ፈልግ

የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለድሆች የምግብ፣ የጤና እና የኑሮ ሁኔታ አማራጮች እንዲረጋገጡላቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ መስከረም 17/2014 ዓ. ም. በቫቲካን ከተገናኟቸው የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ስብሰባ ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፣ ለድሆች የምግብ፣ የጤና እና የኑሮ ሁኔታ አማራጮች እንዲረጋገጡላቸው አሳስበዋል። የስብሰባው መወያያ ርዕስ “የህዝብ ጤና በዓለም አቀፍ እይታ” የሚል መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሕዝቦች መካከል በሚታይ ከፍተኛ የጤና እና የኑሮ ሁኔታ አለመመጣጠን ምክንያት የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በዓለም ዙሪያ ለሰው ልጅ የሚቀርብ የጤና እንክብካቤ እና የኑሮ ደረጃ ተመሳሳይ አለመሆኑን ገልጸው፣ የድሆችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ሕይወት መለወጥ የሚችሉ አማራጮችን በመጠቀም የበቂ ምግብ፣ የጤና እንክብካቤ እና የኑሮ ደረጃቸው እንዲሻሻልላቸው አሳስበዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ የምድራችን ስቃይ እና የድሆችን ጩሄት የበለጠ እንዲጎላ ማድረጉን አስታውሰው፣ ይህ በሆነበት ባሁኑ ጊዜ እንዳልሰማ ከመሆን ይልቅ ልናዳምጣቸው እንደሚገባ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ከመስከረም 17-18/2014 ዓ. ም “የህዝብ ጤና በዓለም አቀፍ እይታ” በሚል ርዕስ ሥር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ፣ የሕክምና እና የባዮሎጂ ምርምር ሥነ-ምግባርን እና የዓለማችን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታን የሚመለከት የሁለት ቀናት ውይይት መካሄዱ ታውቋል። የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ባዘጋጀው የበይነ መረብ ላይ አውደ ጥናት ወደ 100 የሚጠጉ አባላት መካፈላቸው ታውቋል።

የምድራችንን እና የድሆችን ጩሄት ማድመጥ

ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ በርካታ ውይይቶች መካሄዳቸው ቢታወቅም ሳይሰለቹ፣ ወደ ፊት የተሻለ ሕይወት ለመገንባት በሚያስችሉ ርዕሠ ጉዳዮችን በእርጋታ መመልከት እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። እውነተኛ እና ትክክለኛ ለውጦችን ማምጣት ከተፈለገ በዙሪያችን የሚታዩ ክስተቶች በጥንቃቄ በማጤን፣ ከችግሮች ለመውጣት በሚያስችሉ ተጨባጭ ውሳኔዎች ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

እርስ በእርስ መገናኘት ጥምረትን ይጠይቃል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ በህዝብ ጤና እና በዓለም አቀፍ ሥነ-ምግባር ዕድገት ላይ የሚያደርገውን ጥረት ደግፈው፣ አስፈላጊ በሆኑ ሰብዓዊ ቤተሰብ ግንባታ እና በአብሮ መኖር ገጽታዎች ላይ እንድናተኩር ያስችለናል ካሉ በኋላ፣ እነዚህም ሁላችንም ወንድማማቾች ነን የሚለው የሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ማዕከላዊ ጭብጦች መሆናቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሰው ልጅ በጋራ መኖሪያ ምድሩ ውስጥ የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው በግልጽ አሳይቶናል ብለዋል። የአንድነት እንቅፋቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተለያዩ የትምህርት እና የጥናት ዘርፎች መካከል፣ እነርሱም በስነ-ሕይወት እና በንጽህና አጠባበቅ፣ በመድኃኒት አቅርቦት እና በበሽታዎች መቆጣጠሪያ መርሃ ግብር፣ በስነ-ምጣኔያዊ አስተዳደር እና በማኅበረሰብ ሳይንስ፣ በማኅበረሰብ እና በባሕል እድገት ጥናት እና በስነ-ምሕዳር ሳይንስ መካከል የጠበቀ ግንኙነት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህ በተጨማሪ በጤና ሥርዓቶች፣ በቤተሰብ ሕይወት፣ በሥራ ዕድል እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ ቴክኖሎጂያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ስነ-ምግባራዊ መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የጥናት እና የትምህርት ዘርፎች ጥምረት በተለይ በጤና አጠባበቅ ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት፣ ምክንያቱም የጤና እንክብካቤ እና የበሽታ ቁጥጥር የሚወሰነው በተፈጥሮ ሂደቶች ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ሕይወት ጭምር መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። በሰዎች ቸልተኝነት የተነሳ በርካታ ከባድ ችግሮች ተዘንግተዋል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በጤና አጠባበቅ ዙሪያ በሚታዩ ድክመቶች ፈወስ ሊገኝላቸው የሚችሉ የወባ እና የሳንባ ነቀርሳ ሕመሞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት የዳረጋቸው መሆኑን አስታውሰዋል። እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተሰጠው ትኩረት ያህል አልተሰጠም ብለዋል።

