ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን የአንድነት እና የመረዳዳት ባሕሎችዋን እንድታሳድግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መስከረም 16/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አቅርበዋል። ለዕለቱ በተመደበው በማር. ምዕ. 9: 38-41 ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን የአንድነት እና የመረዳዳት ባሕሎችዋን የበለጠ እንድታሳድግ አሳስበዋል።

ክቡራትና ክቡራን አድማጮቻችን፣ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን ያቀረቡትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን ተርጉመን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መካከል ከማር. ምዕ. 9: 38-41 የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እና ደቀ መዛሙርትን ወክሎ በቀረበው በሐዋርያው ዮሐንስ መካከል ስለ ተደረገው አጭር ውይይት ይናገራል። ደቀ መዛሙርቱ በጌታ ስም አጋንንትን የሚያስውጣ አንድ ሰው ባዩ ጊዜ ሥራውን እንዲያቆም አደረጉት። ይህን ያደረጉበት ምክንያትም ከእነርሱ መካከል አንዱ ባለመሆኑ ነበር። በዚህን ጊዜ ኢየሱስ፣ መልካም የሆነውን የሚያደርጉት ሁሉ የእግዚአብሔር ዕቅድ ይፈጸም ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ስለሚያበረክቱ እንዲተውት ጠየቃቸው (ማር. 9:38-41)። ከዚያም እንዲህ በማለት ይመክራቸው ጀመር፥ ‘ሰዎችን ጥሩ እና መጥፎ ብሎ ከመከፋፈል ይልቅ ወደ ልባችን  ተመልሰን በክፉ ነገር እንዳንሸነፍ ንቁ እንድንሆን እና በሌሎች ላይ መሸማቀቅን እንዳናመጣ ተጠርተናል’ አላቸው (ቁ. 42-45 ፣ 47-48)።

የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር በአጭሩ የሰውን ልጅ ሊደርስ የሚችለውን ፈተና በመግለጥ ምክርን የሚሰጥ ነበር። ፈተናውም ራስን ዝግ ማድረግ ነው። ደቀ መዛሙርቱ መልካም ተግባር እንዳይፈጸም ያልወደዱት ፈጻሚው ከእነርሱ ወገን ስላልነበረ ነበር። መልካም ተግባርን ለማከናወን መብት ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ እንደሆነ፣ ለእግዚአብሔር መንግሥት እንዲሰሩ የተፈቀደላቸውም እነርሱ ብቻ እንደሆኑ ያስቡ ነበር። ይህን በማድረግ ልዩ መብት እንዳላቸው በመቁጠር፣ ሌሎች በእነርሱ ላይ ጠላት እስከመሆን ድረስ ይመለከቷቸው ነበር። ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እያንዳንዱ የልብ መዘጋት እንደ እኛ ከማያስቡ ሰዎች እንድንርቅ ያደርገናል። በታሪክ ውስጥም እንዳየነው ከብዙ ክፉ ዝንባሌዎች የሚመጣ መሆኑን እናውቃለን። ብዙውን ጊዜ አምባገነንነትን እና በተቃራኒ ሰዎች ላይ ብዙ ዓመጾችን ከሚያስከትል ፍፁማዊነት ባሕርይ የሚመነጭ መሆኑን እንረዳለን።

ነገር ግን ራስን ዝግ የማድረግ አዝማሚያ በቤተክርስቲያን ውስጥም ያለ እንደሆነ በንቃት መመልከት መልካም ነው። ምክንያቱም ሰዎችን ሊከፋፍል ዘወትር የሚጥር ሰይጣን አልተኛምና። ‘ሰይጣን’ የተባለበት ምክንያትም ለዚህ ነውና። ሰዎችን ለመከፋፈል እና ለማግለል፣ ሁል ጊዜ በሰዎች መካከል ጥርጣሬዎች እንዲኖሩ ያደርጋልና። እነዚያን ደቀ መዛሙርት እንደፈተናቸው ሁሉ ተንኮልን በመጠቀም በሰዎች መካከል መለያየት እንዲኖር ያደርጋል። እኛም ብንሆን አንዳንድ ጊዜ ትሁት እና ለሌሎች ክፍት ከመሆን ይልቅ በበላይነት ስሜት ውስጥ በመግባት ሌሎችን በርቀት ልናስቀምጣቸው እንችላለን፤ በኅብረት ለመራመድ ከመሞከር ይልቅ ‘እኔ አማኝ ነኝ! እኔ ካቶሊክ ነኝ! እኔ የዚህ ወይም የዚያ ማኅበር አባል ነኝ!’ የሚል ስሜት ልናሳይ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ በራሱ ኃጢአት ነው። አማኝ መሆናችንን በማሳየት፣ በሌሎች ላይ ለመፍረድ እና ሌሎችን እስከ ማግለል እንደርሳለን። በሌሎች ላይ የመፍረድ እና ሌሎችን የመለያየት ፈተናን ማሸነፍ እንድንችል ጸጋውን መለመን ያስፈልጋል። እራሳቸውን መልካም አድርገው ከሚቆጥሩ ሰዎች ወገን እንዳንሆን እግዚአብሔር ይጠብቀን። ካኅን ከምዕመናኑ ጋር ልብ ለልብ የማይገናኝ ከሆነ፣ በሐዋርያዊ አገልጋዮች መካከል ግልጽነት የሚጎድል ከሆነ፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት የቆሙለትን ዓላማ እርስ በእርስ የማይጋሩ ከሆነ፣ እነዚህ አዝማሚያዎች የክርስቲያን ማኅበረሰቦችን ለልዩነት እንጂ ለአነድነት የሚጋብዙ አይደሉም። መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው ቦታ እንዲኖረው፣ በሰዎች መካከል ግልጽነት እንዲኖር፣ በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት ፍቅር እርስ በእርስ መቀባበል እንዲኖር እንጂ የተደበቀ ሕይወት እንዲኖር አይፈልግም።

በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመክረን፥ በሌሎች ላይ ከመፍረድ እንጠንቀቅ! ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ በክፉ ሥራችን ወደ ታች ዝቅ ብለን እንዳንታይ ያሳስበናል። ‘አንድ ነገር በውስጣችሁ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንባችሁ ቆርጣችህ ጣሉት!’ ይለናል (ማር. 9 : 43-48)። የሚጎዳችሁ ነገር ካለ ቆርጣችሁ ጣሉት! ለጉዳት አሳልፎ የሚሰጣችሁ ከሆነ ቶሎ ቆርጣችሁ ጣሉት አለ እንጂ ትንሽ የሚሻል ከሆነ ተመልከቱት ወይም አስቡበት አላለም። ኢየሱስ በዚህ አቋሙ እንደ ጥሩ ዶክተር ለራሳችን ጥቅም ሲል ነው። ከእያንዳንዱ ስህተት ታርመን በተሻለ ሁኔታ በማደግ በፍቅር ፍሬን ማፍራት እንድንችል ነው።

እንግዲያውስ፣ ‘በእኔ ውስጥ ወንጌልን እንድቃረን የሚያደርግ ነገር ምንድነው? ብለን እራስን እንጠይቅ። ከሕይወቴ አውልቄ እንድጥለው ኢየሱስ የሚፈልገው ነገር ምንድነው?’ ብለን እንጠይቅ። ሌሎችን በደስታ መቀበል እንድንችል እና ራሳችንን መመልከት የምንችልበትን ኃይል በመስጠት እንድታግዘን እመቤታችን ንጽሕት ድንግል ማርያምን በጸሎት እንጠይቃት።”  

27 September 2021, 16:36