ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የስደተኞች ታሪክ የሕይወት ትምህርት ሊሆነን ይገባል አሉ!

በላቲን ቋንቋ “Scholas Ocurrentes” (ስኮላስ ኦኩረንቴስ) በመባል የሚታወቀው ድርጅት በዓለም ላይ ያሉ ሁሉንም የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ትስስር ለማስተዋወቅ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተደገፈ እና በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር የሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች የሚተሳሰሩበት መረብ ነው። ይህ የትስስር መረብ የትምህርት ማዕከላት ያላቸውን ፕሮጀክቶች የሚያስተሳስር ድርጅት ሲሆን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር የሚተዳደሩ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እርስ በእርሳቸው በማስተሳሰር እና ለመደገፍ በመሞከር፣ በተለይም አንስተኛ የሆነ ግብዓቶች ያላቸውን እና በኢኮኖም አቅም ማነስ እየታተሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን የሚደግፍ አለም አቀፍ የካቶሊክ ትስስር ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 16/2014 ዓ.ም ከScholas Occurrentes ከተሰኘው አለም አቀፍ የትምህርት ቤቶች ትስስር አባላት ወጣቶች ጋር መገናኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ እንደ ተናገሩት ስደተኞች በጉዞአቸው የሚያጋጥሟቸውን ጨካኝ እውነታዎች በማጉላት ወጣቶቹ በጣም የተቸገሩትን ሁሉ ለማገዝ እና ማህበረሰብ የመገንባት ባህል እንዲፈጥሩ አበረታተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐሙስ አመሻሽ ላይ በቫቲካን የScholas Occurentes አለማቀፋዊ ትስስር ድርጅት አባላት ወጣቶችን ባነጋገሩበት ወቅት ለእርሳቸው የቀረቡላቸውን ሁለት ጥያቄዎችን ከመመለሳቸው በፊት አንዳንድ ምስክርነቶችን በጥሞና አድምጠዋል።

Scholas Occurentes በመባል የሚታወቀው ድርጅት በ190 አገሮች ውስጥ የሚሰራ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሕግ ጥላ ሥር የሚተዳደር ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው። ከ 400,000 በላይ የትምህርት ማዕከላትን በማዋሃድ እና በዓለም ዙሪያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህጻናትን እና ወጣቶችን ያካተተ ድርጅ ነው። ይህ ድርጅት ከ20 አመታት በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ የአርጀንቲና የቦነስ አይረስ ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት፣ ተልእኮው የመገናኘትን ባህል ለመፍጠር እና አካታች የትምህርት ሞዴልን ለማስተዋወቅ የተቋቋመ ድርጅት ነው።

ማህበረሰቦች ላይ

በስብሰባው ወቅት በአካል መገኘት ያልቻለችን አንድ ሴት በመወከል በአወያዩ የቀረበ የመጀመሪያው ጥያቄ አንድ ማህበረሰብ "ክፍት" ወይም አካታች እንዴት መሆን ይችላል? የሚለው ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለዚህ ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት አንድ ማህበረሰብ በእያንዳንዱ ሰው የመሳተፍ አቅም አካታች እና ክፍት ሊሆን ይችላል በማለት መልሰዋል። “ይህንን የመሳተፍ አቅም ስናጣ ቅሪተ አካል እንሆናለን” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ። “ነፍስ ቅሪተ አካል ትሆናለች፣ ልብም ቅሪተ አካል ይሆናል፣ እናም በማህበራዊ ደረጃ አስተያየት ትክክል በሆነው ነገር ውስጥ እንወድቃለን፣ እነሱም ወይ ድርቀትን ወይም ጨካኝ ምልክቶችን እንድናሳይ በማድርግ ከሥር መሰረታችን ጋር ያለያየናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ ስሜቶች ሲጠፉ "ውስጣዊ ስሜቶች ይጠፋሉ" ሁሉም ሰው የሚያደርገውን እናደርጋለን፣ እናም ስብዕናችንን እናጣለን ያሉ ሲሆን እውነተኛ ሰዎች መሆን ይኖርብናል ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ደምድመዋል።

በስደተኞች ላይ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመቀጠል በሩዋንዳ የሚኖረውን የአንድ ወጣት ታሪክ ያዳመጡ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም በሩዋንዳ በተከሰተው የዘር ጭፍጨፋ በመሸሽ ቤተስቦቹ ወደ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ተሰደው እንደ ሄዱ እርሱ ግን የትምህርት እድል አግኝቶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዞ በዚያ የሕግ ትምህርት አጥንቶ መመረቁን ገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዚህ ምስክርነት በሰጡት ምላሽ እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ በአገራቸው ውስጥ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የሚሸሹ ስደተኞችን ለመርዳት ምን ሊደረግ ይችላል ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ስደተኞች የራሳቸው የሆነውን ቦታ ትተህ በመሄድ ወደ ሌላ የእነርሱ ወዳልሆነ አገር መሄዳቸው በራሱ አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

"ወላጆችህ ይህን አሰቃቂ ነገር ኖረዋል" በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በነጻነት ለመኖር ባለማቻልህ የተነሳ ከዚያ አሰቃቂ ሁኔታ አምልጠህ ለመሸሽ ተገደሃል ብለዋል። "የሚሰደዱ ስደተኞች በልባቸው ውስጥ ያለው አንድ ነገር ብቻ ነው፣ ይህ ነገር ደግሞ መሄድ" የሚለው እንደ ሆነ የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የስደተኛ ህይወት ከባድ ነው ብለዋል። በሊቢያ የባህር ጠረፍ እየሆነ ያለውን ነገር እየተከታተልኩ ነው በማለት የገለጹት ቅዱስነታቸው እነዚህ ሰዎች ይወሰዳሉ፣ ይሰቃያሉ፣ ሴቶች ይሸጣሉ" እነዚህን ነገሮች መገመት ትችላለህ?" ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "ብዙ ሰዎች እየተሸጡ ይገኛሉ፣ ያ ዛሬ እየሆነ ነው!" በማለት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል ስደተኛ መሆን ማለት በመንገድ ላይ መኖር ማለት ነው ያሉ ሲሆን "ነገር ግን በጎዳናህ ላይ መጓዝ ብቻ ማለት ሳይሆን በከተማ ጎዳናዎች ላይ መጓዝን ብቻ የሚያመለክት ሳይሆን በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዝ ማለት ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ምላሻቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ፍላጎታቸው በእነዚህ ጨካኝ እውነታዎች ውስጥ ተዘፍቀው የሚኖሩ ወጣቶች “ስቃይ” ማጉላት ሳይሆን ስለ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንዲያስቡ መርዳት መሆኑን አሳስበዋል። በቦታው የተገኙት ወጣቶች ከእግዚአብሔር ለተቀበሉት ነገር እንዲያመሰግኑ እና የእነዚህ ስደተኞች ታሪክ ምን እንደሚያስተምራቸው እራሳቸውን እንዲጠይቁ ጥሪ አቅረበዋል።

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወጣቶቹን "በኋላ እንድትገነዘቡት የምፈልገው ነገር ስሜቶቻችሁ እንዲያድጉ ትፈቅዳላችሁ ወይንስ ትሸፍናላችሁ?" በማለት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ስሜትህን ከሸፋፈንክ ይፈነዳል፤ ነገር ግን ስሜትህ እንዲወጣ ከፈቀድክ እነሱን ለይተህ የመጋፈጥ ግዴታ እንዲኖርህ ያደርግሃል  ያ “ብስለት ይሰጥሃል” ካሉ ቡኋላ ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

25 November 2021, 16:00