ምዕመናን ለአፍጋኒስታን ሰላም ጸሎት በማድረግ ላይ፤ ምዕመናን ለአፍጋኒስታን ሰላም ጸሎት በማድረግ ላይ፤ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ያቀረቡት የጸሎት እና የጾም ጥሪ፣ የጦርነት ተቃውሞ መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሁድ ነሐሴ 23/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም መላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ በጸሎት እና በጾም እንዲተባበር አደራ ማለታቸው ይታወሳል። ይህን ጥሪ ከተቀበሉት መካከል አንዱ የሆኑት፣ በሮም የሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር በሥራች የሆኑት ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ለሰላም የሚቀርብ ጸሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው፣ “በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ቡድኖች ሽብርን ይህን ያህል ማስፋፋት ከቻሉ፣ ትናንሽ የክርስቲያን ማኅበረሰብ እና ሰላም ወዳድ ክፍሎችም ሰላምን መፍጠር እና ማሳደግ ይችላሉ” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

ባሁኑ ወቅት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኘውን የአፍጋኒስታን ሕዝብ ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለመላው ክርስቲያን ማኅበረሰብ ባቀረቡት የጸሎት እና የጾም ጥሪ፣ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን በመከራ እና በጭንቅ ውስጥ የሚገኝ ሕዝብን መርዳት ያለብን ወቅት አሁን እንደሆነ ገልጸው፣ ክርስቲያኖች በያሉበት በጸሎት እና በጾም በመተባበር የእግዚአብሔርን ምሕረት እና ይቅርታ እንዲለምኑ አሳስበዋል።

ጸሎት እና ጾም ከመከራ ማሸነፊያ መንገዶች መካከል ናቸው

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ መስከረም 7/2013 በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በሺዎች ለሚቆጠሩ ክርስቲያን እና ክርስቲያን ላልሆኑ እንግዶች ባስተላለፉት መልዕክት፣ በወቅቱ የጦርነት አደጋ ላንዣበብበባት ሶርያ መጸለይ እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል። እንደዚሁም እ. አ. አ በ2017 ዓ. ም. ባስተላለፉት ጥሪ በአመጽ፣ በረሃብ፣ በስደት እና በብዝበዛ ውስጥ ለሚገኑት ደቡብ ሱዳን እና ኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፓብሊክ መጸለይ እና መጾም ያስፈልጋል ማለታቸውን አቶ አንድሬያ ሪካርዲ አስታውሰዋል። በወቅቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት እና የሌሎች እምነቶች ተከታዮች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመገኘት ድጋፉቸውን በሰልፍ መግለጻቸን ያስታወሱት አቶ አንድሬያ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሰልፉ ታዳሚዎች በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ይህን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በጋራ ጸሎታችንን እናቅርብ ማለታቸውን ገልጸዋል። ተመሳሳይ መንገዶችን በመጠቀም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በልዩ ልዩ የእምነት ተቋማት ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞች እና እህቶች ባቀረቡት መልዕክት በከፍተኛ ማኅበራዊ እና ፖለቲካው ችግሮች ውስጥ ለምትገኝ ሊባኖስ፣ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ዓለማችን በገባበት ወቅትም የዓለማች ሕዝብ በመተባበር ችግሮችን በጋራ ማሸነፍ እንዳለበት ጥሪ ማስተላለፋቸውን አስታውሰዋል።

በጦርነት ለሚገኙ አገራት በየቀኑ የመቁጠሪያ ጸሎት ማቅረብ አለብን

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር መሥራች የሆኑት ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ፣ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን የጸሎት እና የጾም ጥሪን በማስታወስ በሰጡት አስተያየት፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ለሰላም የሚቀርብ ጸሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኝ የአፍጋኒስታን ሕዝብ፣ 800 ሽህ ስደተኞች ለሚገኙባት ሞዛምቢክ እና ከፍተኛ የሕዝብ ስቃይ እንዳለባቸው ለማይታውቁ አገራት በሙሉ በየዕለቱ የመቁጠሪያ ጸሎት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ጸሎት የሚደርስባቸውን መከራ እና ስቃይ መቋቋም የማይችሉ በሙሉ እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ ኃይልን የሚያገኙበት መሣሪያ መሆኑን አስረድተዋል።

ሩቅ አገር ለሚካሄድ ጦርነት ምንም ዓይነት መፍትሄ ማግኘት እንደማንችል ይሰማን ይሆናል ያሉት አቶ አንድሬያ፣ ቀስ በቀስ ከዚህ ስሜት ውስጥ ግድ የለሽነት ስሜት እንደሚፈጠር ተናግረው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በደቡብ ጣሊያን፣ ላምፔዱስ ግዛት ስለ “ዓለም አቀፋዊ ግድ የለሽነት” መናገራቸውን አስታውሰዋል። በእርግጥ በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱ በርካታ አሳዛኝ ክስተቶችን በሙሉ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በምስል የምናያቸው ወይም በድምጽ የምንሰማቸው ቢሆንም ምንም ማድረግ እንደማንችል በግድ የለሽነት እናልፋቸዋለን ብለው፣ “ይልቁንስ በዚህ ዓለም ውስጥ እያንዳንዱ ወንድ እና ሴት አንድ ነገር ማድረግ እንደሚችሉ አምናለሁ” ብለዋል። አክለውም “በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ቡድኖች ሽብርን ይህን ያህል ማስፋፋት ከቻሉ፣ ትናንሽ የክርስቲያን ማኅበረሰብ እና ሰላም ወዳድ ክፍሎችም ሰላምን መፍጠር እና ማሳደግ ይችላሉ” ብለዋል።         

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በአፍጋኒስታን እና በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የሚካሄዱ አመጾችን እና ጦርነቶችን እንደሚከታተሉ የገለጹት አቶ አንድሬያ፣ ይህን ተገንዝበው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የሚገነባው ዓለማችን ማኅበራዊ አንድነት የሚታይበት እና ቀጥሎም ወደ ዓለም አቀፋዊ አንድነት የሚያድግ መሆን እንዳለበት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። “ሁላችንም ወንድማማቾ እና እህትማማቾች ነን” ነን በማለት ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የምናገኘው ዓለማችን በሰላም እና በፍቅር መንፈስ የተመሠረተ አንድነትን ለመገንባት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል። ለመገንባት የምንመኘው ማኅበረሰብ በግንብ እና በፍርሃት የታጠረ ሳይሆን፣ አንዱ ሌላውን በፍቅር እና በተስፋ ተቀብሎ የሚያስተናግድበት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል። ፍቅርን እና ተስፋን ማሳደግ የሚቻለው በጸሎት እንደሆነ ገልጸው፣ ጸሎት ድፍረትን አግኝተን አብሮ ለመኖር የሚያስችሉ መንገዶችን ለማሰብ እንደሚያግዝ፣ በሮም የሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር መሥራች የሆኑት ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል።

31 August 2021, 16:17