ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ነፃነት ከእግዚአብሔር ፍቅር የተገኘ እና በቸርነት ሥራ የሚያድግ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥቅምት 10/2014 ዓ. ም. ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ቅዱነታቸው በአስተምሮአቸው፣ ነፃነት ከእግዚአብሔር ፍቅር የተገኘ እና በቸርነት ሥራ የሚያድግ መሆኑን አስረድተዋል።

ክብራትና ክቡራን አድማጮቻችን፣ ከዚህ ቀጥሎ የቅዱስነታቸውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ ከእምነት አስጋራሚነት ጋር ያስተዋውቀናል። ምክንያቱም አንዳንድ የሕይወት ገጽታዎችን በማደሱ ብቻ ሳይሆን፣ በምስጢረ ጥምቀት ወደተቀበልነው አዲስ ሕይወት ስለሚመራን ነው። በምስጢረ ጥምቀት በኩል ከስጦታዎች ሁሉ በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት ስጦታ በእኛ ላይ ወርዷል። በኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና በመወለድ በትእዛዛት ከተመሠረተው ሃይማኖታዊነት ይልቅ ወደ ሕያው እምነት ተሸጋግረናል። ከእግዚአብሔር አባታችን፣ ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር ያለንን አንድነት ማዕከል ወዳደረገው ሕያው እምነት ተሸጋግረናል። ከፍርሃት እና ከኃጢአት ባርነት የእግዚአብሔር ልጆች ወደ መሆን ተሸጋግረናል።

በዛሬው ትምህርታችን በእምነት የሚገኝ ነጻነት ለሐዋርያው ጳውሎስ የሚሰጠው ዋና ትርጉም ምን እንደሆነ   የበለጠ ለመረዳት እንሞክራለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ነጻነት የሥጋን ምኞት መፈጸሚያ መሆን እንደሌለበት ይናገራል። ‘ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል እንጂ ይህ ነጻነታችሁ የሥጋን ምኞት መፈጸሚያ ምክንያት አይሁን።’ (ገላ. 5፡13)

ነፃነት ሲባል፣ ነፃነት ያለው የአኗኗር ዘይቤ አይደለም፤ በሥጋ ምኞት ወይም ተፈጥሮአዊ ፍላጎቶቻችንን የምንከተልበት መንገድ አይደለም፤ ወደ ግል ፍላጎቶች ወይም ወደ ራስ ወዳድነት እንድንገባ የሚያደርገን አይደለም። በተቃራኒው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ነፃነት እርስ በእርስ በመተጋገዝ “አንዳችን ለሌላው አገልጋዮች እንድንሆን የሚጋብዘን ነው” በማለት ይገልጸዋል። በሌላ አነጋገር፣ እውነተኛ ነጻነት በፍቅር በኩል በሙላት ይገለጻል። እንዲህ እንበል እንጂ ቅዱስ ወንጌል ከሚለው የተለየ ሆኖ እናገኘዋለ። ቅዱስ ወንጌል በማገልገል ነፃ እንወጣለን፣ እራሳችንን በምንሰጥበት መጠን ሙሉነት እናገኛለን፣ ሕየወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፣ ‘ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል።’ (ማር. 8፡35) 

ይህን ታዲያ እንዴት ማስረዳት ይቻላል? ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው መልስ በቀላሉ፣ “በፍቅር አማካይነት የሚል ነው” (ገላ. 5፡13) እኛን ነጻ ያደረገን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ነው። ለግል ብቻ ከሚል አስከፊ ባርነት ነጻ የሚያወጣን ፍቅር ነው። ስለዚህ ነጻነት የሚገኘው ወይም የሚያድገው ከፍቅር ጋር ነው። ነገር ግን ልብ ልንለው ይገባል። ይህ ፍቅር በልበ ወለድ ታሪክ ውስጥ እንደሚገለጽ ውስጣዊ ፍቅር፣ ወይም በምንፈልገው እና በምንወደው ነገር ላይ የሚኖረን ብርቱ ፍላጎት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያየነው የቸርነት ፍቅር ነው። በእውነት ነጻ የሚያወጣን ፍቅር ይህ ነው። ይህ ፍቅር በነጻ አገልግሎት አማካይነት የሚያበራ ፍቅር ነው። የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገለጸ ፍቅር ነው። ‘እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁት እናንተም እንድታደርጉት ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ።’ (ዮሐ. 13፡15)

