ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቅዱስ ዮሴፍ የዘመናችን ምሳሌ እና ምስክር ነው ማለታቸው ተገለጸ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን ከሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ሆነው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በኅዳር 08/2014 ዓ.ም ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቅዱስ ዮሴፍ እና እርሱ የኖረበት ሁኔታ በሚል አርእስት የቀረበ የክፍል አንድ አስተምህሮ እንደ ነበረ የተገለጽ ሲሆን ቅዱስ ዮሴፍ የዘመናችን ምሳሌ እና ምስክር ነው ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

(እ.አ.አ) በታኅሣሥ 8/1870 ዓ.ም ብፁዕ ፒዮስ ዘጠነኛ ቅዱስ ዮሴፍ የአለማቀፋዊቷ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ መሆኑን አወጁ። ይህ ከታወጀበት ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በኋላ ለቅዱስ ዮሴፍ የተሰጠ ልዩ ዓመት ውስጥ እየኖርን የምንገኝ ሲሆን እናም (በላቲን ቋንቋ ፓትሪስ ኮርዴ፣ Patris corde በአማርኛ የአባት ልብ) በተሰኘው ሐዋርያዊ መልእክቴ በእርሱ ላይ አንዳንድ አስተያየቶችን አካፍዬ ነበር። እንደበፊቱ ሁሉ ዛሬ በዚህ ወቅት፣ በተለያዩ አካላት በተሰራው ዓለም አቀፍ ቀውስ ውስጥ፣ ድጋፍ፣ ማጽናኛ እና መመሪያ ሊሰጠን አይችልም። ስለዚህ ለእርሱ የምሥክርነት ዑደቶችን ለመስጠት ወስኛለሁ፣ ይህም በምሳሌው እና በእሱ ምሥክርነት ራሳችንን እንድናበራ የበለጠ እንደሚረዳን ተስፋ አደርጋለሁ። በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ እንነጋገራለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዮሴፍ የሚል ስም ያላቸው ከአሥር በላይ ሰዎች አሉ። ከመካከላቸው ዋነኛው የያዕቆብና የራሔል ልጅ ሲሆን በተለያዩ መንገዶች ከባሪያነት ወደ በግብፅ ከፈርዖን ቀጥሎ ሁለተኛው ታላቅ ሰው እስከ መሆን እስከደረሰው ሰው ድረስ ማየት እንችላለን (ዘፍ. 37-50)። ዮሴፍ የሚለው ስም የዕብራይስጥ ቋንቋ ነው "እግዚአብሔር ይጨምርልህ፣ እግዚአብሔር ያሳድግህ" የሚል ትርጓሜ አለው። በመለኮታዊ ስጦታ ላይ በመተማመን የተመሰረተ እና በተለይም የመራባት እና ልጆችን ማሳደግን የሚያመለክት ምኞት፣ በረከት ነው። በእርግጥም ይህ ስም የናዝሬቱ ዮሴፍ የባሕርይ መገለጫ የሆነውን አንድ አስፈላጊ ገጽታ ይገልጽልናል። እርሱ በእምነት የተሞላ፣ በማስተዋል የተሞላ ሰው ነበር። በእግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበቃ ያምናል፣ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበቃ  ላይ እምነት አለው። እያንዳንዱ እርምጃው፣ በወንጌል እንደተገለጸው፣ እግዚአብሔር “እድገትን እንደሚሰጥ”፣ እግዚአብሔር “እንደሚጨምር”፣ እግዚአብሔር “በረከት እንደ ሚሰጥ” በእርግጠኝነት በማመን የታዘዘ ሰው ነበር፣ ያም ማለት እግዚአብሔር ለድነት እቅዱ ቀጣይነት እንደሚሰጥ ያምን ነበር ማለት ነው። በዚህም የናዝሬቱ ዮሴፍ ከግብጹ ዮሴፍ ጋር ይመሳሰላል።

ስለ ዮሴፍ፣ ቤተልሔም እና ናዝሬት በይበልጥ ለመረዳት ይቻል ዘንድ በመጀመሪያ መልካ ምድራዊ ማመሳከሪያ መጠቀም ስለ እሱ ባለን ግንዛቤ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

