ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሜክሲኮ የጎርፍ አደጋ ተጠቂዎችን በጸሎታቸው አስታወሱ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትናንት እሑድ መስከረም 9/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፣ በሜክሲኮ ውስጥ ሂዳልጎ ክፍለ ግዛት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ያረፉትን እና ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች በተለይም በሆስፒታሉ ውስጥ በሕክምና ላይ እያሉ የሞቱትን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ተሰድደው በውጭ አገራት የሚገኙትን፣ በመከራ ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን እና በደል የሚደርስባቸውን በሙሉ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠውላቸዋል። ፍትህ በተገቢው መንገድ በፍጥነት ሲረጋገጥ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።    

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመቀጠልም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት የሮም እና አካባቢዋ ምዕመናን፣ ከፖላንድ፣ ከስሎቫኪያ እና ከሆንዱራስ ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ለልዩ ልዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት አባላት እንዲሁም ቤተሰቦች በቅርቡ በጣሊያን ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የቅዱስ ሜሮን ምስጢርን ለመቀበል ለሚዘጋጁ አዳጊ ወጣቶች እና ተማሪዎችም ሰላምታቸውን አቅርበዋል።

ቀጥለውም በፈረንሳይ ውስጥ ላ ሰሌቴ በተባለ አካባቢ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ለሁለት ሕጻናት በሐዘን እንባ የተገለጸችበትን 175 ዓመት በማክበር ላይ የሚገኙ ምዕመናን አስታውሰዋል። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሐዘን እንባ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኢየሩሳሌም ሰዎች ያፈሰሰውን እንባ እና በጌቴሴማኒ የደረሰበትን ሥቃይ የሚያስታውሰን መሆኑን ገልጸው፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ እኛን የእግዚአብሔር ምሕረት ተካፋዮች ለማድረግ መሆኑንም አስታውሰዋል።

በመጨረሻም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን፣ አገር ጎብኝዎች እና ለእጅግ ንጽሕት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች መልካም ዕለተ ሰንበትን ተመኝተው፣ ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት የዕለቱን ስብከታቸውን አጠቃልለዋል።  

20 September 2021, 17:04