ስለዚህ ለሐዋርያው ጳውሎስ ነጻነት ማለት “የሚፈልገውን ወይም የሚወደውን እንዲያደርግ” የሚፈቅድ ወይም መንገድ የሚከፍትለት አይደለም። እንዲህ ዓይነት መሠረት እና ትርጉም የሌለው ነጻነት ባዶ ነጻነት ነው። ይልቅስ ለውስጣዊ ባዶነት ያጋልጣል። ስንት ጊዜ ነው በውስጣዊ ስሜቶቻችን ብቻ ተመርተን በትልቅ ባዶነት ላይ የወደቅነው? ይህ የሚሆነው የነፃነታችንን ሀብት በመጠቀም ለራሳችን እና ለሌሎች ማበርከት የምንችለውን እውነተኛ መልካምነት መምረጥ ሳንችል ስንቀር እና በመልካም ሁኔታ መጠቀም ባለመቻላችን ምክንያት ነው። ከእውነተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር የሚገኝ ነፃነት ብቻ በተሟላ እና በእውነተኛ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ያኖረናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሌላ መልዕክቱ፣ የተሳሳተ ነጻነት ለሚደግፉ ሰዎች እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል። ሁሉ ነገር ተፈቅዶአል፤ ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም። ‘እያንዳንዱ ሰው የሌሎችንም ጥቅም ያስብ እንጂ የራሱን ጥቅም ብቻ አይመልከት።’ (1ኛ ቆሮ. 10፡23-24) የነጻነትን ትርጉም በሚመቻቸው ወይም በሚስማማቸው መንገድ መተርጎም ለሚፈልጉ ሰዎች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ትክክለኛውን የፍቅርን ትርጉም ያቀርብላቸዋል። እኛን እና ሌሎችን ነጻ የሚያወጣን፣ ሌሎችን ሳንጫን መደማመጥን እንድናውቅ የሚያደርግ፣ ሳያስገድድ ማፍቀርን የሚያውቅ፣ መገንባትን እንጂ ማፍረስን የማያውቅ፣ ለራስ ምቾት እና ጥቅም ሲል ሌሎችን የማይጨቁን እውነተኛ ነጻነት በፍቅር የሚመራ ነጻነት ብቻ ነው። በሌላ አገላለጽ ነጻነት መልካም አገልግሎትን ለማበርከት ያልቆመ ከሆነ፣ ፍሬን የማያፈራበት መካን የመሆን አደጋ ያጋጥመዋል። በሌላ በኩል በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው ፍቅር ወደ ድሆች በመምራት፣ ኢየሱስን ከፊት ገጽታቸው መመልከት እንድንችል ያግዘናል። ስለዚህ አንዱ ለሌላው የሚያበረክተው አገልግሎት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንደጻፈው፣ ሌላው ሁሉ ቀርቶ በቅድሚያ ሌሎች ሐዋርያት በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ስለ ነጻነት የተናገሩትን ትምህርት እንዲያተምር፣ ይህም ድሆችን ማስታወስ እንደሚገባ ያመለክታል። ‘በመካከላቸው ያሉትን ድሆች እንድናስታውስ አደራ አሉን፤ ይህም እኔ በትጋት ያደረግሁት ነገር ነው።’ (ገላ. 2፡10) 

ስለ ነጻነት ሲወራ በስፋት ከሚቀርቡ ዘመናዊ አስተሳሰቦች መካከል አንዱ ‘የእኔ ነጻነት የሚያልቀው ያንተ ነጻነት ሲጀምር ነው’ የሚል ነው። ነገር ግን እዚህ ላይ የእርስ በእርስ ግንኙነት ቦታ የለውም! ይህ የብቸኝነት አመለካከት ነው! በሌላ በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ ያመጣውን የነፃነት ስጦታ የተቀበሉት ሰዎች፣ ነፃነት ከሌሎች መራቅ እንዳለበት ፈጽሞ አያስቡትም። የሰው ልጅ ሁል ጊዜ የአንድ ማህበረሰብ አካል እንጂ በራሱ ብቻ ተወስኖ ወይም ተዘግቶ እንደሚቆይ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም። ማኅበራዊ ልኬት ለክርስቲያኖች መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የግል ጥቅምን ሳይሆን የጋራ ጥቅምን እንዲመለከቱ ያስችላቸዋል።

በተለይም በምንገኝበት በዚህ ታሪካዊ ዘመን፣ ብቸኝነትን ወይም ግለኝነትን ሳይሆን የማኅበራዊ ሕይወት ትርጉም እና የነፃነት ልኬትን እንደገና መገንዘብ አለብን። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አንዳችን ለሌላው እንደምናስፈልግ አስተምሮናል። ነገር ግን ይህ ማወቅ ብቻውን በቂ አይደለም። በየቀኑ በተጨባጭ የምንገልጽበትን መንገድ ማወቅ አለብን። ሌሎች በእኔ ነፃነት ላይ እንቅፋት አለመሆናቸውን በማመን፣ ይልቁንም ነጻነትን ሙሉ በሙሉ መገንዘብ እንድንችል ዕድል መክፈታቸውን እንወቅ። ምክንያቱም ነፃነታችን ከእግዚአብሔር ፍቅር የተወለደ እና በቸርነት ሥራ የሚያድግ ነውና።”

20 October 2021, 16:42