ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት እምነት የሚገለጽበት መንገድ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጣሊያን ውስጥ ክሬሞና ከተማ ከነሐሴ 17-20/2013 ዓ. ም. ድረስ፣ 71ኛ ብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ሳምንት ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ለሚገኙት አባላት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በጣሊያን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ማዕከል ፕሬዚደንት ለሆኑት ለብጹዕ አቡነ ክላውዲዮ ማኒያጎ በላኩት መልዕክት፣ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት እምነት የሚገለጽበት ዋና መንገድ በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበው፣ ያለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በቁምስናዎች ዘንድ ምዕመናን የሚካፈሉበት የመስዋዕት ቅዳሴ ጸሎት እና ሌሎች የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች ተቋርጠው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጣሊያን ውስጥ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተስፋፍቶ በታየበት ያለፈው ዓመት ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዳይወጡ መደረጉን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ክስተቱ አሳዛኝ እንደነበር አስታውሰው፣ በጣሊያን ውስጥ ክሬሞና ከተማ ስብሰባቸውን በማካሄድ ላይ የሚገኙት የምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ተወካዮች፣ ሳምንታዊ የእሑድ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓትን፣ የምስጢራት አገልግሎትን እና የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች በሙላት የሚቀርቡበትን መንገድ በማጤን ለምዕመናኑ አዳዲስ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን እንዲያመቻቹ አሳስበዋል። ይህን በማድረግ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት በምዕመናን መንፈሳዊነት የሚሰጠው ከፍተኛ ሥፍራ ተጠብቆ እንደሚቆይ ያላቸውን ተስፋ ፣ በጣሊያን ውስጥ ክሬሞና ከተማ ከነሐሴ 17-20/2013 ዓ. ም. ድረስ፣ 71ኛ ብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ሳምንት ጉባኤን በማካሄድ ላይ ለሚገኙት አባላት በላኩት መልዕክት ገልጸዋል።

የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በኮቪድ-19 ምክንያት መደናቀፉ

በቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ በብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በኩል የተላከው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት ለጉባኤው ተካፋዮች በንባብ ቀርቧል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ያለፈው ዓመት ጣሊያን ውስጥ አስፈሪ እና አሳዛኝ ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል። ጉባኤው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ዘንድሮ ዓመት መሸጋገሩን ገልጸው፣ በማቴ. 18:20 “ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት ስፍራ እኔ በመካከላቸው እገኛለሁ” በሚለው መሪ ቃል፣ ዘንድሮ ለ71ኛ ጊዜ የሚካሄደው ጉባኤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እንቅፋት ያጋጠመውን የአምልኮ ሥርዓት በጥልቀት ተመልክቶ፣ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት መንገድ እንዲገኝ በማለት ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው አሳስበዋል።

በጣሊያን ውስጥ አስፈሪ እና አሳዛኝ ጊዜ እንደነበር ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሆኖም ግን ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ጀምሮ የተደረገውን ጉዞ መልካምነት ለመመልከት ዕድል የሰጠ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም “በወረርሽኙ ምክንያት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ዕለቱን እና ወቅቱን ጠብቆ አለመፈጸሙ፣ መለኮታዊው የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ለክርስትና ሕይወት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ለማወቅ አስችሎናል” ብለዋል።

የካህናት እና የምዕመና ሐዋርያዊ እረኝነት ተሳትፎ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ 71ኛ ብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ሳምንት ጉባኤ ተካፋዮች በላኩት መልዕክት፣ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ስም በየሳምንቱ ለጸሎት መሰብሰብ አስፈላጊነቱ ከመነሻው ጀምሮ ከክርስቲያናዊ ማንነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህ ማንነት ወረርሽኙ በተስፋፋበት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን ሐዋርያዊ አባቶች እና ምዕመናን ለእግዚአብሔር ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ በመሆኑ፣ የሐዋርያዊ እረኝነት ተሳትፎአቸውን በማሳደግ ወደ ተሟላ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመመለስ፣ ከእግዚአብሔር የሚገኘው የእምነት እና የፍቅር አንድነት በወንድሞች እና በእህቶች መካከል በማሳደግ ታማኝነታቸውን  እንዲገልጹ ያገዛቸው መሆኑን አስረድተዋል። የወረርሽኙ ወቅት ከባድ እና አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ምስጢር፣ ብዙ ሰዎች በወረርሽኙ ለተጎዱት ሰዎች ባበረከቱት የፍቅር እና የወንድማማችነት አገልግሎት ፍሬያማ ውጤት መገኘቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት “መታገድ” እና የዘመን ለውጥ

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ምዕመናን ከማኅበራዊ ግንኙነት ታግደው በዝግ እንዲቀመጡ በመገደዳቸው የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ተቋርጦ መቆየቱ፣ በጣሊያን ውስጥ ቀድሞውኑ የሚታየውን የእሑድ ዕለት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተሳትፎ መዳከም ማረጋገጡ ታውቋል። እውነታው በሰዎች ሕይወት ውስጥ የግንዛቤ ለውጥ፣ በዚህም ምክንያት በእሁድ ዕለት፣ በሚሰበሰቡበት ቦታ፣ በሕብረተሰብ፣ በሰዎች ስሜት እና በቤተሰብ ግንኙነት ላይ ችግር ማስከተሉ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ በየእሑዱ የሚካሄደው የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት የሚዳከመው በባሕል መመሳሰል እና በቁምስና ሕይወት ውስጥ ውህደትን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ሲዳከም፣ የመንፈሳዊ አገልግሎቶች የምሕረት ተልዕኮን ወደ ሁሉም አካባቢዎች ለማድረስ እንቅፋት በመፍጠሩ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ለሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚውሉ አዳዲስ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች

እነዚህ ችግሮች መኖራቸውን የተገነዘቡት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጣሊያን ውስጥ ክሬሞና ከተማ ከነሐሴ 17-20/2013 ዓ. ም. ድረስ፣ 71ኛ ብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ሳምንት ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ለሚገኙት አባላት በላኩት መልዕክት፣ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን በአካል እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል መሳተፍን በተመለከተ መከተል ስላለባቸው አንዳንድ መስመሮች አስተያየት መጠቆም ይችላል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው መደምደሚያ ላይ፣ በቅርቡ ይፋ ያደረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ማብራሪያ ሦስተኛው እትም፣ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት መልካም ፈቃደኝነት ታክሎበት የእግዚአብሔርን ሕዝብ በአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ማነጽ አስፈላጊ እንደሆነ ማሳወቅ መልካም ነው ብለዋል። በመጨረሻም በብሔራዊ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት ሳምንት ጉባኤ ላይ ለተገኙ ካህናት፣ ገዳማዊት እና ገዳማዊያን እንዲሁም ዲያቆናት በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ልከዋል። በጉባኤ የተገኙት በሙሉ በወረርሽኙ ብዙ ጉዳት ለደረሰበት ክልል መጽናኛ የሚሆን ሐዋርያዊ አገልግሎት እንደሚያበረክቱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቱ፣ እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ሥቃይ ለማስታገስ በደንብ እያበበ መሆኑን ገልጸዋል።

24 August 2021, 16:15