ፈልግ

የስደተኞች ችግር በአውሮፓ የስደተኞች ችግር በአውሮፓ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለስደተኞች ድንበሮችን መዝጋት ስብዕናችንን ይቀንሳል ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅት የተመሠረተበት 70ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ከስደተኞች ቁጥር ጀርባ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚመጸኑ በርካታ ወንድሞች እና እህቶች መኖራቸውን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ይህን ከማድረግ ፈንታ ድንበሮቻችንን የምንዘጋባቸው ከሆነ ስብዕናችንን እንቀንሳለን ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅት የተመሠረተበት 70ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ኅዳር 20/2014 ዓ. ም. ባሳተላለፉት የቪድዮ መልዕክት፣ በዓለም ዙሪያ በብዙ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች የሚሰጥ የትኩረት እና እንክብካቤ መጠን እጅግ ያሳዝናል ብለው፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስደተኞች እንደ “ሸቀጥ” ተቆጠረው የፖለቲካ ፉክክር ሰለባዎች ተደርገው እንደሚወሰዱ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅት “IOM”

ዋና ጽሕፈት ቤቱ ጄኔቫ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅት፣ በመንግሥታት ኅብረት ተቋቁሞ በስደት መስክ የሚሰራ ድርጅት መሆኑ ሲታወቅ፣ ቅድስት መንበርም የድርጅቱ አባል አገር ሆና ከቆየች አሥር ዓመታት ማስቆጠሯ ታውቋል። በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የተነበበው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት እንደገለጸው፣ “የሰዎች መከራና ተስፋ መቁረጥ እንዴት ተብሎ ለፖለቲካ አጀንዳዎች ማራመጃ ሊውል ይችላል?” በማለት ጠይቋል። በማከልም “ሰብዓዊ ክብር አደጋ ላይ ሲወድቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዴት በልጠው ሊታዩ ይችላሉ?” በማለት ጠይቆ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ "በየአገራቱ ድንበሮች አካባቢ የሚታየው መሠረታዊ የሰው ልጅ ክብር ማጣት የሁላችንም ስብዕና ይቀንሳል" ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዓለም ዙሪያ የሚታየውን የስደተኞች አያያዝ በማውገዝ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፣ በቅርቡ የእንግሊዝ ቻናልን ሲያቋርጡ የሞቱትን፣ በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ሕይወታቸውን ያጡትን እና ድንበር ተዘግቶባቸው የሚሰቃዩ የቤላሩስ ስደተኞችን በማስታወስ ያለፈው እሑድ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡበት ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑ ታውቋል።

የአመለካከት ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል

በስደት ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲደረግ ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የስደትን አስከፊነት መናገር ብቻ ሳይሆን በሰዎች መካከል እኩልነት ማጣት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ የአካባቢ መራቆት እና የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩ መዘንጋት የለበትም ብለው፣ በተጨማሪም ስለ ወደፊት ዕጣ ፈንታ ማለም፣ ቆራጥነት፣ የውጭ ትምህርት ዕድል፣ የተበታተኑ የቤተሰብ አባላት ተመልሰው መገናኘት፣ አዳዲስ የለውጥ ዕድሎችን ማግኘት፣ ደህንነትን ማስጠበቅ እና አስቸጋሪ ቢሆንም ሰብዓዊ ክብርን የሚያስጠብቅ ሥራን ማግኘት የሚሉ ጉዳዮች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

“በስደት ላይ የሚደረጉ ክርክሮች በእውነቱ የሚሰደዱ ሰዎችን ብቻ የሚመለከት አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይልቁንስ ስለ ሁላችንም ሕይወት፣ ስላለፈው፣ አሁን ስላለው እና የማኅበረሰባችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚመለከት መሆኑን አስረድተው፣ በስደተኞች ቁጥር መብዛት መደነቅ ሳይሆን ነገር ግን ሁሉንም በአካል በማግኘት፣ ፊታቸውን እያየን እና ታሪካቸውን በማዳመጥ፣ በግል እና በቤተሰብ ደረጃ ለሚገኙበት ሁኔታ የምንችለውን ያህል ለማድረግ መሞከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ሰብዓዊ ርኅራሄ፣ ፍትህ እና ወንድማማችነት ሊኖር ይገባል ብለዋል። ዛሬ “የጋራ ፈተና” የሆነብን ነገር ቢኖር “የሚያስጨንቀንን ሁሉ ማስወገድ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መወገድ ያለበትም "ንቆ የመተው ባሕል" እንደሆነ ገልጸው፣ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያላቸው እሴቶች የስደተኞችን አያያዝ፣ አካባቢያዊ እና ብሔራዊ የሰዎች ማኅበራዊ ሕይወትን ሊመሩ ይገባል ብለዋል።