የሰዎች የኑሮ አለመመጣጠን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ለተወሰዱት እርምጃዎች ምስጋናቸውን አቅርበው፣ እስካሁን ሃላፊነት ያልወሰድባቸው ሌሎች ከባድ ችግሮች ማለትም የክትባት ፣ የመጠጥ ውሃ እና የምግብ እጥረቶች ተጠያቂዎች ሊያደርገን ይገባል ብለዋል። የጤና አጥባበቅ ሥርዓቶችን በልዩ ልዩ አቅጣጫዎች የተመለከቱት ቅዱስነታቸው፣ የሰዎች የኑሮ ሁኔታ በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ውሳኔዎች እና አማራጮች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተው፣ እነዚህ ውሳኔዎች በሰዎች የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ላይም ወሳኝ ሚናን የሚጫወቱ መሆኑን አስገንዝበዋል። በተለያዩ አገሮች ውስጥ የዕድሜ ባለጠግነት እና ጤናማ ሕይወት የማግኘት ዕድልን በተመለከተ ከፍተኛ አለመመጣጠን መኖሩን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ ይህ የሚወሰነው በደመወዝ ደረጃ ፣ በትምህርት ብቃት እና በሚኖሩበት መንደር መሆኑን አስረድተዋል። የሰው ልጅ የማይገሰስ ሰብዓዊ ክብር፣ የኑሮ አለመመጣጠንን የምናሸንፍበት ተገቢ ቁርጠኝነት እና ውሳኔ እንድናደርግ ይጠይቃል ብለው፣ አለበለዚያ ሁሉም ሕይወት እኩል አይደለም፣ ወይም የጤና እንክብካቤ ለሁሉም በተመሳሳይ መንገድ አልተዳረሰም የሚለውን አሳዛኝ እውነታን ተቀብለን ለመኖር ያስገድደናል ብለዋል።

ውርጃ እና ኤውታናሲያ - አስከፊ ባህል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጋራ ግብ፣ በተለይም የዓለማችን ነዋሪዎች የጤና አጠባበቅ ሥርዓትን ለማሻሻል እና ጥራቱን ለማሳደግ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መደገፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በዚህ ረገድ የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ በበኩሉ ጠቃሚ አስተዋፅኦን ሊያበረክት እንደሚችል  አስርድተዋል።

በውርጃ አማካይነት ነፍስን የሚገድል አስከፊ ባሕል መኖሩን ቅዱስነታቸው አስታውቀው፣ ይህ ባሕል በአሁኑ ጊዜ እየተለመደ መምጣቱን አስታውሰዋል። “ማኅበራዊ ችግሮችን ለማቃለል የሰውን ሕይወት ማጥፋቱ ተገቢ ነው ወይ?” ብለው በመጠየቅ ውርጃ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ አስረድተዋል። ማኅበራዊ እና ቤተሰባዊ እንክብካቤ የሚያንሳቸው በርካታ አረጋዊያን መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ አረጋዊያን በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የጥበብ መሠረቶች በመሆናቸው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል  ብለዋል። የአረጋውያንን ዕድሜ የሚያሳጥር “የተደበቀ” የዩታናሲያ ሕግን በጥብቅ አውግዘው፣ የካቶሊክ ምሁራን ፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሆስፒታሎች ይህን ከንቱ እና አስከፊ ባሕል መከተል የማይችሉ መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ተናግረዋል።

28 September 2021, 17:08