ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዛሬን ህመም በመፈወስ የነገን ተስፋ ማሳደግ ይገባል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሕዳር 05/2014 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ አምስተኛው የዓለም የድሆች ቀን አስመልክተው መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን የዛሬን ሕመም በመፈወስ የነገን ተስፋ ማሳደግ ይገባል ማለታቸው ተገልጿል። የእግዚአብሔር ማዳን የወደፊት ተስፋ ብቻ ሳይሆን አሁን በቆሰለው ዓለማችን ውስጥ እየሰራ መሆኑን ያስታውሰናል በማለት በእለቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት የተናገሩት ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን “የዛሬን ሕመም በመፈወስ የነገን ተስፋ ማሳደግ” አለብን ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እሁዱ ሕዳር 05/2014 ዓ.ም የዓለም የድሆች ቀን በተከበረበት ወቅት ይህንን ቀን ምክንያት በማድረግ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት የዛሬ ህመም ከነገ ተስፋ ጋር አብሮ የሚኖርበትን ታሪክ ለመተረጎም የሚረዱን የሰው ልጅ ማለትም ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ስላሉት ግራ የሚያጋቡ ምልክቶች በሚናገረው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ስብከት አድርገዋል። ከክፉ ሁሉ ሊያወጣን ከሚመጣው ጌታ ጋር ስንገናኝ አሁን እየኖርንበት ካለው የስቃይ ሕይወቱ ውስጥ እና ቅራኔዎች ሁሉ እርሱ ነጻ ያወጣናል ብለዋል።

የዛሬ ህመም

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ድሆች በታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም የቆሰሉ እና የተጨቆኑት "በመከራ፣ በግፍ፣ በስቃይና በፍትህ እጦት ተለይተው ይታወቃሉ" በማለት "በፍፁም ከእነዚህ ነገሮች ለመውጣ አዳጋች በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ሆነው" ነፃነትን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የዛሬው የዓለም የድሆች ቀን በልዩ ሁኔታ ትኩረት እንድናደርግ ጥሪ ያቀርብልናል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ብዙውን ጊዜ ወደ ዚህ ሁኔታ የሚገቡት በፍትህ እጦት እና በእኩልነት ባለመስተናገዳቸው ምክንያት በመሆኑ “ተጠቅሞ የመጣል ባሕል ባዳበረው ማህበረሰብ” የተነሳ እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን የባሰ ነገር ከመከሰቱ በፊት “ለተጎጂዎች መከራ” ትኩረት እንድንሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የነገ ተስፋ

ይህ ሁኔታ ከሚፈጥረው መከራና ፍርሃት የተነሳ የተስፋ ብርሃን እንዳለ እና “የመዳንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ” እንደሚያመላክት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጠቁመው “ኢየሱስ ልባችንን ለተስፋ ሊከፍትልን ይፈልጋል” በማለት ከጭንቀትና ፍርሃት ነፃ እንድንወጣ ጥሪ አቅርበዋል። "የነገ ተስፋ ዛሬ በህመም መካከል ያብባል" ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የእግዚአብሔር መንግሥት "እንደ ዛፉ ቅጠሎች እያበበች እና ታሪክን ወደ ግብ እየመራች እስከ መጨረሻው ግጥሚያ ድረስ ይህ ተስፋ ዛሬ በቆሰለው ታሪካችን ውስጥ ይሠራል፣ ከጌታ ጋር" ፍፁም ነፃ የሚያወጣን ቀን እስኪደርስ ድረስ በተስፋ መጓዝ ይኖርብናል ብለዋል።

ምን እናድርግ?

