ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስሎቫኪያን ተሰናብተው ወደ ሮም ተመልሰዋል።

በሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ያደረጉትን 34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉኝታቸውን የፈጸሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የዚህ ጉብኝታቸው የመጨረሻ የሆነችውን ስሎቫኪያ ከመሰናበታቸው በፊት ለአገሩ ሕዝብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ መስከረም 5/2014 ዓ. ም በስሎቫኪያ ሳስቲን ከተማ ካከበሩት ዓመታዊ የሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ከፈጸሙ በኋላ ወደ ሮም መመለሳቸው ታውቋል። ከአገሩ ምዕመናን ጋር በሕብረት ለማክበር እጅግ ከተመኙት ከዚህ ታላቅ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በተጨማሪ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሌላው ዓላማ፣  በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የተካሄደውን 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴን መምራት መሆኑ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ትናንት ከሰዓት በፊት በሳስቲን ከተማ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ለምዕመናኑ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በስሎቫኪያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መፈጸማቸውን አስታውቀው፣

በሕብረት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የአገሩን ወጣቶች ጨምሮ ከመላው ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር የስሎቫኪያ ባልደረባ በሆነች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ለረዳቸው እግዚአብሔር ምስጋና ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ቀጥለውም ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ፍሬያማ እንዲሆን ብጹዓን ጳጳሳት ላደረጉት ዝግጅት እና ለመልካም አቀባበላቸው ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ለአገሪቱ ፕሬዚደንት እና ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲሁም ለሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በገሩ ቋንቋ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ከሰዓት በኋላ በአገሪቱ ዋና ከተማ ብራትስላቫ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በነበረው ሥነ-ሥርዓት ላይ የስሎቫኪያ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ክብርት ዙዛና ካፑቶቫ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ጋር ሆነው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደማቅ ሽኝት አድርገውላቸዋል። 

 

16 September 2021, 16:36