ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ፌቲቫል በፖላንድ በተከበረበት ጊዜ (እ. አ. አ 2016) ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ፌቲቫል በፖላንድ በተከበረበት ጊዜ (እ. አ. አ 2016) 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ከወጣቶች ጋር በመሆን የወንድማማችነት ዓለም እውን ማድረግ ይቻላል!”

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለተቸገረው እና ተጋላጭ ለሆነው የማኅበረሰባችን ክፍል ለሚደረግ ድጋፍ አዲሱ ትውልድ ሊያበረክት የሚችለው ዕርዳታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ከወጣቶች ጋር በመሆን የወንድማማችነት ዓለም ለመገንባት ያለንን ምኞት እና ሕልም እውን ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ነሐሴ 6/2013 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በማስታወስ ባስተላለፉት የቲውተር መልዕክት፣ ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ በቂ የዕለት ዳቦን፣ ውሃን፣ መድኃኒትን እና ሥራን ባለማግኘት የሚሰቃዩ በርካታ ሰዎችን በማስታወስ፣ እነዚህን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከችግራቸው ለማውጣት ወጣቶች በፈጠራ ችሎታቸው በመታገዝ እና የወንድማማችነት ዓለምን ለመገንባት ያላቸውን ሕልም እውን ሊያደረጉ እንደሚችሉ ገልጸዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ. አ. አ. 1999 ዓ. ም. ጸድቆ በየዓመቱ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ዋና ዓላማ፣ በማኅበራዊ እድገት ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አጉልቶ ለማሳየት መሆኑ ታውቋል። በዚህም መሠረት ዘንድሮ የተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን መሪ ቃል “የምግብ ሥርዓቶችን መለወጥ” የሚል ሲሆን፣ በወጣቶች የፈጠራ ችሎታ በመታገዝ የወጣቶችን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችን ደኅንነት ማረጋገጥ፣ የወንድማማችነት የጋር ዕድገትን ማምጣት የሚቻል መሆኑን በእንግሊዝ ውስጥ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ማዕከል አባል እና የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ኤኮኖሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ቫለንቲና ሮቶንዲ ገልጸዋል። ወ/ሮ ቫለንቲና ይህን የገለጹት በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች እ. አ. አ. ከኅዳር 19 – 21/2020 ዓ. ም ባካሄዱት ስብሰባ ላይ መሆኑ ታውቋል።

ወ/ሮ ቫሌንቲና አክለውም ወጣቶች የዕድገት እና የወንድማማነት ሕልሞችን እውን ለማድረግ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ምክንያቱም ሲገልጹ ወጣቶች ማኅበራዊ ችግሮችን በጋራ ለማቃለል ሕዝቦች እርስ በእርስ በተቀራረቡበት ዓለም ውስጥ ተወልደው ያደጉ በመሆናቸው ነው ብለዋል። የምንገኝበት ጊዜ በማኅበረሰብ ውስጥ የተግባር መርሃ ግብሮችን እውን ለማድረግ ወጣቶች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱበት ብቻ ሳይሆን ከጋራ መኖሪያ ምድራችን የምናገኘውን ጥቅም እየተጋራን ለምድራችንም አስፈላጊውን እንክብካቤ የምናደርግበት ጊዜ መሆኑን ወ/ሮ ቫለንቲና አስረድተዋል። በተጨማሪም ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁላችንም ወንድማማቾች መሆናችንን እንድንገነዘብ አድርጎናል ብለው፣ ወረርሽኙ ካስከተለው ማኅበራዊ ችግር ብቻውን ሊተርፍ የሚችል ሰው የለም ብለዋል።    

የ “ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ኤኮኖሚ” የሚል እንቅስቃሴ ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረ፣ ቀጣይነት ያለው እና በርካታ ወጣቶችን የሚያሳትፍ መሆኑን ወ/ሮ ቫለንቲና ገልጸው፣ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች እና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ሕይወታቸው በለውጥ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ይረዱታል ብለዋል። በ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የኤኮኖሚ አቅጣጫ መካከል የተለያዩ ሂደቶችን እና ታሪኮችን መመልከት እንደቻሉ የገለጹት ወ/ሮ ቫለንቲና፣ የዩክሬን ተወላጅ የሆነው የማኅበራቸው አባል ወጣት ያን የምህንድስና ሞያውን በማኅበራዊ መገናኛ መንገድ በመጠቀም በድህነት ሕይወት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች አገልግሎት ማዋሉን ገልጸዋል። ይህ የአገልግሎት መንገድ በሩቅ የሚገኙ የደቡብ አሜሪካ እና አፍሪካ ድሃ ማኅበረሰብን ለማገዝ ከተደረጉ ጥረቶች መካከል አንዱ መሆኑን  አስረድተዋል። ወጣት ያን የምህንድስና ዕውቀቱን ከቴሌኮሙኒኬሽን ዕውቀት ጋር በማዛመድ፣ ዩትዩብ በተባለ ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ለድሆች መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከሩን ወ/ሮ ቫለንቲና አስረድተዋል።

ወ/ሮ ቫለንቲና ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የምግብ ሥርዓቶቻችንን እና ልማዶችን በመቀየት ብቻ የለውጥ አራማጆች መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል። በተለይም ባደጉት አገራት ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ኤኮኖሚ ሥርዓት በመከተል የዚህ ለውጥ አራማጆች መሆን የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል። የአንዳንድ ሰብሎች የማምረቻ መገዶች ድህነትን ሊያሳድጉ እንደሚችሉ በመገንዘብ ዘዴውን ለመቀየር የተለያዩ የሙከራ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል። አፈርን ትክክኛ ዘዴን በመጠቀም ካላረሱ ድህነትን ሊያስከትል እንደሚችል የገለጹት ወ/ሮ ቫለንቲና፣ ከዚህ በተለየ መንገድ ለአንዳንድ ሰብሎች የሚደረግ ትክክለኛ የአስተራረስ ስልት መሬትን የበለጠ ትርፋማ በማድረግ በረጅም ጊዜ ሂደት የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጥ የሚችሉ መሆኑን አስረድተዋል።   

14 August 2021, 16:16