ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከሃንጋሪ የእምነት ተቋማት መሪዎች ጋር ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከሃንጋሪ የእምነት ተቋማት መሪዎች ጋር 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሃንጋሪ የእምነት ተቋማት መሪዎች የአንድነት መሠረት እንዲሆኑ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቡዳፔስት ላገኟቸው የክርስቲያኖች አንድነት ምክር ቤት እና የአይሁድ ማኅበረሰብ ተወካዮች ባደረጉት ንግግር ያለፈውን ዘመን በሚገባ በመመልከት ጠንካራ የአንድነት መሠረት በመሆን ዓለም ማበብ እንዲችል እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በሃንጋሪ ባደረጉት አጭር ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ከአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ምክር ቤት ተወካዮች እና ከአይሁድ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር መወያየታቸው ታውቋል። የእምነት ተቋማት ተወካዮች ንግግር ካዳመጡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አንድ ላይ መሰብሰባቸው የአንድነት ምልክት መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ወንድም እንደ እህት አይተዋቸው፣ በጋራ ጉዞአቸው በመታገዝ ሙሉ አንድነትን እንዲያመጡ በማለት ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን አስተላልፈዋል።

ለአይሁድ ማኅበረሰብ

“የእምነት አባታችን በሆነው በአብርሃም ውድ ወንድሞች” ላሏቸው ለአይሁድ እምነት ተወካዮች ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ላለፉት በርካታ ዓመታት በመካከላችን ልዩነት ፈጥሮ የቆየውን ግድግዳ ማፍረስ በመቻላችሁ ያለኝን አድናቆት እገልጻለህ” ብለዋል። ክርስቲያኖች እና አይሁዳዊያን አንዱ ሌላውን እንደ ባዕዳን ሳይሆን እንደ ወንድም እና እንደ እህት የሚተያዩ መሆናቸውን አስረድተው፣ ይህም በእግዚአብሔር የተቀደሰ የለውጥ ምልክት ነው ብለዋል። ይህ ለውጥ የጋራ ጉዞን በአዲስ መልክ እንድንጀምር የሚያስችል፣ ከቀድሞ ጥፋት ነጻ የሚያደርግ የአዲስ ሕይወት ምልክት ነው ብለዋል።

ሰንሰለታማ ድልድይ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለእምነት ተቋማት ተውካዮች ባደረጉት ንግግር፣ በሁለት የተከፈለውን የቡዳፔስት ከተማ የሚያገኛኝ የከተማው ሰንሰለታማ ድልድልይን ጠቅሰው፣ ይህ ድልድልይ ሁለቱን የከተማው ክፍሎች በማገናኘት አንድነትን የሚጠብቅ እንጂ የሚከፋፍል አለመሆኑን ተናግረዋል። በሐይማኖቶች መካከል ይህን የመሰለ ግንኙነት ሊኖር ይገባል ብለው፣ አንዱ ሌላውን ለመዋጥ በሚሞከርበት ጊዜ እኛ አንድነትን ከመገንባት ይልቅ እናፈርሳለን ብለዋል። የከተማው ድልድይ ሌላ ትምህርት ይሆነናል ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጠንካራ እና ረጅም ሰንሰለት በብዙ ነጠላ ቀለበቶች የተገናኘ መሆኑን አስረድተው፣ እኛም ብንሆን እያንዳንዳችን አንድነትን ለማሳደግ የምናበረከተው አስተዋጽኦ አንድነትን ያጠናክራል ብለዋል። አንዱ ሌላውን ለማወቅ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፣ ለአምጽ እና ለጥርጣሬ የተጋለጥን እንሆናለን ብለው፣ ድልድይ ሁል ጊዜ ለመገናኘት ያግዛል ብለዋል።

የዓለም ሃይማኖቶች ተወካዮች

በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የተሰበሰቡት የበርካታ ሐይማኖቶች ተወካዮች ሃላፊነት በሁሉ ሰው ዘንድ የሐይማኖት ነጻነት እንዲከበር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። በብዙ አመጾች ለተጎዳ ዓለማችን ነጻነትን ማምጣት፣ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳንን እና ሰላም ለማምጣት ጸጋ የተሰጣቸው ሰዎች ምስክርነት ነው ብለዋል።

ሚክሎስ ራድኖቲ

ሚክሎስ ራድኖቲ የተባለ ታላቅ የሃንጋሪ ገጣሚን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የጨለማ ዘመን በነበረው የናዚ ሥርዓት ወቅት በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ መታሰሩን ገልጸው፣ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ግጥሞችን ሲጽፍ መቆየቱን አስታውሰዋል። የዚህ ታዋቂ ገጣሚ ማስታወሻ ደብተር፣ የዘር ጭፍጨፋ የተካሄደባቸው አይሁዳዊያን ሕይወት ታሪክ በሚያብራሩ ግጥሞች እና በካምፖቹ የነበረው ቅዝቃዜ በፍቅር ወደ ሙቀት እንደተለወጠ፣ ጨለማም በእምነት ወደ ብርሃን እንደተለወጠ በሚገልጹ ግጥሞች የተሞላ መሆኑን አስታውሰዋል። 

ፍሬን ለማግኘት ከተፈለገ ሥሮች ሊኖሩ ይገባል

በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በነበረው ብቸኝነት ምክንያት ሕይወቱ እየደበዘዘ መምጣቱን የተገነዘበው አቶ ሚክሎስ በግጥሙ፣ እንደ አበባ ከማበቡ በፊት በአንድ ወቅት ሥር እንደነበር የገለጸበት ግጥሙን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እግዚአብሔርን እና ሌሎች ሰዎችን በማዳመጥ የምንታወቅ ከሆነ በዘመናችን ያሉ ሰዎች  በእንግድነት እንዲቀባበሉ እና እንዲዋደዱ ልንረዳቸው እንችላለን ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ላገኟቸው የክርስቲያኖች አንድነት ምክር ቤት እና የአይሁድ ማኅበረሰብ ተወካዮች ያደረጉትን ንግግር ባጠቃለሉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የሰላም ሥሮች እና የአንድነት ቡቃያዎች ከሆንን ፣ ተስፋን ማብቀል የምንችል ከመሆን በተጨማሪ፣ በጉጉት በሚመለከተን ዓለም ዘንድ ያለንን ተዓማኒነት ማረጋገጥ እንችላለን ብለዋል።

13 September 2021, 17:04