ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ተስፋችን እውን የሚሆነው አንድነትን አሳድገን በኅብረት ስንኖር ነው።”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለቱ የመካከለኛው አውሮፓ አገሮች በሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ከመስከረም 2 – 5/2014 ዓ. ም ድረስ 34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ጉብኝት የሚያስታውስ ንግግር አድርገዋል። በዚህ ንግግራቸው “ተስፋችን እውን እና ተጨባጭ ሊሆን የሚችለው አንድነታችንን አሳድገን በኅብረት ስንኖር ነው” ብለዋል።

ክብራትና ክቡራን አድማጮቻችን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያደረጉትን ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬ ዕለት በቡዳፔስት እና በስሎቫኪያ ስላደረግሁት ሐዋርያዊ ጉብኝት መናገር እፈልጋለሁ። በእነዚህ ሁለቱ አገሮች ያደረግሁት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከተጠናቀቀ እነሆ ዛሬ ረቡዕ አንድ ሳምንት ነው። ለሦስት ዓላማ የተደረገ ሲሆን እነርሱም፥ ለጸሎት የተደረገ ንግደት፣ ወደ ጥንታዊ የእምነት አባቶች አገር የተደረገ ንግደት እና የተስፋ ንግደት ነበር።

የዚህ ሐዋርያዊ ጉዞ የመጀመሪያ መዳረሻ ከተማ ቡዳፔስት ሲሆን ዓላማውም በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ከነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. እስከ እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም. ድረስ ሲካሄድ በቆየው 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመገኘት ነበር። ጉባኤው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት የተራዘመ ነበር። ከፍተኛ ተሳትፎ የታየበት ደማቅ ክብረ በዓል ነበር። የጌታችን ዕለት በሆነው እሑድ የተከበረው የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ ክብረ በዓል፣ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ሳያቋርጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያድግበትን እና ያደገበትን ምስጢር ለማክበር የተዘጋጀ ክብረ በዓል ነበር። የመስዋዕተ ቅዳሴውን ጸሎት የተካፈሉት ምዕመናን በመንበረ ታቦት ላይ በነበረው፣ ትሁት እና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ፣ ለሰዎች ሁሉ ለጋስ እና የከበረ ፍቅር ባለው፣ ከዓለማዊነት በሚያነጻ፣ ወደ እምነት መንገድ በሚመራ በቅዱስ መስቀል የታቀፉ ነበሩ።

ወደ ስሎቫኪያ ያደረግሁት የጸሎት ንግደት የተገባደደው በሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ክብረ በዓል ዕለት ነበር። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በሚገኝበት በሳስቲን ከተማ የተከበረው የሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ብሔራዊ ክብረ በዓልም እንደመሆኑ እጅግ በርካታ የእርሷ ልጆች የተካፈሉበት ክብረ በዓል ነበር። እኔም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በተከበረበት በአውሮፓ ልብ ያደረግሁትን ንግደት የጀመርኩት ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስግደትን በማቅረብ ቀጥሎም አምልኮን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ   ለማቅረብ ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝብ ይህን እንዲያደርግ የተጠራ ሲሆን፣ በተለይም አምልኮን፣ ጸሎትን፣ ንግደትን እና አድናቆትን በማቅረብ እና ንስሐን በመግባት እግዚአብሔር በሚሰጠው ሰላም እና ደስታ ለመሞላት ነው። ይህ መንፈሳዊ ተግባር የእግዚአብሔር መኖር በዕለታዊ ፍጆታ በተበረዘበት፣ ቀድሞ የነበረ የጋራ አስተሳሰብ ከአዲስ ርዕዮተ ዓለም ጋር በተደበላለቀበት የአውሮፓ አህጉር ውስጥ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው ነው። በዚህ አውድ ውስጥም እንዲሁ ፈዋሽ እና ፍቱን መልስ የሚመጣው ከጸሎት፣ ከምስክርነት እና በትህትና ከተሞላ ፍቅር ነው።

በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ከታማኝ ሕዝብ ጋር በመገናኘት ለእምነታቸው ሲሉ ከአረመኔዎች የሚፈጸም ስቃይ ከተቀበለው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በመገናኘት የተመለከትኩት እውነት ይህ ነው። ከአይሁድ እምነት ተከታይ ወንድሞች እና እህቶች ፊት የተረዳሁትም ይህን ነው። ከእነርሱ ጋር በአይሁዳውያን ላይ የደረሰውን አስከፊ የዘር ጭፍጨፋን በጋራ አስታውሰናል። ምክንያቱም ትዝታ የሌለበት ጸሎት የለምና።

የሐዋርያዊ ጉብኝቴ ሁለተኛው ዓላማ ከጥንታዊ የእምነት አባቶች ጋር መገናኘት ሲሆን፣ በሁለቱ አገሮች፣ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ እና በስሎቫኪያ ብራቲስላቫ ከተማ ውስጥ ወንድም ከሆኑ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር በመገናኘቴ፣ ምስጋና ያለበት የእምነት እና የክርስትና ሕይወት ትውስታን በቀጥታ ማግኘት ችያለሁ። ሕይወት ያለው የብጹዕ ካርዲናል ማይንሴንቲ፣ የብጹዕ ካርዲናል ኮሬክ እና የብጹዕ አቡነ ፓቬል ፒተር የእምነት ምስክርነቶችን ለመስማት ችያለሁ። ከእነዚህ ብጹዓን አባቶች የሰማኋቸው ምስክርነቶች እስከ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የሚደርሱ፣ ቅዱሳን ወንድሞች፣ ቅዱስ ሲረል እና ቅዱስ መቶዲዮስ ወደ አካባቢው በመጓዝ የወንጌል ምስክርነታቸውን በቋሚነት ማካሄዳቸውን የሚገልጽ ነበር። የእነዚህን ሐዋርያዊ አባቶች ጥንካሬ መገንዘብ የቻልኩት፣ በፕሬሶቭ ከተማ በቅዱስ መስቀል በዓል ላይ በቢዛንቲን ሥርዓት ባቀረብነው የመሥዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ነበር። በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ በቀረቡት መዝሙሮች ውስጥ በእምነታቸው ብዙ ሥቃዮችን የተቀበሉ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሰዎች ልብ መንቀጥቀጥ ይሰማኝ ነበር።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የእነዚህ አባቶች ጥንታዊ የእምነት ምስክርነቶች ሕያውነትን በተከታታይ ስናገር ነበር። ምስክርነቶቹ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተሞሉ በመሆናቸው በእንክብካቤ ተጠብቀው መቆየት አለባቸው። በሙዚዬም ውስጥ እንደተቀመጡ ዕቃዎች መሆን የለባቸውም። በርዕዮተ-ዓለማዊነት፣ ለስልጣን እና ለጥቅም ፍለጋ ዓላማ እና የግል ማንነትን ለማጠናከር መሆን ፈጽሞ የለበትም። እንዲህ የሚሆን ከሆነ ምስክርነቶችን ለጉዳት አሳልፎ በመስጠት ፍሬን እንዳሰጡ ይደረጋሉ ማለት ነው። ቅዱስ ሲረል እና ቅዱስ መቶዲዮስ መታሰቢያቸውን እንድናከብርላቸው የቀረቡ ሳይሆን ፣ የእምነት ምስክሮች በመሆናቸው እንድንመስላቸው የቀረቡ የእምነት ሞዴሎች ፣ የወንጌላዊነትን መንፈስ እና ዘዴውን እንዲሁም የማኅበራዊ ሕይወት ቁርጠኝነትን የምንማርባቸው የእምነት አባቶች ናቸው። ወደ እነዚህ የአውሮፓ ልብ ወደ ሆኑት ሁለቱ አገራት ባደረግሁት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ብዙ ጊዜ ስለ አውሮፓ ኅብረት አባቶች አስብ ነበር። መጓዝ ያለባቸውን መንገድ ተረድተው የኖሩ ፣ አያቶቻቸው የወደፊት ዋስትናቸው የሆኗቸው፣ ከእነርሱ ባገኙት ጥበብ በመበልጸግ የተስፋ ቅርንጫፎች ሊያድጉ ይችላሉ።

