ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በአፍጋኒስታን ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሄው የጋራ ውይይት መሆኑን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያለፈው እሑድ ነሐሴ 9/2013 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአፍጋኒስታን ውስጥ ለተፈጠረው ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግር በውይይት መፍትሄ እንዲገኝለት አሳስበው፣ በአፍጋኒስታን የተፈጠረው አለመረጋጋት እና አመጽ ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ በካቡል ከሚገኝ ካቶሊክ ማኅበረሰብ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የምስጋና መልዕክት መድረሳቸው ታውቋል። በካቡል ከተማ በሚገኙ ካቶሊክ ማኅበረሰብ ስም መልዕክታቸውን ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የላኩት ክቡር አባ ጆቫኒ ስካሌሰ፣ “በአፍጋኒስታን የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጸሎታችንን መቀጠል አለብን” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የአፍጋኒስታን ሕዝብን በጸሎታቸው እንደሚደግፉት ገልጸው፣ እግዚአብሔር ሰላሙን እንዲያወርድ፣ የተለያዩ ወገኖች በጋራ በሚያደርጉት ውይይት ሰላም እንዲገኝ ምዕመናን በጸሎታቸው እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል። አክለውም በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ሴቶች እና ወንዶች፣ ሕጻናት እና አዛውንት ሰላምን አግኝቶ ወደ መኖሪያቸው መመለስ የሚችሉት የበጋራ ውይይቱ በሚያመጣው ስምምነት መሆኑን አስረድተዋል።

የካቡል ምዕመናን የምስጋና መልዕክት

በካቡል ከተማ በሚገኙ ካቶሊክዊ ምዕመናን ስም ለር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የምስጋና መልዕክት የላኩት ክቡር አባ ጆቫኒ ስካሌሰ፣ ካቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በአገሪቱ የሚገኙ የክርስቲያን ማኅበረሰብ የጦርነት ሕመም እንዳያጠቃቸው በጸሎት እንዲተባበሩ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ. አ. አ በ2002 ዓ. ም በአፍጋኒስታን ውስጥ ያቋቋሙት ገለልተኛ የወንጌል ተልዕኮ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ጆቫኒ ስካሌሰ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን አመስግነው፣ ባሁኑ ጊዜ አፍጋኒስታን ሰላም የሚያሻት መሆኑን ገልጸው፣ የመንግሥት ተቃዋሚው ታሊባን ተዋጊ ቡድን ያለ ምንም አመጽ የካቡል ከተማን መቆጣጠሩ የመላው ዓለም የጸሎት ውጤት ነው በማለት ገልጸዋል። የሽግግር መንግሥት እየተመሠረተ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ጆቫኒ፣ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እዲፈቱ ጸሎታችንን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

ወደ ዋና ከተማው የሚደረግ ጉዞ እና በአውሮፕላን ጣቢያ ያለው ትርምስ

የታሊባን ተዋጊዎች በመጨረሻው የውጊያ ሰዓት ፕሬዚደንታዊ ቤተመንግሥት ለመቆጣጠር ወደ ዋና ከተማዋ ካቡል መቃረባቸ ታውቋል። የአገሪቱ ፕሬዚደንት አቶ ጋኒ አካባቢውን ለቅቀው መሰወራቸው ወይም መሸሻቸው ታውቋል። የአሜሪካንን ጨምሮ በካቡል ከተማ የሚገኙ የልዩ ልዩ አገሮች ዲፕሎማቶች ከተማይቱን ለቀው እየወጡ መሆናቸው ተመልክቷል። የታሊባን ተዋጊዎች የአገሪቱን ድንበሮች በፍጥነት መቆጣጠራቸው እና በርካታ የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞችንም በእጃቸው ስር ማስገባታቸው ሲነገር፣ የካቡል ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያ ብቸኛው ከአገር መውጫ በር መሆኑ ታውቋል። የአፍጋኒስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ራሺድ አህመድ፣ የመንግሥት የመጨረሻ ይዞታ የነበረው የቶርክሃም ማቋረጫ በታሊባን ተዋጊዎች እጅ መውደቁን አረጋግጠዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር - ሽግግሩ ሰላማዊ ይሆናል

