ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በዓል በአሲሲ ከተማ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በዓል በአሲሲ ከተማ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “የድሆች ጥያቄ እና ክብር ሊመለስላቸው ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሑድ ኅዳር 5/2014 ዓ. ም. የሚከበረውን አምስተኛውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ ከልዩ ልዩ የአውሮፓ አገራት ከመጡ ድሃ ማኅበረሰብ ጋር በአሲሲ ከተማ ጸሎት አድረገው ተመልሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ልባችንን ክፍተን እርስ በእርስ እንድንረዳዳ፣ ድክመታችንን በማስወገድ በሕይወታችን በርትተን ድህነትን በማጥፋት ዓለማችንን የተሻለች መኖሪያ ልናደርጋት ይገባል ብለዋል። በአሲሲ ከተማ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመላዕክት ንግሥት ካቴድራል ውስጥ በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከጣሊያን፣ ከፈረንሳይ፣ ከፖላንድ እና ከስፔን ከመጡ ስድስት ድሆች የቀረበውን የምስክርነት ቃል አዳምጠዋል።

አንዱ ለሌላው ያለው አስፈላጊነት

ቅዱስነታቸው በንግግራቸው “እያንዳንዳችን አንዱ ለሌላው እናስፈልጋለን” ብለው “አቅመ ደካሞች እንኳን ብንሆን አብረን ከተጋገዝን ዓለምን የተሻለች እንድትሆን የሚያደርግ ጥንካሬ ሊኖረን ይችላል” ብለዋል። በዓለማችን ውስጥ ድህነት አስነዋሪ ሆኖ የሚታይ ቢሆንም፣ ዘወትር በምናደርገው ሥራችን፣ በኤኮኖሚ ፍትሃዊነት እና ራስን ብቻ ለማሳደግ ብለን በምናደርጋቸው ኤኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ሕሊናችንን መመርመር ያስፈልጋል ብለዋል።

የድሆችን መብት መልሶ መገንባት

“ድሆች ድምፃቸው የሚሰማበት ጊዜ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ዓይኖቻችንን ከፍተን ብዙ ቤተሰቦች የሚኖሩበትን የድህነት ሁኔታ በማየት የሥራ እድሎችን በመፍጠር ሰብዓኢ ክብራቸው እንዲመለስ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ወደ ባርነት ሕይወት ወርደው፣ በባሕር ውስጥ ተጥለው እና የጥቃት ሰለባዎች ሆነው ማየት የሚያሳፍር ነው” ብለዋል። “ዛሬ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት የሚያበቃበት፣ የሚከበሩበት ጊዜ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ግዴለሽነት ተወግዶ እርስ በእርስ የመገናኘት እና የመወያየት ጥቅምን እንደገና ማወቅ ይገባል ብለው፣ እኛ ሰዎች ተገናኝተን መወያየትን እስካልተማርን ድረስ የሰው ልጅ መጨረሻው እጅግ አሳዛኝ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።

የድሆች ተስፋ እና ፅናት

ማንኛውም ዓይነት ተቃውሞ ቢያጋጣምም የድሆች ተስፋ በከንቱ አለመጥፋቱን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ድሆችን ዛሬ መገለል፣ ስቃይ፣ ሕመም፣ ብቸኝነት እና ለኑሮ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች እጥረት ቢያጋጥማቸውም ዓይኖቻቸው በምስጋና እንዲሞሉ የሚያስችሉ ትንንሽ ነገሮችን ከማየት አላገዳቸውም ብለዋል። ምንም እንኳን እንቅፋትን በማስወገድ በርትቶ መራመድ ፍሬን እንደሚሰጥ በመገንዘብ፣ አዲስ ጉዞን መጀመር ድፍረትን ይጠይቃል ብለዋል። “ችግሮች የጋራ በመሆናቸው ማሸነፍ የምንችለው አንድ ላይ ስንሆን ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህ ካልሆነ ግን በብቸኝነት ወይም በሀዘን ፈተና ውስጥ እንወድቃለን ብለዋል። የቅዱስ ፍራንችስኮስን ልብ እና ሕይወት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው የቅዱስ ፍራንችስኮስ ልብ እና ሕይወት ከምንም የሚበልጥ ምስክርነት ነው ብለዋል።

የእግዚአብሔርን ቤት መጠገን

ኢየሱስ ክርስቶስ “ቤቴን ጥግን” ብሎ ቅዱስ ፍራንችስኮስን ሲያሳስብ ያችን በድንጋይ የተሠራች ትንሿን ጸሎት ቤት ሳይሆን፣ ጸሎት ቤቷን የሰሯትን፣ የቤተክርስቲያን ሕያዋን ድንጋዮች የሆኑትን ወንዶችን እና ሴቶችን እንዲያንጽ እና እንዲያበረታታ መጠየቁን አስታውሰው፣ ከአውሮፓ አገራት መጥተው በባዚሊካው ውስጥ የተሰበሰቡት ድሃ ማኅበረሰብ፣ ዕርዳታን ለመጠየቅ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የተሰበሰቡ መሆናቸውን አስረድተዋል

እንግዳ ተቀባይነት እና ወንድማማችነት

በካቴድራሉ ውስጥ የምትገኝ ጸሎት ቤት የምታስተላልፈው ሁለተኛው መልዕክት፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ቅድስት ኪያራን የተቀበላት ሥፍራ እንደነበረች ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ በዚህች ጸሎት ቤት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ወንድሞችን እና እህቶችን የተቀበለባት፣ ያለውን ሁሉን ነገር ከብዙ ድሆች ጋር የተካፈሉባት ቤት መሆኗን አስታውሰዋል። እንግዳ ተቀባይነት በተግባር እንድንገልጽ የተጠራንበት ወንጌላዊ ተግባር መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ የሚያንኳኳ ሰው እንዲገባ የቤታችንን እና የልባችንን በር መክፈት ማለት ነው ብለዋል። እውነተኛ የወንድማማችነት ስሜት ልባዊ እንግዳ ተቀባይነትን እና የማኅበራዊ ሕይወት ልምድን ያሳድጋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህ የማይገለጽ ከሆነ ወደ ራስ ወዳድነት፣ ወደ ፍርሃት፣ ወደ ንቀት፣ ሌላውን አለመቀበል ወይም ግድየለሽነትን እንደሚያስከትል አስረድተዋል።

13 November 2021, 15:46