የሐዋርያዊ ጉብኝቴ ሦስተኛው ዓላማ የተስፋ ንግደት ነበር። ምን ጊዜም በማልረሳው በኮሺሴ ስታዲዬም ውስጥ በተደረገው ሥነ-ሥርዓት ላይ በወጣቶች ዓይን ውስጥ ታላቅ ተስፋ መኖሩን ተመልክቻለሁ። በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ይህን የመሰለ ታላቅ በዓል ማክበት እጅግ የሚያበረታታ ምልክት ነበር። ብዙ ወጣት ባለትዳሮች ከልጆቻቸው ጋር በመገኘታቸው አመሰግናለሁ። ለሕይወቷ ዋጋን በመስጠት ክብረ ንጽሕናዋን ከአመፅ የተከላከለችው የስሎቫክ ልጃገረድ፣ የብጽዕት ሐና ኮሌሳሮቫ ምስክርነት በተመሳሳይ መልኩ ጠንካራ እና ትንቢታዊ ነበር። አለመታደል ሆኖ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ከባድ ቁስል ሆኖ በቀጠለበት ባሁኑ ዘመን የሐና   ምስክርነት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አስፈላጊ ነው። ተስፋን በማድረግ ብቻ ለጎረቤቶቻቸው እንክብካቤን የሚያደርጉ እና የሚጨነቁላቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ተመልክቻለሁ። በብራቲስላቫ ከተማ በሚገኝ የቤተልሔም ማዕከል ውስጥ ቤት ለሌላቸው ድሆች መጠለያን በማዘጋጀት በጎ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙ የቅድስት ተሬዛ ሚሲዮናዊያን እህቶችን አስታውሳለሁ። በተጨማሪም የሮማ ማህበረሰብ ተብለው የሚታወቁ ድሆችን በወንድማማችነት ፍቅር በመቅረብ በየጎዳናው ላይ አብረዋቸው የሚሰሩትንም ሁሉ አስባለሁ። የሮማ ማህበረሰብ ተብለው ከሚጠሩ ድሆች ጋር በዓል ለማክበር መገኘት የወንጌል መዓዛ የሚሸትበት ነበር።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ይህ ተስፋ እውን እና ተጨባጭ ሊሆን የሚችለው “አብሮነት” በሚል ቃል ብቻ ሲገለጽ ነው። የዓለማችን ተስፋም እውን የሚሆነው አንድነታችንን በማሳደግ በኅብረት ስንኖር ነው።  በቡዳፔስት እና በስሎቫኪያ ውስጥ በቀረቡ ልዩ ልዩ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ ተካፋይ ሆነናል። ከአብያተ ክርስትያናት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር፣ ከአይሁድ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር፣ ከሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች ጋር እና ከአቅመ ደካማ ሰዎችም ጋር ተገናኝተናል። ተስፋችንም እውን የሚሆነው አብረን የምንኖር ከሆነ ነው።

ሐዋርያዊ ጉብኝቴን ከፈጸምኩ በኋላ በልቤ ውስጥ ያለውን ታላቅ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። በሁለቱም አገሮች ለሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ሲቪል ባለስልጣናት፣ ለሐዋርያዊ ጉብኝቴ ስኬታማነት ለተባበራችሁ፣ ለበርካታ በጎ ፈቃደኞች፣ በጸሎት ለረዳችሁኝ በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት የተዘሩት ዘሮች ጥሩ ፍሬን እንዲያፈሩ ተጨማሪ ጸሎቶችን እንድታቀርቡ አደራ እላለሁ።”    

22 September 2021, 16:36