ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በፍጹም ልባችን ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥቅምት 14/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ለዕለቱ በተመደበው በማር. 10፡ 46-52 በተነበበው ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባቀረቡት ስብከት በፍጹም ልባችን በድፍረት ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ክቡራትና ክቡራን አድማጮቻችን፣ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን ያቀረቡትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አቅርበነዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከማር. 10፡ 46-52 ተወስዶ የተነበበው የዛሬው ቅዱስ ወንጌል፣ ኢየሱስ ከኢያሪኮ ከተማ ሲወጣ በርጤሜዎስ የተባለ ለማኝ ዓይነ ስውርን እንዳዳነው ይተርካል። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ከመግባቱ አስቀድሞ ያደረገው ግንኙነት ነው። በርጤሜዎስ ያጣው ዓይኑን እንጂ ድምጹን አልነበረም። በመንገድ ዳር ተቀምጦ ምጽዋዕት ሲለምን በነበረበት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደምያልፍ በሰማ ጊዜ፥ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ! እባክህ ራራልኝ” እያለ ደጋግሞ ይጮህ ጀመር። በጩሄቱ ያልተደሰቱ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እና ሕዝቡ ጸጥ ለማሰኘት ጥረት አደረጉ። ነገር ግን ዓይነ ስውሩ በርጤሜዎስ ድምጹን ይበልጥ ከፍ አድርጎ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ! እባክህ ራራልኝ” እያለ ይጮህ ጀመር። ኢየሱስም ይህን ሲሰማ ቶሎ ብሎ ቆመ። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ የድሆችን ጩኸት ይሰማል እና በበርጤሜዎስ ድምጽ ምንም አልተረበሸም። በሰዎች እየተነቀፈ ዕርዳታ ባያገኝም የእግዚአብሔርን የልብ ደጅ ለማንኳኳት ፍርሃት በማይሰማው እምነት የተሞላ መሆኑን ኢየሱስ ተገነዘበ። ያደረገለት ተአምር መነሻም እዚህ ላይ ነው። “በል ሂድ እምነትህ አድኖሃል” አለው። (የማር. 10፡52)

የበርጤሜዎስን እምነት ካቀረበው ጸሎት ለማየት እንችላለን። ምንም ዓይነት ዓይናፋርነት የማይታይበት በድፍረት የተመላ ጸሎት ነበር። ከሁሉ በላይ “የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ!” በማለት ነበር ጸሎቱን ያቀረበው። ይህም፣ ኢየሱስ መሲህ መሆኑን እና ወደ ዓለም የሚመጣው ንጉሥ መሆኑን እንደሚያምን የገለጸበት ጸሎት ነበር። በድፍረትም “ኢየሱስ ሆይ!” በማለት ጠርቶታል። ኢየሱስን በመፍራት በሩቅ ቆሞ አልለመነውም። እናም፣ የነበረበትን ችግር በሙሉ ወዳጁ ለሆነው ለእግዚአብሔር “እባክህ ራራልኝ” በማለት በጩሄት ገለጸ። ለአላፊው አግዳሚው እንደሚያደርገው ቀለል ያለ ለውጥ እንዲደረግለት አልጠየቀም። ሁሉን ማድረግ ለሚችል አምላክ፣ ሁሉ ነገር እንዲደረግለት ነበር የጠየቀው። ለሌሎች ሰዎች በሚያቀርበው ልመና ቀለል ያሉ ችግሮቹን እንዲፈቱለት ነበር ይጠይቃቸው የነበረው። ሁሉን ማድረግ ለሚችል ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “እባክህ ራራልኝ!” በማለት ሁሉን ነገር እንዲያደርግለት ጠየቀው። እራሱን ወደ ኢየሱስ አቅርቦ በሕይወቱ የእግዚአብሔርን ምሕረትን እና ርኅራሄን ለማግኘት ብሎ ጠየቀው።

በርጤሜዎስ ብዙ ቃላትን አልተጠቀመም ነበር። ለእራሱ አስፈላጊ የሆነውን ነበር የተናገረው። በሰው ልጅ የማይቻለውን እና ሕይወቱ እንደገና ማበብ የሚችልበትን የእግዚአብሔር ፍቅር ነበር የጠየቀው። ለዚህም ነው ኢየሱስን ምጽዋት ያልጠየቀው። ነገር ግን ሁሉ ነገሩ በግልጽ እንዲታይ አደረገ፡- ዓይነ ስውርነቱ፣ ማየት ካለመቻሉ የተነሳ ስለሚደርስበት ስቃይ ተናገረ። ዓይነ ስውርነቱማ እጅግ ቀላል ከመሆኑ የተነሳ ካሉበት ችግሮች ጋር የሚቆጠር አልነበረም። ሌሎች ካባድ ቁስሎች፣ ውርደቶች፣ የተሰበሩ ህልሞች፣ ስህተቶች እና የልቡ ውስጥ ጸጸቶች ነበሩት። በርጤሜዎስ ከልቡ ነበር የለመነው። ልመናችንስ ምን ይመስላል? የእግዚአብሔርን ጸጋ በምንለምንበት ጊዜ፣ ታሪኮቻችንን፣ ቁስሎቻችንን፣ ውርደቶቻችንን፣ የተሰበሩ ሕልሞቻችንን፣ ስህተቶቻችንን እና ጸጸቶቻችንን እናካትታለ?

“የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ! እባክህ ራራልኝ” በማለት ዛሬ እኛም ይህን ጸሎት መድገም ይኖርብናል። “ጸሎቴ ምን ይመስላል?” ብለን ሁላችንም እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። በድፍረት የተሞላ ነው? የበርጤሜዎስን የመሰለ መልካም ሃሳብ ይዟል? ኢየሱስ በአጠገባችን ሲያልፍ ጸሎታችን እንዴት እንደሚይዘው ያውቃል? ወይስ በማስታውስበት ጊዜ ብቻ ሰላምታን በማቅረብ ይረካል? እነዚያ ጥቅምን ለማግኘት ብቻ የሚደረጉ ጸሎቶች ምንም አይረዱንም። ጸሎቴ “ግልጽ” ነው? ልቤን ወደ እግዚአብሔር ፊት የሚያቀርብ ነው? የግል ታሪኬን እና የሕይወት ተሞክሮዬን ወደ እግዚአብሔር ፊት አቀርባለሁ? ወይስ ሥርዓትን ለመፈጸም ብቻ ሲባል ከልብ ባለማስተዋል በስሜት ብቻ የሚደረግ ጸሎት ነው? ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። እምነት ሕያው በሚሆንበት ጊዜ ጸሎትም ከልብ የሚመነጭ ይሆናል። ትርፍ ነገርን የሚጠይቅ አይሆንም። ወይም ጊዜያዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚጨነቅ አይሆንም። ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ሁሉን ነገር መጠየቅ አለብን። ይህን መዘንጋት የለብንም። ሁለመናችንን በፊቱ አቅርበን ኢየሱስ ክርስቶስን ሁሉ ነገር መጠየቅ አለብን። ጸጋውን እና ደስታንም በልባችን ውስጥ ሊያፈስ ምንም ታህል ጊዜ አይወስድበትም። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በፍርሃት ተይዘን ፣ በስንፍና ወይም ባለማመናችን ከእርሱ ርቀን የምንገኘው እኛ ነን።

ከእኛ ውስጥ ብዙዎቻችን ጸሎት በምናቀርብበት ጊዜ እግዚአብሔር ተዓምራትን ማድረግ እንደሚችል አናምንም። አንድ ታሪክን አስታውሳለሁ። አባት የዘጠኝ አመት ሴት ልጁ አንድ ሌሊት እንኳ እንደማታድር ሆስፒታል ውስጥ ዶክተሮች ይነግሩታል። ይህ አባት አውቶብስ ይሳፈር እና በሰባ ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ቤተመቅደስ ይደርሳል። ወደ ሥፍራው ሲደርስ ቤተመቅደሱ ዝግ ሆኖ ያገኘዋል። ቢሆንም ወደ ቤተመቅደሱ በር ተጠግቶ “ጌታ ሆይ እባክህ አድናት! ነፍስ ስጣት!” እያለ ሌሊቱን በሙሉ ሲጸልይ ያድራል።  

ወደ እመቤታችንም ዘንድ ሲጸልይ፣ ከልቡም እያለቀሰ ወደ እግዚአብሔር እየጮኸ ሌሊቱን በሁሉ ሲጸልይ ያድራል። ጠዋት በንጋቱ ወደ ሆስፒታል ሲመለስ ሚስቱ ምርር ብላ ስታለቅስ ባገኛት ጊዜ፣ ልጁ እንደሞተችበት ያስባል። ነገር ግን ሚስቱ “ለማንም ግልጽ ባለሆነ ሁኔታ፣ ዶክተሮቹ ልጃችሁ ተፈውሳለች!” ማለታቸውን ትነግረዋለች። ሁሉን የጠየቀው የዚያ ሰው ጩኸት ሁሉን ነገር በሰጠው ጌታ ተሰሚነትን አገኘ። ይህ አፈ ታሪክ አይደለም። እኔ ራሴ በአንድ ሀገረ ስብከት ውስጥ አይቼዋለሁ። ሁሉን ሊሰጠን ወደሚችል እግዚአብሔር ዘንድ በምናቀርበው ጸሎት ውስጥ ይህ የመሰለ ድፍረት አለን? እንደ ታላቁ የጸሎት መምህር፣ እንደ ዓይነ ስውሩ በርጤሜዎስ፣ እግዚአብሔርን ሁሉን ነገር እንጠይቅ። በርጤሜዎስ በእውነተኛ፣ ጽኑ እና ደፋር እምነቱ ምሳሌ ይሁነን። በጸሎት የበረታች እመቤታችን ቅድስት ድንግል፣ በፍጹም ልባችን በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በእምነት መመለስን ታስተምረን።”

25 October 2021, 17:02