ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል ፊት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል ፊት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ማርያም የተዘነጉትን እንድናዳምጥ ታስተምረናለች አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሮም ከጳጉሜ 3/2013 - መስከረም 1/2014 ዓ. ም. በአውታረ መረብ አማካይነት በመካሄድ ላይ ላለው 25ኛው ዓለም አቀፍ ሥነ-ማርያማዊ ጉባኤ መልዕክት ልከዋል። በመልዕክታቸው፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት ማርያም በሰፊው ዓለማችን ወንድማማችነት እንዲያድግ ታግዘናለች ብለው፣ በማኅበረሰቡ መካከል የተዘነጉትንም እንድናዳምጣቸው ታስተምረናለች ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ቅድስት ድንግል ማርያም በሰዎች መካከል ልዩነት የማታደርግ፣ የሁላችን እናት ናት” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ይህም “መከፋፈልን ሊፈጥሩ የሚችሉ መሰናክሎችን ማሸነፍ ለሚችል ባህል የማጣቀሻ ነጥብ ነው” በማለት አስረድተዋል። በማከልም “በወንድማማችነት ጉዞ ላይ፣ የመጽናናት ምልክት ያለበትን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሴትነት፣ የደቀ መዝሙርነት፣ የእናትነት፣ የጓደኝነት መልክ እና ልብ እርግጠኛ ተስፋን እንደገና እንድንቀበል መንፈስ ቅዱስ ይጠራናል” ብለዋል።

ከዓለም “ማሪዮሎጂስቶች” እና ምሁራን ጉባኤውን ተካፍለዋል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ፣ 25ኛውን ዓለም አቀፍ ሥነ-ማርያማዊ ጉባኤ ለሚካፈሉት፣ ከመላው ዓለም ለተወጣጡት 300 “ማሪዮሎጂስቶች” እና ምሁራን መልዕክት የላኩ ሲሆን፣ “ማርያም በሥነ-መለኮት እና በባህሎች መካከል፥ ሞዴሎች ፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶች እና አመለካከቶች” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ጉባኤን ያስተባበረው፣ በጳጳሳዊ አካዳሚ ውስጥ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ማርያማዊ የጥናት ማዕከል መሆኑ ታውቋል። በቪዲዮ ምስል አማካይነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን ይህን ጉባኤው በበላይነት የመሩት ብጹዕ ካርዲናል ጃን ፍራንኮ ራቫዚ በቅድስት መንበር የባሕል ጉዳይ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት መሆናቸው ታውቋል።

“ማርያም የስዎችን ጩኸት ታዳምጣለች”

ጉባኤው በአቀራረቡ የመጀመሪያ መሆኑን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የተካፋዮችን ደስታ እንደሚጋሩ ገልጸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተባባሰበት ባሁኑ ወቅት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወንድሞች እና እህቶች ጩኸት መርሳት እንደማይገባ አሳስበዋል። “እውነተኛ ደስታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣው ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ አብረን የተሻለ የወደፊት ሕይወት መገንባት ስለምንችል፣ ሁል ጊዜ በማኅበረሰቡ ዘንድ ለተዘነጉ ሰዎች ድምፅ ቦታ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል። ውብ በሆነው የወንጌል አገልግሎት፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰው ልጅ እና ለምድራችን የጋራ ጥቅም በምናቀርበው አገልግሎት ውስጥ በማኅበረሰቡ መካከል የተዘነጉትን ሰዎች ማዳመጥ እንድንችል፣ እሷ ራሷ የድምፅ አልባዎች ድምጽ በመሆን ታስተምረናለች ብለዋል።

በጳጳሳዊ አካዳሚ፣ የዓለም አቀፍ ማርያማዊ ጥናት ማዕከል ተግባር

ጳጳሳዊ ዓለም አቀፍ ማርያማዊ አካዳሚ ከ60 ዓመታት በላይ የማስተማር አገልግሎቱ፣ ቅድስት ማርያምን በተመለከተ ጥልቅ ግንዛቤዎችን ፣ ሀሳቦችን እና ፍንጮችን ሲያበረክት መቆየቱን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አስታውሰው፣ ታኅሳስ 4/2019 (እ. አ. አ.) ለአካዳሚው በላኩት መልዕክት፣ በምንገኝበት ተለዋዋጭ ዘመን የ “ማርዮሎጂ” ጥናት በባህሎች መካከል ውይይት እንዲኖሩ በማድረግ ወንድማማችነትን እና ሰላምን ማሳደግ የሚችል ጠቃሚ መድረክ መፍጠሩን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ ጳጳሳዊ አካዳሚው ከጊዜ ወደ ለውጦችን ለማሳየት የሚያደርገውን ጥረት በማጥበቅ፣ የዘመኑን ምልክቶችን በሚገባ በመረዳት፣ ለቤተክርስቲያን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ጥቅም ሲል የሚያቀርበውን አገልግሎት በቁርጠኝነት በጽናት መቀጠል እንዳለበት አደራ ብለዋል።

ቃል ሥጋን የመልበስ ምስጢር

የቀድሞ ር. ሊ. ጳ በነዲክቶስ 16ኛ አስተምህሮን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “የማርያም ስብዕና የያዘው ምስጢር፣ በሥጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ቃል ምስጢር ነው” ብለው፣ ይህም እግዚአብሔርን መምሰል የሚታይበት እና በትክክል ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የሚያቀርብ ቃል መሆኑን አስረድተዋል።

09 September 2021, 17:49