን፣ ነገር ግን በምትኩ ወደ ኢየሱስ መሄድ አለብን ሲሉ ጳጳሱ የተናገሩ ሲሆን ኢየሱስ ልባችንን እንዲፈውስ እድል እንስጠው ብለዋል።

ደረጃ ሁለት፡ ሥቃያቸውን መጋራት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሚቀጥለው እርምጃ "ሥቃያቸውን ተካፍለዋል" የሚለው ነው ብለው በመናገር ስብከታቸውን የቀጠሉ ሲሆን አብረው በጋራ ሆነው እርዳታ ይጠይቃሉ ብሏል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ። "ይህ የክርስቲያናዊ ህይወት እና የቤተክርስቲያን መንፈስ ልዩ ባህሪ ምልክት ነው፣ ማሰብ፣ መናገር እና እንደ “እኔ” ሳይሆን እንደ "እኛ" ማድረግ፣ ግለሰባዊነትን እና ልብን የሚጎዳ ራስን የመቻል ስሜትን መተው” ይኖርብናል ብለዋል።

እነዚህ ሁለት ዓይነ ስውራን ብዙ የሚያስተምሩን ነገር አለ ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን የቀጠሉ ሲሆን “እያንዳንዳችን በኃጢአት ምክንያት በሆነ መንገድ ዓይነ ስውር ነን” በማለት ተናግሯል፣ ይህ ደግሞ “እግዚአብሔርን እንደ አባታችን እንዳናየውና እርስ በርሳችን እንደ ወንድሞችና እህቶች እንዳንተያይ ይከለክላል” ብለዋል። ይህ ኃጢአት እውነታውን ያዛባል ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን የውስጣችንን ዓይነ ስውርነት ብቻችንን ከተሸከምን ልንደክም እንችላለን፣ "እርስ በርሳችን መደጋገፍ፣ ህመማችንን መጋራት እና የመጪውን መንገድ በጋራ መጋፈጥ ያስፈልገናል" ብለዋል ።

የወንድማማችነት ስሜታችንን እናድስ

ውድ ወንድሞች እና እህቶች "የራሳችንን ጨለማ እና በቤተክርስቲያን እና በህብረተሰብ ውስጥ ከፊታችን ያሉ ፈተናዎች ሲገጥሙን፣ የወንድማማችነት ስሜታችንን እንድናድስ ተጠርተናል" ያሉት ቅዱስነታቸው ተከፋፍለን ከሄድን ከዓይነ ስውርነታችን ፈጽሞ አንፈወስም” ሲሉም አክለዋል። ፈውስ እውን የሚሆነው ሕመማችንን አንድ ላይ ስንሸከም፣ ችግሮቻችንን በጋራ ስንጋፈጥ፣ ስንሰማና ስንነጋገር ነው ብለዋል።

ደረጃ ሦስት፡ ምሥራች

ሦስተኛውና የመጨረሻው ደረጃ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደ ገለጹት “ምሥራቹን በደስታ ሰበኩ” የሚለው ነው ያሉ ሲሆን ኢየሱስ ሁለቱን ዓይነ ስውሮች ከፈወሳቸው በኋላ ሁለቱ “ምሥራቹን ለአካባቢው ሁሉ ማዳረስ” ጀመሩ ብለዋል። በዚህ ውስጥ ትንሽ አስቂኝ ነገር አለ ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ። "ኢየሱስ የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ ነግሮአቸው ነበር፣ ነገር ግን ያደረጉት ተቃራኒውን ነው" አላማቸው ግን ጌታን አለመታዘዝ አልነበረም ብለዋል ጳጳሱ። "በመፈወሳቸው እና ከኢየሱስ ጋር በመገናኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በቀላሉ መቆጣጠር አልቻሉም" ነበር ይህ ደግሞ “ሌላው የክርስቲያን መለያ ምልክት ነው” ሲል አክሏል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ስብከታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ለተገኙ ሰዎች ሁሉ  የቅዱስ ወንጌልን የነጻነት መልእክት “በደስታ” ስለኖሩ አመስግነው “በዚህ መንገድ እንዲቀጥሉ” አበረታተዋል። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንዳሉት ሁለቱ ዓይነ ስውሮች፣ "አንድ ጊዜ ኢየሱስን እንገናኝ፣ ለምናገኛቸውም ሁሉ ያለ ፍርሃት የኢየሱስ ምስክሮች እንድንሆን ከራሳችን እንውጣ!" ብለዋል።

"ወንድሞች እና እህቶች ጌታ ኢየሱስም የዓይነ ስውሮችን ጩኸት እየሰማ በቆጵሮስ ጎዳናዎች እያለፈ ነው" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሳስበዋል። "አይኖቻችንን እና ልባችንን ሊነካ እና ወደ ብርሃን ሊመራን፣ በመንፈሳዊነት ዳግም መወለድን እና አዲስ ጥንካሬን ሊሰጠን ይፈልጋል" ያሉ ሲሆን በእርሱ ላይ ያለንን እምነት እናድስ ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተናግረዋል። “ለእርሱ እንንገረው፡- ኢየሱስ ሆይ፣ ብርሃንህ ከጨለማችን እንደሚበልጥ እናምናለን፤ አንተ እንድምትፈውሰን እናምናለን፣ ኅብረታችንን ማደስ ትችል ዘንድ ደስታችንን ያብዛልን" ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠቃለዋል።

03 December 2021, 16:24