ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሁለንተናዊ እድገት ማምጣት የሚቻልበት መንገድ መኖሩን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፈረንሳይ አገር ከኅዳር 17-19/2014 ዓ. ም. የሚከበረውን ማኅበራዊ ሳምንት ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፣ የአገሪቱ ዜጎች ለችግር ለተጋለጡት እና ለፍጥረታት በሙሉ መልካምን በመመኘት፣ ሁለንተናዊ እድገትን ማምጣት የሚቻልበትን የተስፋ ጎዳናን እንዲያመቻቹ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓመታዊው ማኅበራዊ ሳምንትን ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶችን ስታደርግ የቆየች የፈረንሳይ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ባሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ስልጠና የሚሰጥበት እና ውይይት የሚካሄድበትን መድረክ ማዘጋጀቷ ታውቋል። "የወደፊቱን ህልም በድፍረት በማለም፣  ለሰዎች እና ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል" የሚል መሪ ሃሳብ ያለው የዘንድሮ ማኅበራዊ ሳምንት፣ ከዓርብ ኅዳር 17 እስከ እሑድ ኅዳር 19/2014 ዓ. ም. በመከበር ላይ መሆኑ ታውቋል።

በጋራ ማለም አዲስ እውነታን ይፈጥራል

በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የተፈረመው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት፣ የበዓሉ ተካፋዮች አሁን በሚኖሩበት እውነታ ላይ በማስትኮር የወደፊት ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል። ቅዱስነታቸው “ይህን ለማድረግ መፍራት የለብንም” ብለው፣ "በተለይም ይህ ህልም በጋራ መሆን አለበት" ብለዋል። 

የፈረንሳይ ሕዝቦችም፣ “ውድ አማዞንያ” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ የገለጿቸውን ሕልሞች  እንዲመለከቱ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የድሆችን መብት እና የባሕል ሃብቶችን የሚጠብቅ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችን የተፈጥሮ ውበቷን የሚንከባከብ እና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገለጸውን የእግዚአብሔርን የፍቅር ወንጌል የሚቀበል ማኅበረሰብ ለመገንባት ማለም አለብን ብለዋል። እነዚህ ሕልሞች እውን ሊሆኑ የሚችሉት በጋራ ሲካፈላቸው ብቻ እንደሆነ ገልጸው፣ በፈረንሣይ የሚከበረውን ማኅበራዊ ሳምንታት የሚመስሉ ዝግጅቶች መንገዶችን ለማመቻቸት የሚያግዙ መሆናቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል።

ክርስቲያን ለዓለም ያለው ተስፋ

ዓለማችንን ክፉኛ የጎዳው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ “አኗኗራችንን መለወጥ እንዳለብን አስተምሮናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ሰዎች በተስፋ እንዲኖሩ የሚያደርጋቸውን የወደፊቱን ጊዜ ማለም አለብን” ብለዋል። በማከልም፣ "እንደ ክርስቲያኖች በዚህ ወሳኝ ጊዜ ወደ ዓለም ማምጣት የምንችለው የሚያምር የተስፋ ባህሪ ይህን ነው" በማለት አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፈረንሳይ አገር ከኅዳር 17-19/2014 ዓ. ም. የሚከበረውን ማኅበራዊ ሳምንት ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ የፈረንሳይ ዜጎች በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉት ውይይት በእግዚአብሔር እንዲመራ ፈቃዳቸው ጠይቀው፣ ዓለማችን ከምን ጊዜም አብልጦ የሚፈልገውን የተስፋ መንገድ በሥራዎቻቸው እንዲያዘጋጁ፣ ለፍጥረታት እና ተጋላጭ ማኅበረሰብን እንዲደግፉ፣ እግዚአብሔር ልባቸውን እንዲከፍት፣ አእምሮአቸውን በማብራት ለውይይት እንዲያነሳሳቸው በመለመን መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።  

27 November 2021, 16:18