ቅዱስነታቸው፣ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ከሚረዳ ማኅበር አባላት ጋር በቅ. ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ቅዱስነታቸው፣ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ከሚረዳ ማኅበር አባላት ጋር በቅ. ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የአመጽ ሰለባ ለሆኑ ሴቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጣሊያን ውስጥ በደል የደረሰባቸውን እና በተለይም በችግር ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች ድጋፍን ለሚሰጥ ማኅበር አባላትን ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአመጽ ሰለባ ለሆኑ ሴቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ድምጻቸውንም ማድመጥ እንደሚገባ በማሳሰብ፣ የማኅበሩ አባላት በአርአያነታቸው ይህን ለማድረግ የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲያድሱ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጥቃት ሰለባዎችን ማዳመጥ፣ ጥበቃን ማድረግ፣ መርዳት እና ስቃያቸውንም ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ያስገነዘቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በየዓመቱ ኅዳር 16 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በማውገዝ የሚከበረውን ዕለት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በተለያየ መልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ህገወጥ ዝውውሮችን፣ ጥቃቶችን፣ ጉስቁልናዎችን እና ግድያዎችን በማውገዝ የዓለምን ትኩረት መሳባቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከሚያቀርቡት ሳምንታዊ የትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮ አስቀድመው፣ በጣሊያን ውስጥ በደል ለደረሰባቸው ሴቶች ድጋፍ ከሚሰጥ ማኅበር አባላት ጋር በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ተገናኝተው ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

የበለጠ ፍትሃዊ እና ደጋፊ ማኅበረሰብ ሊኖር ይገባል

ቅዱስነታቸው ለማኅበሩ አባላት በሙሉ ካስተላለፉት መልዕክት ጋር፣ ማኅበሩ በደል ለደረሰባቸው እና ጭንቀት ውስጥ ለሚገኙት ሴቶች ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለሚያበረክተው የዕርዳታ እና የድጋፍ አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። “አመጽ እና ብጥብጥ መጥፎ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ማኅበሩ በሚያደርገው ጠቃሚ እንቅስቃሴ አማካይነት የበለጠ ፍትሃዊ እና የሚደጋገፍ ማኅበረሰብን መገንባት የሚያስችል አስተዋፅዖን እንዲያበረክቱ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ ማኅበሩ በሚያሳየው መልካም ምሳሌው፣ የአመጽ ሰለባ ለሆኑ ሴቶች የሚያሳየውን ቁርጠኝነት እንደገና በማደስ እንዲቀሰቀስ፣ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ስቃያቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

የጥቃቱ ሰለባ ሴቶችን ተቀብሎ የማስተናገድ ዕቅድ

በደል እና ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች፣ ድጋፍ የሚሰጥ ማኅበር በጣሊያን ውስጥ ተቋቁሞ አገልግሎቱ መስጠት የጀመረው፣ እ. አ. አ በ2006 ዓ. ም. ሲሆን፣ ከድረ ገጹ መረዳት እንደተቻለው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ለደረሰባቸው 489 ሴቶች በቂ እና ውጤታማ የሞራል፣ የስነ-ልቦና እና የህግ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ታውቋል። በቁጥር 37 የሚደርሱ የማኅበሩ በጎ ፈቃደኞች ያለ ምንም ትርፍ ተጨባጭ እና አስቸኳይ ዕርዳታን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ታውቋል። ማኅበሩ ባሁኑ ጊዜ የዕርዳታ እቅዱን በማስፋት፣ የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ ሴቶች የሚሆን መጠለያ ማዕከል አስገንብቶ አገልግሎት ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑ ታውቋል። በማዕከሉ የሚስተናገዱ ሴቶች ጥበቃ እንደሚደረግላቸው፣ ለደህንነታቸውም ዋስትና እንዲያገኙ እና የሚኖሩበት ቦታ ምቾት እንዳለው እንዲያውቁ ለማድረግ መሆኑን የማኅበሩ ተጠሪዎች ገልጸዋል።   

24 November 2021, 16:50