ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ግድ የለሽነትን አስወግደን የተቸገሩትን መርዳት እንደሚያፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ ያደረጉትን የሁለት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማጠናቀቃቸው በፊት ከአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጋር የጋራ ጸሎት አቅርበዋል። በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችን ጨምሮ ከልዩ ልዩ አብያተክርስቲያናት የመጡ እንግዶች በተካፈሉት የጋራ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባቀረቡት ጸሎት፣ እግዚአብሔር የሰዎችን ሕሊና እንዲያበራ ለምነው፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ልጆቹ እንደ ወንድም እህት እንደ እንዲኖሩ አስቦ እግዚአብሔር ባዘጋጀው የሰላም እቅድ ላይ አስተንትነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት ዓርብ ኅዳር 24/2014 ዓ. ም. በቆጵሮስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማጠቃለል ከሰደተኞች ጋር ሆነው ባቀረቡት የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የጋራ ጸሎት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ንግግራቸው፣ ስደተኞች በሚያሳዩት ምስክርነት አማካይነት እግዚአብሔር የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰላም መንግሥቱን ለታናናሾች እንደሚገልጽ አስረድተው፣ ስደተኞች በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እንግዶች አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

በጋራ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች የመጡ ስደተኞች የሕይወት ታሪካቸውን እያስታወሱ ምስክርነታቸውን ያካፈሉ ሲሆን፣ በልባቸው ውስጥ የነበረውን ሕልም እውን ለማድረግ ብለው ባደረጉት የስደት እና የመከራ ጉዞ ወቅት የደረሰባቸውን የጥላቻ ቁስል ሕመም አስታውሰዋል። “ስደተኞችን ስናዳምጥ እግዚአብሔር የሚነግረን የትንቢት ቃል ኃይል በተሻለ ሁኔታ እንረዳለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “እናንተ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ እንግዶች እና መጻተኞች አይደላችሁም” በማለት ስደተኞችን አጽናንተዋል።     

ለክርስቲያኖች መስታወት

የስደተኞች የሕይወት ታሪክ እንደ መስተዋት ማንነታችንን ማወቅ እንዳለብን ያስታውሰናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በክርስቲያኖችም መካከል ጥላቻ ተፈጥሮ ሊኖር የሚገባውን መልካም ግንኙነት እንደጎዳው አስታውሰው፣ ከእርስ በእርስ ግጭት ወደ አንድነት ጎዳና መጓዝ እንዳለብን እግዚአብሔር በሕልማችን አማካይነት እንደሚነግረን አስረድተዋል። ዓለም ሲከፋፈል እንዲሁም በክርስቲያኖች መካከል መከፋፈል ሲፈጠር መደሰት እንደሌለብን እግዚአብሔር እንደሚያሳስበን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በታሪክ ውስጥ መጓዝ እንዳለብን የእግዚአብሔር እቅድ እና ፈቃድ መሆኑን ገልጸው፣ የሰው ልጅ ሕልም ከመለያየት ግንብ እና ከጠላትነት የጸዳ፣ እንግዳ መሆን በሌለበት እና ዜጎች በሙሉ እርስ በእርስ የሚዋደዱበት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። 

የወንድማማችነት አውድ መሆን

በሕዝቦቿ መካከል አሰቃቂ ክፍፍል የታየባት የቆጵሮስ ደሴት፣ በእግዚአብሔር ጸጋ አማካይነት ወንድማማችነት የሚገለጽባት እና የሚያድግባት እንደምትሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ይህ እንዲሆን ሁለት ነገሮች በተግባር መታየት አስፈላጊ እንደሆነ ቅዱስነታቸው ተናግረው፣ የመጀመሪያው ለእያንዳንዱ ሰው ክብር እውቅና መስጠት እና ሁለተኛው፣ የሁላችን አባት ለሆነው እግዚአብሔር ግልጽ ታማኝነት መግለጽ ናቸው ብለዋል። እነዚህ ሁለቱ ነገሮች ተፈጻሚነትን የሚያገኙ ከሆነ “የሕዝቦቿ ሕልም እና ምኞት ከግጭት ወደ አንደነት፣ ከጥላቻ ወደ ፍቅር በተጨባጭ እርምጃዎች ሊተረጎም ይችላል” ብለዋል። “በትዕግስት የተሞላ ጉዞ ከቀን ወደ ቀን እግዚአብሔር ወዳዘጋጀልን ምድር ይመራናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በጋራ በምንኖርባት መሬት ሰዎች አንተ ማን ነህ? ወይም አንቺ ማነሽ ብለው ቢጠይቁ፣ ‘እኔ ወንድምህ ነኝ’፣ ወይም ‘እኔ እህትን ነኝ’ ብለን የምንመልስባት ምድር ትኖረናለች” ብለዋል።  

"በዝምታ መቀመጥ አንችልም!"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጋራ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ተወካዮች እና ከልዩ ልዩ አገራት ለመጡት ስደተኞች ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፣ በስደተኞች ላይ የሚደረግ ልዩነት ያስከተለውን የዘመናችን ስቃይ ማሸነፍ እንደሚገባ ተማጽኖአቸውን አቅርበው፣ በስደተኞች ላይ በየዕለቱ የሚደርሱ ክስተቶች አሳዝኖናል ብለዋል።

"ልቤ ውስጥ ያለውን መናገር እፈልጋለሁ!" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰዎች ችግር ውስጥ ወድቀው ዕርዳታን በመፈለግ ምግብ፣ መጠለያ፣ ነፃነት እና ወንድማማችነትን ሲጠይቁ በሽቦ ወይም በድንጋይ የተዘጋ በር ወይም ድንበር የሚያጋጥማቸው መሆኑን በቁጭት ተናግረዋል። በመሆኑም ይህን የመሰለ ሁኔታ ሲያጋጥም እግዚአብሔር ሕሊናችንን እንዲያበራ በጸሎታቸው ጠይቀው፣ ግዴለሽነት በነገሠበት በዛሬው ባሕል በመታለል፣ በመከራ እና በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ከመመልከት ይልቅ ፊታችንን ወደ ሌላ አቅጣጫ ማዞር እንደማያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል።

04 December 2021, 16:46