የካርዲናሎች መማክርት በአውታረ መረብ ስብሰባ ላይ የካርዲናሎች መማክርት በአውታረ መረብ ስብሰባ ላይ 

የካርዲናሎች መማክርት በሚቀጥለው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ላይ ውይይት አካሄደ

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል የካርዲናሎች መማክርት ሰኞ መስከረም 10/2014 ዓ. ም. በአውታረ መረብ አማካይነት ባካሄደው ስብሰባ የሚቀጥለውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በሚመለከቱ ሲኖዶሳዊ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሄዱን ይፋ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰኞ ከሰዓት በኋላ በተካሄደው የካርዲናሎች መማክርት ስብሰባ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም መካፈላቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ ማክሰኞ ይፋ ባደረገው መግለጫ አስታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ኦስካር ሮድሪገስ ማራዲያጋ ካቀረቡት አጭር የመግቢያ ንግግር ቀጥለው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲኖዶሳዊነትን አስመልክተው ቀጣዩ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጀመሪያ ተግባር ላይ ሃሳባቸውን ያካፈሉ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት ያደረጓቸውን ሁለት ንግግሮች የሃሳባቸው ማዕከል ሆነው የእንዳገኟቸው፣ የመጀመሪያው እ. አ. አ በ2015 ዓ. ም. የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የተመሠረተበት 50ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ያደረጉትን ንግግር እና ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 8/2014 ዓ. ም ለሮም ሀገረ ስብከት ምእመናን ያደረጉትን ንግግር ማስታወሳቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ ገልጿል።

መግለጫው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሃሳብ ተመርኩዞ እንዳብራራው፣ የስብሰባው ዋናው ዓላማ  በአንዳንድ የተወሰኑ ጭብጦች ላይ የቤተክርስቲያን ሕይወት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለመሆኑን፣ በመደማመጥ እና በሐርያዊ አገልግሎት አመለካከት በሁሉም ደረጃዎች የሚታዩ ምልክቶችን፣ በተለይም ቤተክህነታዊ የበላይነት እና የግትርነት ፈተናዎችን መመልከት መሆኑን ገልጿል።

የካርዲናሎች መማክርትም ሲኖዶሳዊ መንገዶችን የሚመለከቱ አንዳንድ ሃሳቦችን ለውይይት ያቀረበ ሲሆን፣ በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሊታዩ የሚችሉ ወገናዊነት እና የወገናዊነት ፍላጎት ላይ መወያየቱን ገልጿል። የካርዲናሎች መማክርት የሚቀጥለውን ስብሰባ በታኅሳስ ወር 2014 ዓ. ም በአካል ተገናኝቶ ለመወያየት መስማማቱ ታውቋል።

ሰኞ መስከረም 10/2014 ዓ. ም. በአውታረ መረብ አማካይነት የተካሄደውን ስብሰባ የተካፈሉት ብጹዕ ካርዲናል ኦስካር ሮድሪገስ ማራዲያጋ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሬይናርድ ማርክስ፣ ብጹዕ ካርዲናል ሴን ፓትሪክ ኦማሊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ኦስቫልድ ግራሲያስ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ቤርቴሎ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ማርኮ ሜሊኖ መሆናቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል።  

23 September 2021, 17:06