የካቡል ከተማ ምንም ዓይነት ጥቃት ሳይደርስባት ሽግግሩ በሰላም እንደሚከናወን የአፍጋኒስታን ጊዜያዊ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱል ሳታር ሚርዛኩላ በቪዲዮ መልዕክታቸው አስታውቀዋል። ለካቡል ከተማ ነዋሪዎች ባሰሙት መልዕክት፣ የጸጥታ አስከባሪዎች የከተማዋን ደህንነት እንደሚጠብቁ አረጋግጠውላቸዋል። በካቡል ከተማ የሚገኙ 600 የእንግሊዝ ወታደሮቿ ዜጎቻቸውን ከከታማው ለማውጣት ከአፍጋኒስታን ኃይሎች ጋር መተባበራቸው ታውቋል። በካቡል በሚገኝ የሩሲያ ኤምባሲ የሚገኙ ሠራተኞች ከተማዋን የሚለቁበት ቀን ያላታወቀ ሲሆን ዲፕሎማቶቿ መደበኛ ሥራቸውን መቀጠላቸው ታውቋል።   

የታሊባን ኃይል - ዓመፅን አንጠቀምም

አገሪቱ እጅግ በተረበሸችበት ባሁኑ ወቅት የታሊባን ተዋጊዎች በካቡል አውሮፕላን ጣቢያ አካባቢ የሚገኘውን ታዋቂ እስር ቤት በቁጥጥራቸው ማስገባታቸው ሲነገር ታራሚዎችንም ደህንነቱ አስተማማኝ ወደ ሆነበት አካባቢ ማዛወራቸው ታውቋል። ከዋና ከተማዋ በስተምዕራብ በኩል የሚገኝ የካቡል ዩኒቨርሲቲ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የሚገኝ መሆኑ ታውቋል።

ባይደን - ይህንን የወረስኩትን ጦርነት ለተተኪዬ አልሰጥም

አመሪካ በካቡል ከተማ በሚገኝ ኤምባሲዋ ውስጥ የሚሠሩ ዜጎቿን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ቁጥራቸው ከሦስት እስከ አምስት ሺህ የሚደርሱ ወታደሮቿን መላኳ ታውቋል። የአሜሪካ መንግሥት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒ ብሊንከን ከአፍጋኒስታን እስላማዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ፕሬዚደንት ከሆኑት ከአሽራፍ ጋኒ ጋር ትናንት መወያየታቸው ታውቋል። ሁለት ወገኖች በውይይታቸው ወቅት በአገሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉ አመጾችን በጋራ ለመከላከል መስማማታቸውን የጠቅላይ ጸሐፊው አንቶኒ ብሊንከን ቃል አቀባይ ገልጸዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ይህን ጦርነት ከሌሎች የወረሱት መሆኑን ገልጸው፣ “ለተተኪዬ አሳልፌ አልሰጥም” ብለዋል። 

የአውሮፓ ህብረት - ስደትን በተመለከተ አስቸኳይ የአውሮፓ ስምምነት ያስፈልጋል

የኔቶ አባል አገራት በአፍጋኒስታን ውስጥ የፖለቲካ መፍትሄ “ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስቸኳይ ነው” በማለት አስታውቋል። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ማርጋሪቲስ ሺናስ ለስደተኞች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበው፣ በአፍጋኒስታን ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር አውሮፓ ከእንግዲህ መጠበቅ እንደማትችል ገልጸዋል። አክለውም በአፍጋኒስታን ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ ለመቀነስ ጊዜው አሁን እንደሆነ እና በአዲሱ የአውሮፓ የስደተኞች ደንብ ላይ መስማማት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።       

17 August 2021, 16:20