ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ባደረጉት ንግግር “ልዩነቶች የማይታረቁ አይደሉም” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከኅዳር 23 እስከ 27/2014 ዓ.ም ቆጵሮስን እና ግሪክን በቅደም ተከተል ለመጎብኘት ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን ቀደም ሲል መጥቀሳችን የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በቆጵሮስ እያደረጉት በሚገኘው በሁለተኛው ቀን ሐውርያዊ ጉብኝታቸው ከቆጵሮስ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ተገናኝተዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በንግግራቸው ወቅት በካቶሊክ እና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የጋራ ትስስር እና የቅዱስ በርናባስን አርአያነት በመያዝ ጥልቅ ውይይት ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት አስምረውበታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቆጵሮስ ኦርቶዶክስ ካቴድራል ሕዳር 24/2014 ዓ.ም አርብ ጠዋት የቅዱስ ሲኖዶስ ጳጳሳት ጋር በተገናኙበት ወቅት ሰላምታ ባቀርቡበት ወቅት በቆጵሮስ መገኘታቸው የሚጋሩት “የጋራ ሐዋርያዊ ተልዕኮ” እንዳለ እንዳስታውስ አድርጎኛል ብለዋል። “ሐዋርያው ጳውሎስ ቆጵሮስን አልፎ ወደ ሮም ሄደ” ያሉት ቅዱስነታቸው “እኛም የዚያው ሐዋርያዊ ቅንዓት ወራሾች ነን፣ እናም አንድ ነጠላ መንገድ ከእኛ ጋር ይገናኛል፣ ይህ መንገድ ደግሞ የቅዱስ ወንጌል መንገድ ነው። በዛው መንገድ ስንሄድ የበለጠ ወንድማማችነትን እና ሙሉ አንድነትን እየፈለግን እንጓዛለን” ብለዋል።

መጽናናት እና መማከር

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ትኩረት ወደ ቅዱስ በርናባስ ምስል ዞሯል፣ ስሙም “የመጽናናት ልጅ” እና “የምክር ልጅ” ማለት እንደሆነ ቅዱስነታቸው በወቅቱ የገለጹ ሲሆን አክለውም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “ለቅዱስ ወንጌል መስበክ አስፈላጊ የሆኑትን ሁለቱንም ባህሪያት አጣምሮ መያዙ ተገቢ ነው” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የመጽናናት ልጆች እንድንሆን ከፈለግን አንድ ቃል ከመናገራችን በፊት እንኳን በቅድሚያ ማዳመጥ ይኖርብናል፣ ሌሎችን ለማወቅ እና ያላቸውን መልካም ነገር ለመጋራት እፈልጋለሁ ወይ? ብለን ለራሳችን ጥያቄ ማቅረብ ይኖርብናል” ያሉ ሲሆን ምክንያቱም ቅዱስ ወንጌል የሚተላለፈው በመገናኛ አውታር ብቻ ሳይሆን በኅብረት በመሥራት ጭምር ነው” ብለዋል።

ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለውም በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ካቶሊኮች በጳጳሳት ሲኖዶስ በኩል ሊለማመዱት የሚፈልጉት ይህንን ነው ብለዋል ።

ጸሎት እና ቅርበት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በንግግራቸው ወቅት በጸሎታቸው እና በቅርበት ከእነርሱ ጋር እንደ ሚሆኑ የገለጹ ሲሆን እንዲሁም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እጅግ አስጨናቂ ችግሮች በሚገጥሟቸው ወቅት ከእነርሱ ጋር እንደምትሆን እንዲሁም “በሚያበረታታቸው ጥሩ እና ድፍረት የተሞላበት ተስፋ” ውስጥም በሚገቡበት ሰዓት ጭምር አብረዋቸው እንደ ሚጓዙ አረጋግጠዋል።

“ሐዘናችሁና ደስታችሁ የእኛም ነው፤ እንደ ራሳችን እንገነዘባቸዋለን። በተመሳሳይ ጊዜ፣ የእናንተ ጸሎት በጣም እንደምንፈልግ ይሰማናል ብለዋል። በንግግራቸው ወቅት ብፁዕ አቡነ ክሪሶስቶሞስ 2ኛ ስለ እናት ቤተ ክርስቲያን በተናገሩት ንግግር ምን ያህል እንደተነኩ ቅዱስነታቸው ተናግሯል።

ያለፈው ጊዜ የነበሩ ክፍፍሎችን መወጣት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ በቅዱስ በርናባስ ሕይወት ውስጥ ከነበሩት ገጽታዎች መካከል የሚገኘው ሌላው እይታ ደግሞ ደፋር እና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ እንቅስቃሴው ነው ያሉ ሲሆን "በግልጽ ወይም በድፍረት ምልክቶችን በመፍራት ሽባ እንዳንሆን ወይም ስለ 'የማይታረቁ ልዩነቶች' ለመነጋገር አንሸነፍ" ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለውን ሁሉ በሐዋርያት እግር ሥር በማስቀመጥ ቅዱስ በርናባስ ወደ ልባቸው እንደገባ አመልክተዋል። " ካለፈው ክፍፍላችን በመላቀቅ የመንግስቱን መስክ በትእግስት፣ በብርታት እና በተጨባጭ ምልክቶች እንድናለማ ይጋብዘናል" ብለዋል።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ በሊቀ ጳጳሱ ጎልቶ የሚታየው ፓናጊያ ክሪሶፖሊቲሳ “የወርቃማው ከተማ እመቤታችን” እንደ ሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ዛሬ ለተለያዩ ክርስቲያናዊ ኑዛዜዎች እና የአምልኮ ቦታ ነው፣ ​​በሕዝቡ በጣም የተወደደ እና ብዙውን ጊዜ ለትዳር በዓላት የሚመረጥ ስፍራ ነው። "በመሆኑም ልጆቿን በአንድነት በምትሰበስብ በእግዚአብሔር እናት እይታ በእምነት እና በህይወት የመተሳሰር ምልክት ነው" ብሏል።

ውሸትን ማሸነፍ

ሌላው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የጠቀሱት ነገር በቅዱስ በርናባስ ሕይወት ውስጥ በተለይም በውሸት እና በተንኮል አድራጎት ዙሪያ የደረሰበትን ፈተናዎች ነበር። "ዛሬም ቢሆን ያለፈው ታሪክ በፊታችን ያስቀመጠው የውሸት እና የማታለል ችግር በሚገባ ይንጸባረቃል” በማለት የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ "የራሳችንን ሳይሆን የእርሱን መንገዶች እንድንከተል ጥበብ እና ድፍረት እንዲሰጠን ጌታን እንጠይቀው" ብለዋል።

ወደቦች እና ድልድዮች

በማጠቃለያው ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደገለጹት እንደ ቅዱስ በርናባስ ያሉ ብዙ ቅዱሳን እንዳሉ አመልክተዋል፣ “ሁላችንም ወደ ምንፈልግበት ወደብ አብረን እንድንጓዝ ቅዱሳኑ ያበረታቱናል። ከላይ ሆነው በምስራቅና በምዕራብ መካከል ያለውን ድልድይ፣ የሰማይና የምድር ድልድይ የሆነችውን ቆጵሮስ እንድንሠራ ያበረታቱናል” ብለዋል።

02 December 2021, 16:28