በአውሮፓ ውስጥ የሚታይ የስደት ቀውስ በአውሮፓ ውስጥ የሚታይ የስደት ቀውስ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጉዳት ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን መርዳት እንደሚያስፈልግ አስሰቡ

በቆጵሮስ እና በግሪክ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ያካሄዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከኅዳር 25-27/2014 ዓ. ም በግሪክ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ሌስቦስ የተባለች የግሪክ ደሴትም መጎብኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በግሪክ ባደረጉት ቆይታ በሌስቦስ ደሴት የሚገኙ በርካታ ስደተኞችንም ጎብኝተዋል። በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅዱስነታቸው ከስደተኞች ጋር የኅብረት ጸሎት አቅርበው ከስደተኞች የቀረቡ ምስክርነቶችንም አድምጠዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ጉዳት ደርሶባቸው ችግር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ስደተኞችን መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግሪክ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ተጠቃሽ በሆነው በሌስቦስ ከሚገኙ የልዩ ልዩ አገራት ስደተኞች ጋር ሆነው፣ በየእሑዱ የሚያቀርቡትን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ያቀረቡ ሲሆን የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መካፈላቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግሪክ ውስጥ በርካታ ስደተኞች የሚገኙበትን የሌስቦስ ደሴት ሲጎበኙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ በፊት እ. አ. አ በ2016 ዓ. ም. ከብጹዕ ወቅዱስ ፓርትሪያርክ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ከአቴንስ ከተማ እና ከመላው ግሪክ ሊቀ ጳጳስ ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ኢሮኒሞስ ጋር ሆነወ መጎብኘታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዚያን ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሌስቦስ የሚገኙ ስደተኞች፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሰው ልጅ ላይ የደረሰው አሰቃቁ መከራ ዋና ተዋናይ መሆናቸውን ገልጸው፣ በመከራ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰደተኞች ዘወትር ተስፋን የሚያደርጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እ. አ. አ በ 2016 የነበረው ሁኔታ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ 2016 በሌስቦስ የስደተኞች መጠለያ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት፣ ሄላስ የተባለ ካቶሊካዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ወ/ሮ ሐና ማርያ ስቴላ ወቅቱ እጅግ በጣም አስቸጋሪ፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች ከቱርክ ተነስተው ወደ ግሪክ የገቡበት ዓመት እንደነበር አስታውሰዋል። ግሪክ ባጋጠማት ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ አቅም ያልነበራት ትንሽ አገር መሆኗን አስታውሰዋል።

ሌስቦስ ምልክት ይሆናል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ 2016 በደሴቲቱ የተጠለሉ ስደተኞችን በጎበኟቸው ወቅት ለዓለም አቀፉ ማበረሰብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተስፋ ቆርጠው በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ትኩረት በመስጠት ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ በማለት ማሳሰባቸው ይታወሳል። በግሪክ የሌስቦስ ስደተኞች መጠለያ እ. አ. አ በ2020 በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ የወደመ ሲሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ሥፍራውን መጎብኘታቸው ታውቋል። ከአምስት ዓመት በፊት በመጠለያው የነበሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከ25,000 ወደ 3,000 ዝቅ ማለቱ የገለጹት ወ/ሮ ሐና ማርያ ስቴላ፣ የግሪክ መንግሥት በደሴቲቱ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ቁጥር በመገደብ ከፍተኛ ቁጥጥር ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ ድርጅታቸው ያልተቀበለው መሆኑን ገልጸው፣ ስደተኞችን ሙሉ በሙሉ ከማኅበራዊ አውድ ማግለል ሰብዓዊ ክብራቸውን የሚቀንስ መሆኑን አስረድተው፣ ስደተኞች በአገሪቱ ውስጥ የሚያደርጉት ነፃ እንቅስቃሴ በአገሪቱ ደህንነት ላይ ችግር ማስከተሉ ቢታመንበትም ቁጥጥሩ በሌሎች መንገዶችም ቢከናወን መልካም እንደሚሆን አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለስደተኞች ያደረጉት እርዳታ

እ. አ. አ ከ2015 ጀምሮ ስደተኞች ወደ ግሪክ ድንበር ከደረሱ በኋላ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚጠቀሙባቸው የግሪክ ኤጄዎ ደሴቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ደሴቶች አንዷ በሆነች በሌስቦስ ደሴት ሄላስ የተሰኘ ካቶሊካዊ በጎ አድራጎት ድርጅት የተለያዩ እቅዶችን በመወጠን ወደ ደሴቶቹ የሚመጡ ስደተኛ ሴቶችን፣ ልጃ ገረዶችን እና ወንዶችን የሚያሳትፉ ፕሮግራሞችን በመዘርጋት ከዕርዳታ አቅርቦት ሥራ በተጨማሪ የሥነ-ልቦና አገልግሎት በማቅረብ ላይ መሆኑ ታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጤና ላይ ባስከተለው ስጋት ምክንያት በስደተኞች መጠለያ የሚሰጡ ድጋፎች መጠናከራቸውን የገለጹት ወ/ሮ ሐና ማርያ ስቴላ፣ ባሁኑ ጊዜ ከሌስቦስ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በተጨማሪ ዋና ከተማ አቴንስን ጨምሮ በሳሞስ እና ኪዮስ ደሴቶችም ድርጅታቸው እርዳታን በማቅረብ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በግሪክ ከሚገኝ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅት በተጨማሪ በአውሮፓ አገራት ውስጥ የጣሊያን እና የጀርመን ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅቶችም በደሴቶቹ ለሚገኙ ስደተኞች እርዳታቸውን እንደሚያቀርብ የገለጹት ወ/ሮ ሐና ማርያ ስቴላ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2019፣ በቫቲካን የር. ሊ. ጳ በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራዬቭስኪ በኩል የ100,000 ዩሮ ዕርዳታ ማድረጋቸውን ወ/ሮ ሐና ማርያ ስቴላ አስታውሰው፣ ግሪክ ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ጋር የምትዋሰን አገር በመሆኗ ሁሉም አገራት ለስደተኞች በሚደረግ የእንክብካቤ አገልግሎት እንዲሳተፉ፣ ስደተኞች ወደ አገራቱ ሲደርሱ ሰብአዊ ክብርን በመስጠት መልካም አቀባበል እንዲያደርጉላቸው አሳስበው፣ ለስደተኞች ውጤታማ አገልግሎትን ማቅረብ እንዲቻል በኅብረት ጠንክሮ መሥራት እና ግሪክ ለሰደተኞች የመጨረሻ ግባቸው መሆን የለባት በማለት አሳስበዋል።

06 December 2021, 17:39