ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ለባግዳድ ሆስፒታል የሕክምና መገልገያ መሣሪያን ለገሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በኢራቅ መዲና ባግዳድ ለሚገኝ የቅዱስ ሩፋኤል ሆስፒታል ንጹሕ አየር የሚያመነጭ የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያ ለግሰዋል። ቅዱስነታቸው የለገሱት የንጹሕ አየር መተንፈሻ መሣሪያው፣ በሆስፒታሉ ውስጥ የሕክምና ዕርዳታን በማግኘት ላይ ለሚገኙ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሕሙማን አገልግሎት የሚውል መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከቅዱስነታቸው የተለገሰለትን የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያ የተቀበለው የባግዳድ ቅዱስ ሩፋኤል ሆስፒታል፣ መሣሪያውን በይፋ ለአገልግሎት ያዋለው ሲሆን፣ መሣሪያው ለሆስፒታሉ የተበረከተው፣  በቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከተመደበ የዕርዳታ ምንጭ መሆኑ ታውቋል።  

ከሆስፒታሉ አስተዳደር የቀረበ ምስጋና

በባግዳድ ከተማ የሚገኝ የቅዱስ ሩፋኤል ሆስፒታል አስተዳዳሪ እህት ማርያን ፒዬር፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተለከላቸውን የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያን ተቀብለው፣ ለቅዱስነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። እህት ማርያን ፒዬር ለቅዱስነታቸው በላኩት የምስጋና መልዕክት፣ “መሣሪያው ሆስፒታሉ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተጠቁ ህሙማን የሚያቀርበው የሕክምና እርዳታ አገልግሎት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያድርግ ነው” በማለት አመስግነዋል።

አገልግሎት ከቅዱስ ሩፋኤል ሆስፒታል ባሻገር ነው

የሆስፒታሉ ዳይሬክተር አቶ ካሌብ ማንሱር ሳዋ እና የላቦራቶሪ ዲፓርትመንት ኃላፊ ዶክተር አምጃድ ካቺክ ማጂድ፣ ማሽኑ ያለ ችግር ለመተንፈ የሚያግዝ ንጹሕ አየር ለህሙማን በመስጠት ለተከታታይ ወራት አገልግሎት ሲያቀርብ መቆየቱን አረጋግጠው፣ የንጹሕ አየር አቅርቦቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሕሙማኑን ለማከም አስፈላጊ እንደ ሆነ እና ተጨማሪ የቫይሬሱ ተጠቂዎች ወደ ሆስፒታሉ በሚመጡበት ጊዜ የሕክምና ድጋፍ ለመስጠት የሚያግዛቸው መሆኑን አስረድተዋል። የሕክምና ባለ ሙታዎቹ አክለውም፣ መሣሪው የሚያመርተው ንጹሕ አየር፣ በቅዱስ ሩፋኤል ሆስፒታ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎችን ጨምሮ ለሌሎች ሆስፒታሎችም የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።

25 November 2021, 16:33