ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መልካም የሚሠሩት ዘላለማዊ በሆነ ነገር ላይ መዋለ ንዋያቸውን ያፈሳሉ አሉ!

በኅዳር 05/2014 ዓ.ም ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ በምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የአለም የድሆች ቀን ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህንን ቀን ምክንያት በማድረግ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በእለቱ ለተገኙ ምዕመናን በእለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ (ማርቆስ 13፡24-32) ተንተርሰው ባደረጉት አስተንትኖ የቁሳቁስ ነገሮች ጊዜያዊ ተፈጥሮ እና አካላዊ ገጽታ በማንፀባረቅ ምእመናን ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዲመሰርቱ ጋብዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዕለቱን የወንጌል ክፍል በመጥቀስ (ማርቆስ 13፡24-32) ኢየሱስ ከቃሉ በቀር ሁሉም ነገር ያልፋል እንዳለ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እናም ምእመናን በምድር ላይ መንግሥተ ሰማያትን እንዲገነቡ ጋብዘው “መልካም ነገር ስለማይጠፋ ለዘላለም ይኖራል” ማለታቸው ተዘግቧል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በእሁድ ኅዳር 05/2014 ዓ.ም የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉ በኋላ ባደርጉት አስተንትኖ ኢየሱስ “በዚያን ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ” ያለውን የማርቆስ ወንጌል አስታውሰዋል።

ነገር ግን፣ ጌታ አጥፊ አይደለም፣ አላማው ይዋል ይደር እንጂ ከእግዚአብሔር ፍቅር እና ከቅዱስ ወንጌል ማዳን መልእክት በቀር ሁሉም ነገር እንደሚያልፉ እንድንረዳ አስቦ የተናገረው ነው እንጂ እኛን ለማስፈራራት አስቦ የተናገረው እንዳልሆነ ቅዱስነታቸው አክለው ገልጸዋል።

በህይወት ውስጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች መመሪያ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ጠቃሚ መልእክት በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊ በሆኑ ውሳኔዎች ውስጥ ይመራናል፣ ያሉ ሲሆን ፈጣን በሆነ መልኩ እርካታን ለሚሰጡን ነገሮች ብዙ ዋጋ እንዳንሰጥ እና በሚያልፉ ነገሮች ላይ እንዳንጣበቅ ያሳሰቡ ሲሆን "እንደ ገንዘብ፣ መልክ፣ አካላዊ ደህንነት" ከእነዚህ አሁናዊ እና ጊዜያዊ ከሆኑ ነገሮች ባሻገር መሄድ አስፈላጊ ነው ያሉ ሲሆን በትዕግሥት እና መልካም በማድረግ ሕይወታችንን መገንባት ይኖርብናል ብለዋል።

ኢየሱስ ለእኛ ሁላችን የሚያቀርብልን ግብዣ ሕይወታችንን በአሸዋ ላይ እንድንገነባ አይደለም “ኢየሱስ እንዳለው ታማኝ ደቀ መዝሙር ህይወቱን በዓለት ላይ ያጸና ነው፣ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው” ማለቱን አስታውሰዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክት በመጥቀስ  “ፍቅር መቼም ቢሆን ማለቅያ የለውም” ያሉ ሲሆን “በጎ የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ ዘለዓለማዊ በሆኑ ነገሮች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ” በማለት አስታውሰውናል።

ሰማይን በምድር ላይ መገንባት

“ለጋስ የሆነ፣ የዋህ፣ ታጋሽ፣ የማይቀና፣ የማይከራከር፣ የማይመካ፣ የማይታበይ፣ ሰው አክባሪ የሆነ ሰው ስናይ፣ (ቆሮ 13፡4-7) እንደነዚህ አይነት ሰዎች መንግሥተ ሰማያትን በምድር ላይ የሚሠሩ ሰዎች ናቸው በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎች አይስተዋሉም ወይም ሙያ ላይኖራቸው ይችላል፣ ነገር ግን በዚህ መልክ እያከናወኑ የሚገኙት ነገር አይጠፋም ምክንያቱም ጥሩ ነገር አይጠፋም፣ ለዘላለም ይኖራል" ማለታቸው ተገልጿል።

ስለዚህም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል እንደተናገሩት ሕይወትን በቃሉ ላይ መመሥረት “ከታሪክ ክስተቶች ማምለጥ ማለት ሳይሆን፣ ወደ ምድራዊ እውነታዎች ውስጥ መግባት ጠንካራ ለመሆን፣ በፍቅር ለመለወጥ፣ የዘላለምን ምልክት በእነሱ ላይ በማተም የእግዚአብሔር ምልክት" እንዲሆኑ ማደረግ ነው ብለዋል።

ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት አማኞችን በመጋበዝ ጠቃሚ ምርጫዎችን እንዲያደርጉ በመጋበዝ አስተንትኖዋቸውን የደመደሙት ቅዱስነታቸው “ከመወሰናችን በፊት፣ በኢየሱስ ፊት እንደ ህይወታችን ፍጻሜ፣ ፍቅር በሆነው በእርሱ ፊት እንደምንቆም እናስብ። እኛ እዚያ፣ በእሱ መገኘት፣ በዘለአለም ሕይወት በር ላይ እንዴት እንደ ምንገኝ ዛሬ ውሳኔ እንወስናለን። በጣም ቀላሉ እና በጣም ፈጣን ላይሆን ይችላል ፣ ግን ትክክለኛው ነገር ይሆናል ብለዋል።

ክርስቶስ በድሆች ውስጥ አለ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መልአከ እግዚአብሔር ማርያን ያበሰረበትን ጸሎት ከደገሙ በኋላ ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት “ዛሬ አምስተኛውን የዓለም የድሆች ቀን እናከብራለን” በማለት ተናግረዋል።

“የምሕረት ኢዮቤልዩ ፍሬ ሆኖ” የተቋቋመ ቀን እንደ ሆነ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው "ክርስቶስ በድሆች ውስጥ አለ" በማለት በቅርብ ቀናት በግላስጎው በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ COP26 ላይ "የድሆች ጩኸት፣ ከምድራችን ጩኸት ጋር አንድ ሆኗል" በማለት ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት "የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ደፋር እና አርቆ አስተዋይ እንዲሆኑ አበረታታለሁ" ያሉ ሲሆን ዛሬ በዓለም የድሆች ቀን “Laudato sì “ (ውዳሴ ለአንተ ይሁን) የተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክት የድርጊት መርሃግብር ዋና ሐሳብ የተቀናጀ ሥነ-ምህዳርን የሚያበረታታ ምዝገባዎች መከፈታቸውን አጉልተዋል ብለዋል።

የዓለም የስኳር በሽታ ቀን

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ላይ እንደ ገለጹት እ.አ.አ በየዓመቱ ህዳር 14 የሚከበረውን "የዓለም የስኳር ህመም ቀን" እየተከበረ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

ወጣቶችን እና ሕፃናትን ጨምሮ ብዙ ሰዎችን የሚያጠቃ ሥር የሰደደ በሽታ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ለሁሉም እና ችግሮቻቸውን በየቀኑ ለሚካፈሉት እንዲሁም ለሚረዱ የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች እጸልያለሁ” ማለታቸው ተገልጿል።

14 November 2021, 12:49

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >