ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በብርሃነ ልደቱ ወቅት የሚቀርብ የመዝሙር ወድድር አዘጋጆች እና ተሳታፊዎች ጋር ሲገናኙ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በብርሃነ ልደቱ ወቅት የሚቀርብ የመዝሙር ወድድር አዘጋጆች እና ተሳታፊዎች ጋር ሲገናኙ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የወረርሽኝ ወቅት ቢሆንም ብርሃነ ልደቱ ሙሉ ተስፋን ይዞ እንደሚመጣ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኅዳር 13/2014 ዓ. ም. በብርሃነ ልደቱ ወቅት የሚቀረቡ የመዝሙር ወድድር አዘጋጆችን እና ተሳታፊዎችን በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የርህራሄ እና የየዋህነት በዓል መሆኑን ገልጸው፣ በበዓሉ ወቅት የሚቀርቡ ትናንሽ ምልክቶች በባሕላዊ ፣ ማኅበራዊ እና ትምህርታዊ ሂደቶች ውስጥ እድገት እና ለውጥ የሚያመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ለወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እንቅፋት ያጋጠመው የብርሃነ ልደቱ በዓል፣ አንዳንድ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚያደርግ ቢሆንም ነገር ግን ተስፋን እንዳንቆርጥ የሚጋብዘን መሆኑን ገልጸዋል። በወረርሽኙ ምክንያት በዓሉን የሚያደምቁ መብራቶች ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚሰጠን የልብ ውስጥ ደስታ መጠን ሊጎድል እንደማይችል ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የብርሃነ ልደቱ በዓል የየዋህነት በዓል ነው

እ. አ. አ በ2015 ዓ. ም. ተመሠርቶ የትምህርት ተልዕኮችን በማገዝ ላይ ለሚገኝ “Gravissimum Educationis” ለተሰኘ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ቅዱስነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ወጣቶቹ የሚያቀርቡት የመዝሙር ውድድር፣ የብርሃነ ልደቱ በዓል ሊከበር በተቃረበበት እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቋቋም ጥረቶች በሚደረጉበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፣ በብርሃነ ልደቱ መታሰቢያ ወቅት እየገጠመን ያለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፈተና ሊያስደነግጠን አይገባም ብለው፣ ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ከምንም በላይ የርኅራኄ በዓል፣ ውበቱም ትሁት እና በሰዎች የልብ ደስታ የተሞላ ነው ብለዋል።

ትናንሽ ምልክቶች ብዙ ነገሮችን ይለውጣሉ

የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት ከሁሉም በላይ ስጦታ እና አዳዲስ ፈተናዎችን የምንጋራበት አጋጣሚ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት የበለጠ የሚደምቀው ተጨባጭ የሆኑ የፍቅር ሥራዎችን ስናጋራ መሆኑን አስረድተዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በዓል አንድነት የሚያረጋግጥ፣ ከአንገት በላይ የሚከወን ሳይሆን ልብን በማስፋት ለእርግጠኝነት የሚጋብዝ እና የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች በደንብ ሊረዱት የሚችሉት እና ራስን በስጦታ በማቅረብ ባሕላዊ፣ ማህበራዊ እና ትምህርታዊ ለውጦችን ማመንጨት የሚችሉበት መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

ድፍረት እና ብልሃት ሊኖር ይጋባል

ዓለም አቀፍ የትምህርት ስምምነቶችን ለማስረዳት የሚረዱ በርካታ የትምህርት ጥምረቶች መኖራቸውን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን መስጠት፣ ክፍፍልን ማስወገድ የሚችሉ ሰዎችን ለማዘጋጀት እንደሚረዳ ገልጸው፣ ልዩነትን አስወግዶ ሰብዓዊ ግንኙነቶችን እንደገና ለመገንባት እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ የሚረዱ እሴቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል። እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት ድፍረትን ይጠይቃል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ “የሰውን ልጅ ማዕከል ያደረገ” እና “ራስን ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ዝግጁ የማድረግ” ድፍረት እና ብልሃት ሊኖር ይገባል ብለዋል። ወጣቶቹ አዳዲስ የብርሃነ ልደቱ ዜማዎችን ደርሰው ለትልቅ ሥራ ማብቃታቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ እነዚህን የጥበብ ሥራዎች ለሌሎች በማጋራት በአንድነት የተሻለች ዓለምን ለማለም መብቃታቸውን አስረድተዋል።

ትርጉም ያለው ውበት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዘንድሮ በሚከበር የብርሃነ ልደት በዓል ላይ የሚቀርብ የመዝሙር ወድድር አዘጋጆች እና ተሳታፊዎች ያደረጉትን ንግግር ከማጠቃለላቸው በፊት፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እ. አ. አ ታኅሳስ 8/1965 ዓ. ም. ለስነ ጥበብ ሰዎች ባቀረቡት መልዕክት፣ የብርሃነ ልደቱን ውበት ለመመልከት ተስፋን መቁረጥ እንደሌለባቸው መጋበዛቸውን አስታውሰው፣ የብርሃነ ልደቱ ውበት ሥጋን የለበሰው አምላክ መገልጥ፣ የፊት ገጽታ ውበት የሚታይበት፣ የታሪኩ ውበት የሚታይበት፣ ቅዱስ ፍራንቸስኮ እንዳስተማረን፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን የሚሞሉ ፍጥረታት የሚታዩበት እና በልዑል ውዳሴ የሚሳተፉት መሆኑን አስረድተዋል።

በብርሃነ ልደቱ በዓል የሚቀርብ የመዝሙር ውድድር

ዘንድሮ በሚከበረው የብርሃነ ልደቱ በዓል ላይ የሚቀርቡ የመንፈሳዊ ዜማዎች ውድድር፣ ከብሔራዊ መዘምራን ጋር በጥምረት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከውድድሩ የሚገኝ የገንዘብ ገቢ ለበጎ አድራጎት ሥራ በመመደብ በሦስት ምድቦች ማለትም ለጽሁፍ፣ ለሙዚቃ እና ለትርጉም ሥራ የሚውል መሆኑ ታውቋል። ውድድሩን የተሳተፉ ሦስት ምርጥ ሥራዎች፣ እ. አ. አ. በ2021 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚቀርብ የብርሃነ ልደቱ ኮንሰርት ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። 

23 November 2021, 16:14