በብሉይ ኪዳን የቤተልሔም ከተማ ቤተ ሌም ተብላ ትጠራለች ትርጓሜውም “የዳቦ ቤት” ወይም ደግሞ ኤፍራታ፣ በዚያ በሰፈሩት ነገዶች ስም ይጠራል። በአረብኛ ግን ይህ ስም "የስጋ ቤት" የሚለውን ትጉም ይሰጣል፣ ምናልባትም በአካባቢው ብዙ የበጎች እና የፍየሎች መንጋዎች ስላሉ የተሰጠ ስያሜ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ፣ እረኞቹ ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከቱት በአጋጣሚ አይደለም (ሉቃ. 2፡8-20)። በኢየሱስ ታሪክ ብርሃን እነዚህ ስለ እንጀራ እና ስጋ የሚጠቅሱ ጥቅሶች የቅዱስ ቁርባንን ምስጢር ያመለክታሉ፣ ኢየሱስ ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ ነው (ዮሐ. 6፡51)። ስለ ራሱ እንዲህ ይላል፡- “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” (ዮሐ 6፡54) በማለት ይናገራል።

ቤተልሔም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዘፍጥረት መጽሐፍ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተጠቅሳለች። ቤተልሔም በአጭር ግን አስደናቂ በሆነው የሩት መጽሐፍ ከተነገረው ከሩት እና ከኑኃሚን ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው። ሩት ኢዮቤድ የሚባል ወንድ ልጅ ወለደችለት ከእዚያም እሴይ የንጉሥ ዳዊት አባት ተወለደ። የኢየሱስ ሕጋዊ አባት የሆነው ዮሴፍ የመጣው ከዳዊት ዘር ነው። ከዚያም ነቢዩ ሚክያስ ስለ ቤተ ልሔም ታላላቅ ነገሮችን ተንብዮአል “አንቺ ግን፣ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፤ ከይሁዳ ነገዶች መካከል ትንሿ ብትሆኚም፣አመጣጡ ከጥንት፣ ከቀድሞ ዘመን የሆነ፣ የእስራኤል ገዥ፣ ከአንቺ ይወጣልኛል” (ሚክ 5፡1) )። ወንጌላዊው ማቴዎስ ይህንን ትንቢት ወስዶ ከኢየሱስ ታሪክ ጋር ያገናኘው ይህ እንደ ተፈጸመ ለማሳየት እንደ ሆነ ግልጽ ነው።

እንድያውም የእግዚአብሔር ልጅ ቃል ሥጋ ለብሶ የተገለጠበት ቦታ ኢየርሱሳሌም እንድትሆን ሳይሆን የፈለገው በተቃራኒው  ቤተልሔምን እና ናዝሬትን በመምረጥ ምንም ዓይነት ዜና የማይሰማባቸውን ከዘመኑ ኃይሎች ጩኸት የራቁትን ሁለቱን ርቀው የሚገኙትን መንደሮች ነበር የመረጠው። ሆኖም ኢየሩሳሌም በጌታ የተወደደች ከተማ ነበረች (ኢሳ 62፡1-12)፣ “ቅድስት ከተማ” (ዳንኤል 3፡28)፣ በእግዚአብሔር የተመረጠች ማደሪያው (ዘካሪያስ 3፡2፤ መዝ 132፡13) )። በእርሷ ውስጥ የሕግ መምህራንን ጸሓፍትን ፈሪሳውያንን ካህናትን እና ሽማግሌዎችን፣ የሕዝብ አልቆች (ሉቃ. 2:46፣ ማቴ 15:1፣ ማርቆስ 3:22፣ ዮሐ 1:19፣ ማቴ. 26፡3) የሚኖሩባት ከተማ ነበረች።

ለዚህ ነው የቤተልሔምና የናዝሬት መመረጥ ዳርቻዎች እና ገጠራማ ወጣ ይሉ ሥፍራዎች በእግዚአብሔር የተመረጠ መሆኑን የሚነግረን። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም አልተወለደም ፣ ኢየሱስ በገጠራማ ስፋራ ተወልዶ እስከ ሠላሳ ዓመቱ ድረስ ሕይወቱን በዚያ ዳርቻ ወይም ገጠራማ በሆነ ስፍራ በመኖር እንደ ዮሴፍ አናጢ ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል። ለኢየሱስ፣ ዳርቻ ወይም ገጠራማ ስፍራዎች ሞገስ ተሰጥቷቸዋል። ይህንን እውነታ በቁም ነገር አለመውሰድ ራሱን በመልካ ምድራዊ እና ነባራዊ ሁኔታዎች ውስጥ መግለጥ የቀጠለውን የእግዚአብሔርን ወንጌል እና ሥራ በቁም ነገር አለመውሰድ ነው። ጌታ ሁል ጊዜ በድብቅ በከባቢ አየር ውስጥ ይሠራል ፣ በነፍሳችን ውስጥ ፣ በነፍስ ዳርቻ ፣ በስሜቶች ፣ ምናልባትም የምናፍርባቸው ስሜቶች ፣ ጌታ ግን ወደፊት እንድንሄድ ሊረዳን ይችላል። ጌታ እራሱን በየአካባቢው ፣በመልክአ ምድራዊ እና ነባራዊ ሁኔታ መግለጥ ቀጥሏል። በተለይም ኢየሱስ ኃጢአተኞች ፍለጋ ይሄዳል፣  ወደ ቤታቸው ይገባል፣ ያናግራቸዋል፣ ወደ መለወጥም ይጠራቸዋል። ስለዚ ነው የሕግ መምሕራን እና ጸሐፍት “ይህንን መምህራችሁን ተመልከቱ፣ ከሃጥኣን ጋር ይበላል፣ ከእርኩሳን ጋር ይሄዳል” በማለት ተቆጥተው የተናገሩት በዚህ ምክንያት ነው። ክፉ ያላደረጉትን ነገር ግን መከራ የደረሰባቸውን ድውያንን፣ የተራቡትን፣ ድሆችንና ታናናሾችን ይሻል። ኢየሱስ ሁልጊዜ ወደ ልባችን ዳርቻ፣ ወደ ነፍሳችን ዳርቻ ይወጣል፣ ይህ ነው፣ ከኅፍረት የተነሳ ወደ ማናሳየው ትንሽ የተደበቀ ክፍል እርሱ በመግባት ያድነናል።

