ከፋውንዴሽኑ አባላት መካከል አንዷ ከፋውንዴሽኑ አባላት መካከል አንዷ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ መረዳዳት ነጻነትን እና ሰብዓዊ ክብርን የሚያጎናጽፍ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ወድቀው ለሚገኙ እናቶች እና ሕጻናት የመጠለያ እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚያቀርብ ካቶሊካዊ ፋውንዴሽን አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። “Archè” በመባል የሚታወቀው ፋውንዴሽኑ አሳዳጊ እና ረዳት የሌላቸውን ሕጻናት፣ ለአመጽ እና ለጥቃት የተጋለጡ አቅመ ደካማ እናቶችን ተቀብሎ የተለያዩ ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ሲያቀርብ መቆየቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ“Archè” ፋውንዴሽን ምሥረታ 30ኛ ዓመት ታስቦ በዋለበት፣ ነሐሴ 27/2013 ዓ. ም. የማዕከሉ አባላት ላበረከቱት አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ፋውንዴሽኑን በጣሊያን ሚላኖ ከተማ እ. አ. አ በ1991 ዓ. ም. የመሠረቱት ክቡር አባ ጁሰፔን በቶኒ፣ በወቅቱ የኤች አይ ቪ ኤይድስ ሕመም በሕጻናት እና በእናቶች ጤና ላይ ላስከተለው ችግር መፍተሄ ለማግኘት መሆኑን ቅዱስነታቸው በማስታወስ፣ የፋውንዴሽኙ መሥራች ለሆኑት ለክቡር አባ ጁሰፔ እና ረዳቶቻቸው በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

“Archè” የሚለው የፋውንዴሽኑ መጠሪያ ስም የመጣንበት መሠረት እንደሚገልጽ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ እንደምናውቀው በመጀመሪያ ፍቅር እንደነበር፣ እርሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረድተዋል። ሕይወት፣ መልካም የሆነው ሁሉ እና እውነት ፍቅር ከሆነው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚመጣ አስረድተው፣ ሕጻን ከእናት ማሕጸን እንደሚወለድ፣ ፍቅር ሥጋን በመልበስ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጸው ከእናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማሕጸን መሆኑን አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቫቲካን ለተቀበሏቸው የፋውንዴሽኑ አባላት ባደረጉት ንግግር፣ ድርጅታቸው ሲመሠረት አሳዳጊ እና ረዳት የሌላቸውን ሕጻናት፣ ለአመጽ እና ለጥቃት የተጋለጡ አቅመ ደካማ እናቶችን እና በሕመም የሚሰቃዩትን ተቀብሎ ዕርዳታዎችን ሲያቀርብ እንደነበር ገልጸው፣ የመጠለያ አገልግሎትን ካገኙት መካከል አብዛኛዎቹ ስደተኞች እንደነበሩ አስታውሰዋል።           

የተስፋ ምልክት

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የ“Archè” ፋውንዴሽን ማኅበረሰብ የተስፋ ምልክት ሆኖ መገኘቱን ተናግረው፣ ከሁሉም በላይ የተስፋ ምልክትነቱ በማዕከሉ ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች እና ሕጻናት ነው ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ አገልግሎቱን ለሚጋራቸው፣ ለበጎ ፈቃደኞች፣ ለወጣቶች እና ከማዕከሉ ተረጂዎች ጋር ሕይወትን ለሚካፈሉ ወጣት ባለትዳሮች የተስፋ ምልክት መሆኑን አስረድተዋል። በማዕከሉ ውስጥ የሚቀርብ የአገልግሎት ልምድ ከባድ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም በሌላ ወገን ደስታን እንደሚሰጥ አስረድተው፣ ይህ ደስታ በመተጋገዝ የሚገኝ፣ የነጻነት እና የሰብዓዊ ክብር ጎዳናን ለመራመድ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በንግግራቸው መጨረሻ ለማዕከሉ አባላት ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፣ የሚቀጥለውን ዓመት መታሰቢያ በሮም ከተማ በሚቋቋመው አዲስ ማዕከል ውስጥ የሚያከብሩ መሆኑን አብሥረውላቸዋል። “ይህ ማዕከል እግዚአብሔርን በመምሰል ለድሆች ቅርበት እና ርህራሄ የሚገለጽበት፣ ሁል ጊዜ ለሰዎች አገልግሎት የቆመ ማዕከል ሊሆን ይጋባል” ብለዋል።   

02 September 2021, 16:11