ፈልግ

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ በቆጵሮስ እና በግሪክ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጎዞ ጀመሩ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከኅዳር 23 እስከ 27/2014 ዓ.ም ድረስ የሚያደርጉትን 35ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን ለቅዱስነታቸው በወጣው የጉዞ መርሃግብር መሰረት የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ መዳረሻ ወደ ሆንችው ቆጵሮስ ደርሰዋል። በቆጵሮስ ለሁለት ቀናት ያህል የሚያደርጉትን ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ግሪክ እንደ ሚያቀኑ የተገለጸ ሲሆን በግሪክ የዛሬ አምስት አመት ገደማ የጎበኟትን የሌስቮስ ዴሴት ከጎበኙ በኋላ በሚቀጥለው ሰኞ ኅዳር 27/2014 ዓ.ም ወደ መንበራቸው ቫቲካን እንደሚመለሱ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት ዝቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለት ሀገራት ውስጥ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲጀምሩ በመጀመሪያ ወደ ቆጵሮስ በመብረር በምስራቃዊ ሜዲትራኒያን አካባቢ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዟ ጀምረዋል።

ከሮም ከተማ ተንስተው የሦስት ሰዓት በረራ አድርገው ትላንት ኅዳር 22/2014 ዓ.ም ወደ ቆጵሮስ ያቀኑት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጉዞዋቸው ወቅት “ጉዞው የሚያምር ነው፣ እናም አንዳንድ ቁስሎችን እንነካለን፣ሁላችንም የምናገኛቸውን መልዕክቶች በሙሉ እንደምንቀበል ተስፋ አደርጋለሁ" በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 22/2014 ዓ.ም በቆጵሮስ በሚገኘው ላርናካ አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ከሰዓት ቡኋላ አመሻሹ ላይ 11 ሰዓት ገደማ የደረሱ ሲሆን በቆጵሮስ የቅድስት መንበር አባሳደር በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቲቶ ኢላና አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በመቀጠልም የቆጵሮስ ፓርላማ አፈጉባሄ ለቅዱስነታቸው የእንኳን ደህና መጡ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ሦስት የባህል ልብስ የለበሱ ሕጻናት ለቅዱስነታቸው የአበባ ጉንጉን አቅርበውላቸዋል። የክብር ዘበኛ ባንድ ሙዚቃ ካማ በኋላ የቅድስት መንበር እና የፓርላማው ፕሬዝዳንት የየራሳቸውን የልዑካን ቡድን አባላት አስተዋውቀዋል።

በቦታው ላይ የተገኙ በርካታ ህጻናት የቫቲካን እና የቆጵሮስን ባንዲራ የያዙ ሲሆን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን “እንወዶታለን” በማለት በደስታ የተቀበሏቸው ሲሆን ከመካከላቸው አንዱ "ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የሰላም ምልክት" የሚል መፈክር ይዞ ታይቷል።

በአውሮፕላን ማረፊያው ቅዱስነታቸው ምንም ዓይነት ንግግር ያላደረጉ ሲሆን ነገር ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና የቆጵሮስ ፓርላማ አፈጉባሄ ዲሜትሪዎ በተርሚናል ውስጥ በሚገኝ ክፍል ውስጥ ለጥቂት ጊዜ መነጋገራቸው ተገልጿል። በመቀጠልም ቅዱስ አባታችን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት በመኪና ከተጓዙ በኋላ በመዲናይቱ ኒቆስያ ወደ ምትገኘው የጸጋ እመቤታችን ማርያም ካቴድራል ያመሩ ሲሆን በእዚያም የቆጵሮስ ማሮናዊት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ መንበረ ፓትርያርክ፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን/ ገዳማዊያት፣ ዲያቆናት፣ ካቴኪስቶች እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበራት በተገኙበት ንግግር አድርገው ነበር።

ምስራቅ ሜዲትራኒያን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ አቆጣጠር በ2010 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ወደ ቆጵሮስ ካደረጉት ጉብኝት በመቀጠል ለሁለተኛ ጊዜ በአንድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተደረገ ሐዋርያዊ ጉብኝት ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ ሜዲትራኒያን ደሴት ያደረጉት ጉዞ መሪ ቃል “በእምነት እርስ በርሳችን መጽናናት” የሚል ሲሆን ይህም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ጢሞቴዎስ ከጻፈው የመጀመሪያ መልእክት የተወሰደ ነው። የሐዋርያት ሥራ የቅዱስ በርናባስ ስም “የመጽናናት ልጅ” ማለት እንደሆነ ያስረዳል።

የቆጵሮስ ሕዝብ ብዛት 850,000 ሲሆን ከእነዚህ መካከል 80 በመቶው ክርስቲያኖች ሲሆኑ ካቶሊኮች 38,000 ናቸው፣ ይህም በመቶኛ ሲሰላ 4.47 ከመቶ ያህሉ የካቶሊክ እምነት የሚከተሉ ናቸው። የሙስሊም ሐይማኖት የሚከተሉት ደግሞ 2 በመቶውን ይይዛሉ። አብዛኞቹ የቆጵሮስ ሰዎች ራሳቸውን የግሪክ ኦርቶዶክስ ሐይማኖት ተከታይ አድርገው ራቸውን ይቆጥራሉ። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ስር መሰረቶቻቸውን የያዙት በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢየሩሳሌም ከወደቀች በኋላ በሰፈሩት የመስቀል ጦረኞች ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በቆጵሮስ ደሴት መገኘቱ የሚታወቅ ሲሆን በእዚያ የነበረው የደሴቱን ሮማዊ ገዥ ሰርግዮስ የክርስትና እምነት እንዲቀበል ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳደርገው ከታሪክ ለመረዳት ይችላል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “በታሪክ፣ በባህል እና በወንጌል ወደ ተባረከችው ድንቅ አገራችሁ ለመምጣት በዝግጅት ላይ ነኝ” ሲሉ ከዚህ ቀደም ይህንን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው በፊት ተናግረው እንደ ነበረ የሚታወቅ ሲሆን እ.አ.አ በኅዳር 27/2014 ዓ.ም ባስተላለፉት መልእክት “በደስታ ወደ እናንተ እየመጣሁኝ ነው፣ በትክክል በወንጌል ስም የእነዚያ አገሮች የመጀመሪያዎቹ ታላላቅ ሚስዮናውያን፣ በተለይም የሐዋርያው ​​ጳውሎስ እና የበርናባስ ፈለግ እንድተከተሉ እፈልጋለሁ። ወደ መነሻችው መመለስ ጥሩ ነው እናም ቤተክርስቲያን የወንጌልን ደስታ እንደገና ማግኘቷ አስፈላጊ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።

