ፈልግ

ቅድስት ድንግል ማርያም የመላዕክት ንግሥት ባዚሊካ - አሲሲ ቅድስት ድንግል ማርያም የመላዕክት ንግሥት ባዚሊካ - አሲሲ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለጸሎት ወደ አሲሲ እንደሚጓዙ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. ወደ መካከለኛው ጣሊያን ከተማ አሲሲ የግል ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታወቋል። ቅዱስነታቸው በአሲዚ የሚያደርጉት ጉብኝት ዋና ዓላማ ከመላው አውሮፓ ከሚሰበሰቡ ወደ 500 ከሚጠጉ ድሃ ማኅበረሰብ ጋር ለመገናኘት፣ ምስክነታቸውን ለማዳመጥ እና አብረው የጋራ ጸሎት ለማቅረብ መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል። ቅዱስ ፍራንችስኮስ በኖረባት አሲዚ ከተማ የሚያደርጉትን የአንድ ቀን ጉብኝታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀንን ለማስታወስ በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ እሑድ ኅዳር 5/2014 ዓ. ም. የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አክሎ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ የቅዱስነታቸውን ጉብኝት መርሃ ግብር ጠቅሶ እንዳስታወቀው፣ ከልዩ ልዩ የአውሮፓ አገራት የሚመጡ ወደ 500 የሚጠጉ ድሃ ማኅበረሰብ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወደ ኖረባት አሲሲ ከተማ የመጡት መንፈሳዊ ጉዞን በማድረግ መሆኑን የሚገልጽ ስጦታ ለቅዱስነታቸው እንደሚያቀርቡ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ስብከት ለማዳመጥ መሆኑን አስረድቷል። በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ምስክርነታቸውን የሚያቀርቡት ሰዎች ስድስት ሲሆኑ፣ ሁለት ከፈረንሳይ፣ አንድ ከፖላንድ፣ አንድ ከስፔን እና ሁለት ከጣሊያን መሆናቸው ታውቋል። የእነዚህ ሰዎች ምስክርነት ካዳመጡ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሥፍራው ለተገኙት በሙሉ ስብከታቸውን እንደሚያቀርቡ እና ለጋዲያኑ ያመጡት ስጦታ የሚታደል መሆኑ ታውቋል።

"ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው" 

በቅድስት መንበር የአዲስ ስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ ዘንድሮ ኅዳር 5/2014 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከድሆች ጋር የሚገናኙባቸው በርካታ ዝግጅቶች መኖራቸውን አስታውቆ፣ አጋጣሚው ምዕመናን ከቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር፣ በተለያዩ ምክንያቶች በድህነት ለወደቀው ማኅበረሰብ የዕርድታ እጃቸውን የሚዘረጉበት መሆኑ ታውቋል። ዘንድሮ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን እንዲሆን የተመረጠው መሪ ቃል፣ ከማር. 14፡7 ላይ የተወሰደ እና "ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው" የሚል መሆኑ ታውቋል። በአሲሲ ከተማ በተዘጋጀው እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚገኙበት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተለያዩ ካቶሊካዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ምጽዋት ሰብሳቢ ክፍል የር. ሊ. ጳ. በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እና የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ እንደሚገኙ ታውቋል። ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. በአሲሲ ከተማ የሚቀርብ መንፈሳዊ ዝግጅት በቫቲካን ሚዲያ በቀጥታ የሚተላለፍ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ ብሔራዊ እና ዓለማ አቀፍ ሚዲያዎች በኩል እንደሚተላለፍ ታውቋል።

ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአሲሲ ከተማ ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. ከሚያካሄዱት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በኋላ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀንን ምክንያት በማድረግ እሑድ ኅዳር 5/2014 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል። የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎቱን ሁለት ሺህ ያህል ምዕመናን እንደሚካፈሉት ይጠበቃል።

በዕለቱ የሚከናወኑ ተግባራት

ዘንድሮ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ በሮም ከተማ የተለያዩ የአገልግሎት ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን ከእነዚም መካከል በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ በድህነት ሕይወት ለሚገኙ አርባ ቤተሰቦች የምግብ እና የሕክምና ዕርዳታ የሚደረግላቸው ሲሆን፣ በየዓመቱ የሚቀርብ የነጻ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እንደሚዘጋጅ ታውቋል። ወደ ማዕከሉ መጥተው የሕክምና ዕርዳታ የሚደርግላቸው ቤተሰቦች፣ በገንዘብ አቅም ማነስ በበሽታ የሚሰቃዩ የሮም ከተማ ድሃ ቤተሰቦች እንደሚሆኑ ተገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አንዳንድ አገሮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እጅግ መጎዳታቸውን፣ ስቃዩ የበረታባቸው የሕክምና አገልግሎት ማግኘት የማይችሉ ድሃ ቤተሰቦች መሆናቸውን አስታውሰው፣ ሌላው ቀርቶ በቤታቸው የሚበላ ነገር በማጣት የዕርዳታ ምግብ ለማግኘት ተሰልፈው የሚውሉ ሰዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር አያያዝው፣ ዘንድሮ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ሰብከቶች አቅማቸውን አስተባብረው የሚችሉትን ዕርዳታ ለድሆች እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።

09 November 2021, 16:15