ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለም የበለጠ እንዲተባበር አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሑድ መስከረም 16/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት፣ ዕለቱ 107ኛ ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መሆኑን በማስታወስ፣ ዓለም የበለጠ እንዲተባበር መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለ107ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ካቶሊካዊ ምዕመናን ከመኖሪያቸው ለተሰደዱት በሙሉ ልባቸውን እንዲከፍቱ አደራ ብለዋል። በዕለቱ ባቀረቡት ስብከትም ጭፍን ጥላቻንና ፍርሃትን አስወግደው በመቀራረብ በኅብረት እንዲጓዙ፣ በማኅበረሰቡ መካከል ተጋላጭ ወደሆኑት፣ ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ ተፈናቃዮች፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች እና ብቻቸውን ወደቀሩት በመቅረብ ዕርዳታቸውን እንዲያቀርቡላቸው ጠይቀው፣ እያንዳንዱ ሰው ማንንም ወደ ጎን ያማያደርግ ሁሉ አቀፍ ማኅበራዊ ሕይወት ለመኖር መጠራቱን አስረድተዋል። 

ስደተኞችን ማቋቋሚያ ዕቅዶች

በጣሊያን የዕርዳታ ድርጅት አማካይነት በርካታ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ የስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀንን ማስታወሳቸው ታውቋል። መስከረም 16/2014 ዓ. ም በተከበረው በዓል ላይ ተካፋይ የሆኑት በርካታ ሰዎች፣ በቅድስት መንበር የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መምሪያ ክፍል ምክትል ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ እና ከክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ ጋር በመሆን በቫቲካን ወደሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የእግር ጉዞ አድርገዋል።

ለስደተኞች ትኩረትን መስጠት

ብጹዕ አቡነ ሮበርት ቪቲሎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ዕለቱን በማስመልከት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። እርሳቸው በጠቅላይ ጸሐፊነት በሚመሩት ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የስደተኞች ምክር ቤት ስም ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፣ ቤተክርስቲያን እና የሰው ልጅ በሙሉ ከብቸኝነት ይልቅ የአንድነት ጎዳናን መጓዝ እንዳለባቸው ማሳሰባቸው ይታወሳል። በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተለይም በካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድም መከበሩ አስፈላጊ እንደሆነ ብጹዕ አቡነ ሮበርት ቪቲሎ ገልጸው፣ ክርስቲያን እንደመሆናችን ስደተኛን በክብር ተቀብሎ የማስተናገድ ሃላፊነት አለብን ብለዋል። 

ድንበሮችን ከመዝጋት ይልቅ ጥያቄአቸውን መመለስ

“በርካታ ማኅበረሰብ የሌላ አገር  ዜጎችን ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተመልክተናል” ያሉት ብጹዕ አቡነ ሮበርት፣ በዓለም ዙሪያ በርካታ አገሮች ድንበሮቻቸውን በመዝጋት ለአደጋ የተጋለጡ ሰዎች የሚያቀርቡትን የሕይወት አድን ዕርዳታ ጥያቄን ውድቅ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። የሰሜን አሜሪካ ድንበሮች ለስደተኞች ዝግ በመሆናቸው ምክንያት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፣ በቅርቡ በሜክሲኮ ስደተኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ትክክል አለመሆኑንም ተናግረዋል። “ሰሜን አሜሪካ፣ በድህነት ምክንያት አገራቸውን ለቅቀው የተሰደዱ ጣሊያናዊ ወላጆቻቸውን ተቀብሎ ያስተናገደ አገር ነው” ያሉት አቡነ ሮበርት፣ ወላጆቻቸውን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ስደተኞች ለአገሪቱ ዕድገት ከፍተኛ ተሰጥኦዎችን ማበርከታቸውን አስረድተዋል።

ስደተኞችን በመርዳት ካቶሊኮች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ

ብጹዕ አቡነ ሮበርት አክለውም፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ድርጅቶች እና ሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ድርጅቶች በስደት ላይ የሚገኝ የዓለም ሕዝብ በመርዳት በቀዳሚነት መጠቀሳቸውን አስታውሰው፣ ካቶሊካዊ ድርጅታቸው ከግለሰቦች እና ከሌሎች መንግሥታትዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት  የሚያገኘው የሰብዓዊ ዕርዳታ መጠን መመናመኑ ችግር መፍጠሩን ገልጸዋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መርጃ ድርጅቶችን ማገዝ፣ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ያጡትን ሰብዓዊ ክብር መልሰው እንዲያገኙ ያግዛቸዋል ብለዋል።   

27 September 2021, 17:01