የሁለቱ ሀገራት ጉብኝት የውዕደት ቃና አለው። በቁጥር አንስተኛ የሆኑ የካቶሊክ ማህበረሰቦችን እምነት ከማጠናከር ባሻገር የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የአካባቢ መሪዎችን "በሐዋርያዊ ወንድማማችነት" እንደሚገናኙ ቅዱስነታቸው መናገራቸው ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ቆጵሮስን “በአህጉሪቱ የቅድስት ምድር ምሽግ” በማለት የገለጿት ሲሆን ግሪክን ደግሞ “የጥንታዊ ባህል መገኛ” በማለት ገልጸዋታል፣ ጉብኝቴ ከአውሮፓ ጥንታዊ የውኃ ጉድጓዶች ለመጠጣት አጋጣሚውን ይፈጥርልኛል ብለዋል። አውሮፓ የቅዱስ ወንጌልን መስፋፋት እና ታላላቅ ስልጣኔዎችን እድገት ያሳየውን የሜዲትራኒያን ባህር አከባቢዎች ችላ ልትል አትችልም በማለት አክለው መግለጻቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ዛሬ የሜዲትራኒያን ባህር አከባቢ ታላቅ የቀብር ስፍራ ሆኗል ሲሉ በቁጭት የተናገሩት ቅዱስነታቸው ከጦርነትና ከድህነት ሲሸሹ ስደተኞችና ፍልሰተኞች በማዕበሉ ተውጠዋል ያሉ ሲሆን “እንደ አንድ መንፈሳዊ ተጓዥ በመሆን በሰብዓዊነት በግሪክ ሌስቦስ ደሴት ውስጥ የሚገኙትን ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንደገና እጎበኛለሁ” ብለዋል ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከኅዳር 23 እስከ 25/2014 ዓ.ም ድረስ በቆጵሮስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚቀጥሉ ሲሆን በዚህ መሰረት ትላንት ኅዳር 23/1014 ዓ.ም ማምሻው ላይ 12 ሰዓት አከባቢ ከካህናት፣ ከገዳማዊያን/ገዳማዊያት፣ ዲያቆናት፣ ካቴኪስቶች፣ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራት እና የቆጵሮስ መንፈሳዊ ንቅናቄዎች አባልት ጋር በኒቆሲያ በሚገኘው የጸጋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ በተገናኙበት ወቅት ቅዱስነታቸው ንግግር ማደረጋቸው ይታወሳል።

በመቀጠልም በተመሳሳይ ቀን ከምሽቱ 1፡30 አከባቢ በኒኮሲያ በሚገኘው የፕሬዝዳንት ቤተ መንግሥት የእንኳን ደህና መጡ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል። በወቅቱ በኒኮሲያ በሚገኘው የፕሬዝዳንት ቤተ መንግስት የግል ቢሮ ውስጥ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንትን በትህትና መጎብኘታቸው ተገልጿል። ከምሽቱ 2:00 በኒኮሲያ በሚገኘው የፕሬዝዳንት ቤተ መንግስት "የሥነ ሥርዓት አዳራሽ" ውስጥ ከባለሥልጣናት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ እና ከዲፕሎማቲክ አካላት ጋር ተገናኝተው ቅዱስነታቸው ንግግር ማደረጋቸው ተገልጿል።

አርብ ሕዳር 24/2014 ዓ.ም

አርብ እለት ኅዳር 24/2014 ዓ.ም ደግሞ ከጥዋቱ 4፡30 ገደማ በኒቆስያ በሚገኘው የቆጵሮስ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ብፁዕ አቡነ ክሪሶስቶሞስ 2ኛ ጋር ተገናኝተዋል።

እኩለ ቀን አከባቢ ከቀኑ 5፡00 ላይ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በኒቆስያ ኦርቶዶክስ ካቴድራል ውስጥ ተገናኝተዋል። ከዚያም በኋላ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ በኒኮስያ መስዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል።

አመሻሹ ላይ ወደ 12፡00 ሰዓት ገደማ ላይ ደግሞ በኒቆሲያ በሚገኘው የቅዱስ መስቀል ደብር ቤተክርስቲያን ከስደተኞች ጋር በጋራ ጸሎት ያደርጋሉ።                        

ቅዳሜ ኅዳር 25/2014 ዓ.ም ኒኮሲያ - ላርናካ - አቴንስ

ከቀኑ 5:10 በላርናካ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመሰናበቻ ሥነ ሥርዓት የሚካሄድ ሲሆን ከእዚያ በመቀጠል ከቀኑ 05:30 ወደ አቴንስ ጉዞ ይጀምራሉ።

02 December 2021, 16:34