የጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ የጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የእግዚአብሔርን ፍጥረት መንከባከብ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከብጹዕ ወ ቅዱስ ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ከካንተርበሪው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ ጋር በኅብረት ይፋ ባደረጉት መልዕክት፣ የእግዚአብሔርን ፍጥረት ለመንከባከብ ቁርጠኝነት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ የጋራ መልዕክታቸው፣ ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለአካባቢያዊ ውድመት የጋራ ምላሻችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስርድተው፣ የአጭር ጊዜ ጥቅሞች ለማረጋግጥ ከመተባበር ይልቅ ዘላቂነት ያለውን ትኩረት መስጠት አስፈላጊነት መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አስከፊ ውጤት መመልከታቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ አደጋው ድሃን ከሃብታም ሳይለይ፣ ደካማን ከጠንካራ ሳይለይ፣ በሁሉም ላይ ጉዳትን አስከትሏል ብለዋል። አንዳንዶች ወረርሽኙን ለመከላል በመጠኑም ቢሆን የመከላከል አቅም ቢያገኙም። ሌሎች ደግሞ ክፉኛ ቢጎዱም፣ በዓለማችን ውስጥ በፍጥነት የተዛመተውን ቫይሬስ ለመከላከል የተደረገው ጥረት፣ የእርስ በእርስ መደጋገ አስፈላጊነት አስተምሮናል ብለዋል።

እነዚህን ምልከታዎች ይፋ የሆኑት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ከካንተርበሪው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ፣ ከብጹዕ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ ጋር ነሐሴ 26/2013 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት የጋራ መልዕክት መሆኑ ታውቋል። የሐይማኖት መሪዎቹ በመልዕክታቸው በዚህ ዓለም አቀፋዊ ጥፋት መካከል፣ የሁሉ ሰው ሕይወት ደህንነት ካልተረጋገጠ በቀር ማንም ሰው ተነጥሎ የራሱን ሕይወት ብቻ ማዳን እንደማይችል አስረድተው፣ በዚህም መሠረት የአንዳችን ድርጊት በሌላው ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እናዳለው እና ዛሬ የምናከናውነው ተግባር ነገ በሚሆነው ነገር ላይ የራሱ ፋይዳ እንዳለው አስርድተዋል።

ሕይወትን መምርጥ

የሐይማኖት መሪዎቹ የጋራ መልዕክት ይፋ የሆነው፣ ከነሐሴ 26/2013 - መስከረም 24/2014 ዓ. ም. በሚቆየው በፍጥረት መታሰቢያ ወቅት መሆኑ ታውቋል። ወቅቱ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳተፍ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን በሕብረት እንዲጸልዩ ዕድል ለመስጠት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኅዳር ወር 2014 ዓ. ም. በስኮትላንድ ግላስጎ የወደ ፊት የጋራ ምድራችን ዕድልን አስመልከተው ለሚያካሂዱት ጉባኤ በሚዘጋጁበት ወቅት መሆኑ ታውቋል። ለሚቀጥለው ትውልድ የምናስረክበው ዓለም ምን መምሰል እንዳለበት ጊዜ ሳይባክን መወሰን እንደሚያስፈልግ የሚያሳስበው የሐይማኖት መሪዎች መልዕክት፣ የኑሮ ወጋችንን መለወጥ እና ሕይወት መምረጥ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። ከኦሪት ዘዳግም ምዕ. 30:19 “እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤” የሚለውን ጥቅስ በመምረጥ፣ ይህም የእምነት ወይም የአስተሳሰብ ልዩነቶችን ሳንመለከት ሁላችንም “የምድራችንን እና የሕዝቦችን ጩኸት ለማዳመጥ እና፣  እግዚአብሔር ለሰጠን ምድር ትርጉም ያለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ቃል እንድንገባ” ይጋብዘናል ብለዋል።

ከአጭር ጊዜ ጥቅም ይልቅ ዘላቂነት ያለው

ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ መረጋጋትን ማረጋገጥ የሚቻለው “ከእግዚአብሔር ለተቀበልናቸው ስጦታዎች የግል እና የጋራ ኃላፊነት ሊኖር ያገባል” በማለት የሃይማኖት መሪዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በክርስትና ባሕል፣ በቅዱሳት መጽሐፍት ሆነ ቅዱሳን፣ የአሁኑን እና መጪውን ጊዜ በማመዛዘን “አሁን ከምናየው ይልቅ የበለጠ ተስፋን የሚሰጥ ነገር ወደ ፊት” መኖሩን እንደሚያስረዱ የገለጹት የሐይማኖት መሪዎቹ፣ በሉቃ. 12. 13-21 ላይ የተገለጸውን “የሃብታሙ ሰው ሞኝነት” እንደዚሁም በሉቃ. 15. 11-32 ላይ የተገለጸውን “ጠፍቶ የተገኘው ልጅ” ምሳሌን ጠቅሰው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገኝ ጥቅም ከመቀበል ይልቅ ፣ ርካሽ የሚመስሉ አማራጮችን ከመቀበል መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል፣ የሐይማኖት መሪዎቹ።

