ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለጸሎት ወደ ቡዳፔስት እና ስሎቫኪያ እንደሚሄዱ አስታወቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሁድ ነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፣ በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ከነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. እስከ እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም. ድረስ በሚካሄደው 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመገኘት ወደ ቡዳፔስት እንደሚጓዙ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቡዳፔስት ከተማ የሚቀርበውን የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመሩ በኋላ ለጥቂት ቀናት በስሎቫኪያ ወደሚገኝ የሐዘንተኛይቱ ማርያም ቤተ መቅደስ ንግደት የሚያደርጉ መሆኑንም አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው ከአገሪቱ ምዕመናን ጋር ሆነው የሚያሳልፏቸው ቀናት የውዳሴ እና የጸሎት ቀናት እንደሚሆኑ አስረድተዋል። ይህን መንፈሳዊ ጉዞ ላስተባበሩት በሙሉ ልባዊ ሰላምታቸውን አቅርበው፣ የእርሳቸውን መንፈሳዊ ጉብኝት በናፍቆት ለሚጠብቀው የስሎቫኪያ ሕዝብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አክለውም በጉዞአቸው ወቅት ምዕመናን በጸሎታቸው እንዲያግዟቸው ጠይቀዋል። ወደ ስሎቫኪያ በሚያደርጉት ንግደት፣ በመከራ እና በስደት ውስጥ ወንጌልን የመሰከሩ ብዙ የእምነት ጀግኖች አማላጅነት በጸሎት የሚጠይቁ መሆኑን ገልጸው፣ ዛሬም ቢሆን አውሮፓ በቃላት ሳይሆን ከሁሉም በላይ በተግባር ፣ በምሕረት እና በእንግዳ ተቀባይነት የአገልግሎት ሥራዎች ፣ የሚወደን እና የሚያድነን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሥራች ቃል መመስከር እንድትችል የሰማዕታቱን ዕርዳታ እንለምናለን ብለዋል።

ትናንት ነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. በሁሉም ዘንድ ማዘር ተሬዛ በመባል የምትታወቅ የካልኩታ ቅድስት ተሬዛ ዓመታዊ መታሰቢያ ክብረ በዓል መሆኑን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ፣ በዓለም ዙሪያ የቸርነት አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ለሚገኙት የቅድስት ተሬዛ የፍቅር ሥራ ሚሲዮናዊን በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው፣ ለድሆች መጠለያ እና የምግብ ዕርዳታን በማቅረብ የሚታወቁ፣ በቫቲካን ውስጥ ለሚገኙ “የማርያም ስጦታ” እህቶች በሙሉ ሰላምታቸውን እና ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በአርጄንቲና፣ ካንታማርካ ክፍለ ሀገር የኮርዶባ ሀገረ ሰብከት ጳጳስ የነበሩት ፍራንችስካዊ አቡን ማሜርቶ ኤስኩዊ የብጽዕና አዋጅ ይፋ መደረጉን ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ማሜርቶ በአካባቢው ወንጌልን በመስበክ፣ ቤተክርስቲያንን እና ሲቪል ማኅበረሰብን በማነጽ እና በማሳደግ ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከቱ መሆናቸውን አስረድተዋል። አክለውም የእርሱ ምሳሌነት በጸሎት እና በሐዋርያዊ አገልግሎት እንድንተባበር፣ ሰላምን እና ወንድማማችነትን ለማሳደግ ይርዳን ብለዋል።

ከጥቂት ቀናት በኋላ አዲሱን ዓመት የሚያከብሩ አይሁዳዊ ማኅበረሰቦችን ያስተወሱት ቅዱስነታቸው፣ የአይሁድ እምነትን ለሚከተሉ አይሁዳዊያን ወንድሞች እና እህቶች በሙሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል። የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለሚያከብሩት በሙሉ አዲሱ ዓመት ብዙ የሰላም ፍሬን የሚያገኙበት ዓመት እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል። 

ቅዱስነታቸው እንደተለመደው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት የተገኙ የሮም እና አካባቢዋ ምዕመናንን፣ የልዩ ልዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አባላትን፣ ከእነዚህ መካከል መቶኛ ዓመታቸው ለሚያከብሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅበርተኞች ሰላምታ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልካም መኞታቸውን ገልጸው የእመቤታችንን ጥበቃ ተመኝተውላቸዋል። በቅርቡ ምስጢረ ሜሮንን እና የመጀመሪያ ቁርባን ለተቀበሉ የተለያዩ ቁምስናዎች አዳጊ ልጆች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ከአውሮፓ አገራት፣ ከፖላንድ እና ከሊቷኒያ ለመጡት ምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸውዋል።

በመጨረሻም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና አገር ጎብኝዎች በሙሉ መልካም ዕለተ ሰንበትን ተመኝተው፣ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት የዕለቱን ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።  

06 September 2021, 15:50