ከዚህ አንፃር በጊዜው የነበረው ማህበረሰብ ከእኛ ብዙም የተለየ አይደለም። ዛሬም መሃል እና ዳር አለ። ቤተክርስቲያንም ከዳር እስከዳር ምሥራቹን ለመስበክ እንደተጠራች ታውቃለች። የናዝሬት አናጺ የሆነው እና በእግዚአብሔር እቅድ ለወጣት እጮኛው እና ለራሱ የሚታመን ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አለም ሆን ብሎ ችላ በምለው ነገር ላይ ዓይኖቿን እንድታደርግ ያሳስባታል። ዛሬ ዮሴፍ እንዲህ በማለት ያስተምረናል፡- “ዓለም አብዝቶ በሚያመሰኘው ነገር ላይ ዐይኖቻችሁን አታድጉ፣ ወደ ማዕዘኑ ተመልከቱ፣ ወደ ጥላው ተመልከቱ፣ ከዳር እስከ ዳር፣ ዓለም የማይፈልገውን ተመልከቱ። እያንዳንዳችን ሌሎች የሚጥሉትን ጠቃሚ ነገር እንድናስብበት ያሳስበናል። ከዚህ አንጻር እርሱ በእውነት የወሳኙ ነገር ጌታ ነው፡ የሚያስጨንቀን ነገር ትኩረታችንን እንደማይስብ ነገር ግን መገኘትና አድናቆት እንዲኖረን በትዕግስት ማስተዋልን እንደሚጠይቅ ያሳስበናል። አስፈላጊ የሆነውን ለማወቅ፣ መላው ቤተክርስቲያን ይህንን ግንዛቤ፣ ይህን የመለየት ችሎታ፣ አስፈላጊ የሆነውን ነገር የመገምገም አቅም እንዲያገኝ እንዲማልድ እንጠይቀው። እንደገና ከቤተልሔም እንጀምር፣ ከናዝሬትም እንጀምር።

ዛሬ በጣም በተረሱ የአለም መልካ ምድራዊ አካባቢዎች ውስጥ ለሚኖሩ ወይም የመገለል ሁኔታ ላጋጠማቸው ወንዶች እና ሴቶች ሁሉ መልእክት ልልክ እፈልጋለሁ። የሚመለከቱትን ምስክርነት እና ጠባቂነት በቅዱስ ዮሴፍ ውስጥ ያግኙ። በዚህ ጸሎት ወደ እርሱ መዞር እንችላለን፣ ቀለል ያለ ነገር ግን ከልብ በሚመነጨው ጸሎት ነው።

ቅዱስ ዮሴፍ፣

አንተ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር የምትታመን

እና ምርጫዎችንም በእርሱ በመመራት የተገበርክ፣

በፍቅር እቅዱ ላይ እንጂ

በራሳችን እቅድ ላይ ብዙ እንዳንመካ አስተምረን።

አንተ ከዳርቻው የመጣህ

እይታችንን እንድንቀይር እርዳን

እና አለም የሚጥለውን እና የተገለለውን ነገር እንድንመርጥ እርዳን።

ብቸኝነት የሚሰማቸውን አጽናና

በፀጥታ የሚሰሩትን ደግፍ

ህይወትን እና የሰውን ክብር ለመጠበቅ እንችል ዘንድ እርዳን።

 አሜን!

17 November 2021, 13:19