በድሆች ላይ ያልተመጣጠነ ጉዳት ደርሷል

በዓለማችን ውስጥ የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሃ ሕይወት መጥፋትን እና የአከባቢ መራቆትን ማስከተሉን ያስታወሱት የሐይማኖት መሪዎች፣ “ይህ ሊከሰት የቻለው ዓለማች ሊቋቋም ከሚችለው በላይ የምድርን ሃብቶች በስግብግብነት ስለበዘበዝን” ነው ብለዋል። ጥልቅ ኢፍትሃዊነት መኖሩንም ገልጸው፣ የእነዚህን ጥሰቶች አስከፊ መዘዝ የሚሸከመው የዓለማችን ድሃ ማኅበረሰብ መሆኑን አስረድተዋል። የአየር ንብረት ለውጡ “የወደፊት ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን አስቸኳይ የህልውና ጉዳይ” መሆኑን በቅርብ ወራት ውስጥ የታየው የአየር ለውጥ እና ያስከተለው የተፈጥሮ አደጋ ግልፅ ያደርገዋል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪም “የጎርፍ አደጋ፣ የደን ቃጠሎ እና ድርቅ ማህበረሰቦች ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወሩ አስገድዷቸዋል ብለው፣ ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች በርካታ የዓለማችንን ክልሎች እንዳጠፉ፣ የውሃ እና የምግብ ዋስትና እጦት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ግጭትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።

መጪው ትውልድ አልተረፈም

“መጪው ጊዜ የከፋ ይሆናል” ያሉት የሐይማኖት መሪዎቹ ምድራችንን ከጥፋት ለማዳን “ከእግዚአብሔር ጋር ተባብሮ መሥራት” ያስፈልጋል ብለው፣ ኃላፊነትን ወስዶ አሁን ተግባራዊ የማያደርጉ ከሆነ የዛሬው ትውልድ እና ዓለማችን ለአስከፊ መዘዞች መጋለጡን አስረድተዋል። የሐይማኖት መሪዎቹ አክለውም፣ “ትውልዳችን በፈጸመው ኃጢአት ንስሐ እንገባለን ብለው፣ እግዚአብሔር ከሰጠን ተስፋ ጋር የሚስማማ ጸሎት ለማቅረብ እና ቁርጠኛ እርምጃን ለመውሰድ በዓለም ዙሪያ ካሉ እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን ጎን እንቆማለን።

ለውጥን ለማምጣት መተባበር ያስፈልጋል

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭነታችንን እና የሥርዓቶቻችን ደካማነት ግልጽ ማድረጉን የገለጹት የሐይማኖት መሪዎቹ፣ ያጋጠመውን ችግር ምርጫዎችን ያስቀምጥልናል ብለው፣ ምርጫዎቹም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ መሆን ወይም አደጋዎችን ለመከላከል የሚያግዙ ዕድሎችን በመጠቀም  ወደ ለውጥ እና ወደ ዕድገት መሻገር ነው ብለዋል። ይህን ለማድረግ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀማችን ላይ የግል ሃላፊነትን የሚያካትቱ ለውጦችን ማድረግን እንደሚያስፈልግ፣ እንዲሁም “ፍጥረትን ለመንከባከብ በገባነው ቁርጠኝነት በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መካከል የቅርብ ትብብር” እና በሕዝቦች መካከል ያሉትን ባህላዊ መሰናክሎች ማፍረስ ፣ የተፈጥሮ ሃብቶች ለመቀራመት የሚደረጉ ውድድሮችን ማቆም እና  አዲስ የሥራ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል።

ለክርስቲያኖች በሙሉ የቀረበ ጥሪ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ከብጹዕ ወ ቅዱስ ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ እና ከካንተርበሪው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ጃስቲን ዌልቢ ጋር በኅብረት ሆነው ለመላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ ባቀረቡት የጋራ ጥሪ፣ እያንድንዱ አማኝ እና መልካም ፈቃድ ያለው ሁሉ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለአካባቢ ብክለት ስጋት የጋራ ምላሽን ለመስጠት ሃላፊነትን ወስዶ ሚና መጫወት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በህዳር ወር 2014 ዓ. ም ያዘጋጀውን ጉባኤ ለሚሳተፉ የዓለም መሪዎች በሙሉ ጸሎታቸውን አቅርበው፣ “ህይወትን መምረጥ ማለት መስዋዕትነትን መክፈል እና ራስን መግዛትን መለማመድ ነው” ብለዋል። “ዘላቂነት ያለውን ጥረት ማድረግ በድህነት ላይ ተጽዕኖን እንደሚፈጥር እና ለዚህም ዓለም አቀፍ ትብብር የሚያስፈልግ መሆኑን አስርድተዋል።

ይህን መልዕክት በጋራ ለማቅረብ የተገደዱበት የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጹት ሦስቱ የሐይማኖት መሪዎቹ፣ “የእግዚአብሔርን ፍጥረት መንከባከብ ቁርጠኝነት ያለበት መልስ የሚጠይቅ መንፈሳዊ ተልዕኮ ነው” ብለው፣ አሁን የምንገኝበት ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ እና የጋራ መኖሪያ ምድራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት ወሳኝ ጊዜ ነው” ብለዋል።

08 September 2021, 16:35