ከስቃይና ከተስፋ አንጻር ይህን እውነታ በመመልከት ክርስቲያኖች የሚፈለጉት ምንድን ነው? በማለት በስብከታቸው የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "የዛሬን ህመም በመፈወስ የነገን ተስፋ መንከባከብ አለብን" ማለት ነው ብሏል። የክርስቲያን ተስፋ ነገ ይሻሻላል የሚል የዋህ ተስፋ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርን የድነት ተስፋ “ዛሬ፣ ነገ እና በየቀኑ ተጨባጭ በሆነ መልኩ የሚገለጽ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው ሕይወታችንን በተጨባጭ መልኩ እንድንኖር የሚያደርግ የተግባር ጥሪ ነው ብለዋል። ይህም ማለት ኢየሱስ የመረቀውን የፍቅር፣ የፍትህ እና የወንድማማችነት መንግሥትን ከዕለት ወደ ዕለት በተጨባጭ ምልክቶች መገንባት ማለት ነው ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን ይህም እውን ሊሆን የሚችለው የተቸገሩትን ሰዎች በቸልታ በማይመለከቱ ሰዎች ውስጥ ነው፣ የርኅራኄ ምስክሮች መሆን አለብን ሲል ገልጿል።

ተስፋን ማደራጀት አለብን

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለድሆች በጣም ቅርብ ለነበሩት ለሟቹ ጣሊያናዊ ጳጳስ ዶን ቶኒኖ ቤሎ “በተስፋ ልንረካ አንችልም፤ ተስፋን ማደራጀት አለብን" ተስፋችን በተጨባጭ መገለጽ ያለበት በውሳኔዎች፣ ስምሪት፣ ለፍትህ እና ለአብሮነት በመስራት፣ የድሆችን ስቃይ ለማቃለል ነው “ ብለው መናገራቸውን ያስታወሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተስፋ እውን መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።  ይህንን ተስፋ እውን ለማድረግ ድሆችን ለመርዳት ቤተክርስቲያን የምታደርገውን ጥረት በበጎ ፈቃደኝነት የሚረዱትን ሰዎች ሁሉ ቅዱስነታቸው አጋጣሚውን ተጠቅመው አመስግነዋል።

ተስፋ የሚለመልመው በእርጋታ ነው

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል (ማርቆስ 13፡24-32) ላይ እንደምናነበው የበለስ ቅጠሎች የሚለመልሙት ቅርንጫፎቹ ሲያድጉ እንደሆነ ሊቀ ጳጳሱ ገልጸው ይህ ቃል “ርኅራኄ” የሚለው ቃል “በዓለም ላይ ተስፋ እንዲያብብና የድሆችን ስቃይ የሚያቃልል” መሆኑን ገልጸዋል። ከራስ ወዳድነት እና ከውስጥ ግትርነት ወጥተን የአለምን ሰቆቃ ለመግታት በንቃት ልንሳተፍ እና ችግሩን ለማቃለል መስራት አለብን ብሏል። ለስላሳዎቹ የዛፍ ቅጠሎች በዙሪያችን ያለውን ብክለት እንዴት እንደሚስቡ እና "ወደ መልካምነት እንደሚቀይሩት" ያመለከቱት ቅዱስነታቸው ችግሮቹንና ተግዳሮቶቹን ከመወያየት ይልቅ ቅጠሎቹ እንደሚያደርጉት “ቆሻሻ አየር ወደ ንጹሕ አየር መለወጥ”፣ ክፉን በመልካም ምላሽ በመስጠት፣ “እንጀራን በጋራ በመቁረስ ክፉ ነገሮችን በመልካም የምንቀይር መሆን እንችል ዘንድ አንድ ነገር ማድረግ አለብን ያሉ ሲሆን ከተራቡት ጋር አብሮ የሚኖሩ፣ ለፍትህ እየሰሩ፣ ድሆችን ከፍ ከፍ በማድረግ ክብራቸው እንዲመለስ ማደረግ ይኖርብናል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በማጠቃለያው ላይ ቤተክርስቲያን ለድሆች ስትደርስ ምሥራቹን ለመስበክ እና ከእነሱ ጋር ስትሄድ፣ ከሥቃያቸው የተነሳ ተስፋ እንደሚፈጠር ለማሳየት ምን ያህል ውብ እና ትንቢታዊ እንደሆነች ጠቁመዋል። "ይህን የተስፋ አመለካከት ወደ ዓለማችን እናምጣ" በማለት ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠቃለዋል።

14 November 2021, 12:56