ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንትን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንትን በቫቲካን በተቀበሏቸው ጊዜ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንትን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰኞ ጥቅምት 15/2014 ዓ. ም የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ፍራንክ-ዎልተር ስቴንሜይርን በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ክቡር ፕሬዚደንት አቶ ፍራንክ-ዎልተር ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ከተገናኙ በኋላ፣ በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ተመርተው ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ከብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ጋርም መገናኘታቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አክሎ አስታውቋል።

ሁለቱ ወገኖች በአገር አቀፍ ደረጃ በጀርመን ውስጥ በሚስተዋሉ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ቀጥለውም ትኩረታቸውን በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በማድረግ በተለይም ስደትን፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግጭቶችን እና እነዚህ ግጭቶች ለመፍታት በሚያስችሉ የብዙ ወገኖች ቁርጠኝነት ላይ የጋራ ውይይት አካሂደዋል።

የጀርመን ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ፍራንክ-ዎልተር ስቴንሜይር ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል እና የሕይወት ዛፍ የሚል ስም የተሰጠውን ሥዕል ለቅዱስነታቸው በስጦታ አቅርበውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በበኩላቸው እ. አ. አ በ2021 ዓ. ም. ያስተላለፉትን የሰላም መልዕክት፣ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሰነድ፣ በመጋቢት 18/2012 ዓ. ም. ያቀረቡትን የመላው ዓለም የጸሎት ጉባኤ መዝጊያን የሚያብራራ መጽሐፍ እና በጀርመንኛ ቋንቋ የተብራራ የኖኅ ምስል ለጀርመኑ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ለክቡር አቶ ፍራንክ-ዎልተር ስቴንሜይር በስጦታ አቅርበውላቸዋል።

26 October 2021, 10:37