ከስደት የሚገኙ ጥቅሞች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን በመቀጠል፣ ስደተኞችን መቀበል ብቻ ሳይሆን ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዕድገት የሚያበረክቱትን ጥቅም ማሰብ እንደሚገባ አሳስበዋል። በአንድ ወገን ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ የስደተኞች ጉልበት የሠራተኛን እጥረት የሚያካክስ በመሆኑ ተቀባይነት አለው ብለው፣ በሌላ ወገንም ስደተኞች ብዙን ጊዜ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀባይነትን ያለማግኘት ችግር መኖሩን አስረድተዋል።

እንደ አለመታደል ሆኖ በሰው ልጅ ፍላጎት እና ክብር ላይ የበላይነትን የተቀዳጀው የኢኮኖሚ ጥቅም ድርብ ችግር ማስከተሉን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ የሥራ ዘርፎች መዘጋት፣ በሥራው ዓለም በርካታ ቁጥር ይዘው በሚገኙ ስደተኞች ላይ ከፍተኛ ጫና ከማሳደሩ በተጨማሪ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የገንዘብ ድጋፍ መርሃ ግብር፣ በመሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባቶችን እንዳያገኙ ማድረጉን አስረድተዋል።

ችግሩን በክብር መወጣት

እነዚህን የዕለት ተዕለት ችግሮች በክብር ለመሻገር ልዩ ልዩ የመፍትሄ መንገዶችን መፈለግ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ በስቃይ መካከል ተስፋን ማድረግ ገዳቢ ፖሊሲዎችን ሁል ጊዜ እንደሚያሸንፍ ገልጸው፣ ለስደተኞች ሕጋዊ መንገዶች የሚመቻቹላቸው ከሆነ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች መረብ የመውደቅ፣ የመበዝበዝ እና የመሰቃየት ዕድላቸው እንደሚቀንስ አስረድተው፣ ስደተኞች “በመላው ሰብዓዊ ቤተሰብ መካከል ያለውን ትስስር አጉልተው የሚያሳዩ፣ የባሕል ውድ ሃብት፣ የንግድ ልውውጦችን ለማዳበር የሚያስችል ቁርኝት የሚታይበት የዳያስፖራ ማህበረሰቦችን የሚያካትቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚና

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባቀረቡት መልዕክት፣ የሕገወጥ ስደት መንስኤዎች በአስቸኳይ መልስ እንዲያገኙ፣ ስደት ተስፋን ከመቁረጥ የሚወሰድ እርምጃ ከመሆን ይልቅ በማስተዋል የሚደረግ ምርጫ እንዲሆን በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በትውልድ አገራቸው ሰላማዊ እና የተረጋጋ ኑሮ መኖር የሚችሉ አብዛኞቹ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ለመሰደድ እንደማይገደዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ የተሻለ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች በአስቸኳይ የሚመቻቹ ከሆነ ሰላምን፣ ፍትህን፣ ደህንነትን እና የሰውን ክብር ሙሉ በሙሉ ለማስክበር ስደት ብቸኛው አማራጭ ሊሆን እንደማይችል ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። “አደጋ ላይ የወደቁት ስደተኞች እውነተኛ ሰዎች እንጂ የቁጥር ብዛት አይደሉም” በማለት ቅዱስነታቸው ተናግረው፣ “ይህን በመገንዘብ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ተቋሞቿ በስደት ጉዞ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በክብር የመቀበል፣ ደህንነታቸውን የመጠበቅ፣ የመንከባከብ እና ከማኅበረሰቡ ጋር አብረው እንዲኖሩ የማድረግ ተልዕኮዋን መቀጠል ይገባል” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

30 November 2021, 16:25