ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ኢየሱስን የሕይወት እንጀራ አድርገን ልንቀበለው ይገባል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሐምሌ 25/2013 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከዮሐንስ ወንጌል  6፣24-35 ላይ ተወስዶ በተነበበውና ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ መሆኑን በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን ኢየሱስን የሕይወት እንጀራ አድርገነው ልንቀበለው ይገባል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ስርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የወንጌሉ የመጀመሪያ ትዕይንት (ዮሐ 6 ፣ 24-35 ን ይመልከቱ) ወደ ቅፍርናሆም የሚሄዱ አንዳንድ ጀልባዎችን ​​ያሳየናል፣ በተጨማሪም ሕዝቡ ኢየሱስን እንደሚፈልግ ያሳየናል። ይህ በጣም ጥሩ የሆነ ነገር ነው ብለን ልናስብ እንችላለን ፣ ሆኖም ቅዱስ ወንጌል እግዚአብሔርን መፈለግ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ያስተምረናል። እሱን ለምን እንደምንፈልግ መጠየቅ አለብን። በእርግጥ ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም” (ዮሐንስ 6፡26) በማለት ይመልስላቸዋል። በእውነቱ ሰዎቹ ኢየሱስ እንጀራውን እና ዓሳውን በተዐምር እንዲበዛ ያደርገበትን ሁኔታ እና ተአምር ተመልክተዋል ፣ ነገር ግን የዚያን ምልክት ትርጉም አልተረዱም ነበር - በውጫዊው የተዓምሩ ገጽታ ላይ ብቻ ተቸንክረው ቀርተዋል፣ ቁሳዊ በሆነው እጅራ ላይ ብቻ ተመስጠው ቀሩ- እዚያ ብቻ ተቸንከረው ቆሙ ወደ ጥልቁ ትርጉም ለመሄድ አልፈለጉም።

እራሳችንን ልንጠይቅ የምንችለው የመጀመሪያ ጥያቄ እዚህ አለ - ለምን ጌታን እንፈልጋለን? ጌታን ለምን እንሻለን? እምነቴን ወይም እምነታችንን የሚያነሳሱ ነገሮች ምንድን ናቸው? በሕይወታችን ካጋጠሙን ብዙ ፈተናዎች መካከል ፣ ከብዙ ፈተናዎች መካከል ጣዖት የማምለክ ፈተና ብለን የምንጠራው አለና ይህን ማስተዋል አለብን። ለራሳችን ጥቅም ስንል ብቻ እግዚአብሔርን እንድንፈልግ እና ችግሮቻችንን እንዲፈታልን፣ እኛ በራሳችን ማግኘት የማንችለውን ነገሮች እንዲሰጠን፣ ፍላጎቶቻችን ከተሟሉ በኋላ ለእርሱ ምስጋና እንድናቀርብ የሚገፋፋን እርሱ ነው። ነገር ግን በዚህ መንገድ እምነት ጥልቅ ሳይሆን ይቀራል፣ ውጫዊ በሆነ መልኩ በተዐምራዊ ነገሮች ላይ ብቻ ተቸንክሮ ይቀራል፣ እግዚአብሔር እንዲመግበን እንጠብቃለን ፣ ከዚያም ስንጠግብ ስለ እርሱ እንረሳለን። በዚህ ያልበሰለ እምነት መሃል ያለው እግዚአብሔር ሳይሆን የራሳችን ፍላጎት ነው። ስለእኛ ፍላጎቶች ፣ ብዙ ነገሮችን አስባለሁ… ፍላጎቶቻችንን ለእግዚአብሔር ልብ ማቅረቡ ትክክል ነው ፣ ነገር ግን እኛ ከጠበቅነው በላይ የሚሠራው ጌታ ፣ በመጀመሪያ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ከእኛ ጋር ለመኖር ይፈልጋል። እናም እውነተኛ ፍቅር ቅድመ ሁኔታዎች የሉትም፣ ነፃ ነው - እርሱ የሚወደን በምላሹ እንድንወደው ጠብቆ አይደለም። ይህ የግል ጥቅም ነው፣ እናም በህይወት ውስጥ ብዙውን ጊዜ እኛ በግላዊ ፍላጎት እንገፋፋለን።

ሕዝቡ ኢየሱስን የጠየቀው ሁለተኛው ጥያቄ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” (ዮሐንስ 6፡28) የሚለው ነበር። በኢየሱስ የተበሳጩ የሚመስሉ ሰዎች ያቀረቡት ጥያቄ እስኪመስል ድረስ “እግዚአብሔርን የመፈለግ ሂደታችንን እንዴት እናነፃለን? የራሳችንን ፍላጎት ብቻ ከሚያስብ አስማታዊ እምነት እንዴት እግዚአብሔርን ወደ ሚያስደስት እምነት እንሄዳለን?” ለማለት የፈለጉ የሚመስሉ ጥያቄዎችን የሚያቀርቡ ይመስላል። ኢየሱስም መንገዱን ያሳየናል - የእግዚአብሔር ሥራ አብ የላከውን ማለትም ራሱን ኢየሱስን መቀበል ነው ብሎ ይመልሳል። ሃይማኖታዊ ልምዶችን መጨመር ወይም ልዩ ትዕዛዞችን ማክበር ማለት አይደለም። ኢየሱስን መቀበል፣ ኢየሱስን በሕይወታችን ውስጥ ማስገባት፣ ከኢየሱስ ጋር የፍቅር ታሪክ ውስጥ ገብቶ መኖር ማለት ነው። እምነታችንን የሚያነጻው እርሱ ነው። ይህንን በራሳችን ማድረግ አንችልም። ነገር ግን ጌታ ከእኛ ጋር የፍቅር ግንኙነት ይፈልጋል - እኛ ከምንቀበላቸው እና ከምናደርጋቸው ነገሮች በፊት እርሱ ሊወደን ተዘጋጅቶ ይጠብቀናል። ከፍላጎት እና ከስሌት አመክንዮ በላይ የሆነ ከእርሱ ጋር ግንኙነት መመስረት ይገባናል።

ይህ እግዚአብሔርን ይመለከታል፣ በተጨማሪም የእኛን ሰብአዊ እና ማህበራዊ ግንኙነቶችንም ይመለከታል -በመጀመሪያ የፍላጎታችንን እርካታ ስንፈልግ ሰዎችን የመጠቀም እና ሁኔታዎችን ለራሳችን ዓላማ የመበዝበዝ አደጋ ተጋርጦብናል። ስለ አንድ ሰው ስንቱን ሰምተናል ለምሳሌም “ግን እሱ ሰዎችን ይጠቀማል ከዚያም ይረሳቸዋል”? የሚለውን ቃል ስንቴ ስምተናል? ለራስ ጥቅም ሰዎችን መጠቀም - ይህ መጥፎ የሆነ ነገር ነው። እናም ከሰዎች ይልቅ ጥቅሞችን የሚያስቀድም ሁሉ ለህብረተሰቡ ህይወትን የማያመነጭ ማህበረሰብ ይገነባሉ። የቅዱስ ወንጌሉ ግብዣ ይህ ነው - ለሚመግበን ቁሳዊ እንጀራ ብቻ ከማሰብ ይልቅ ኢየሱስን የሕይወት እንጀራ አድርገን እንቀበለው እና ከእርሱ ጋር ካለን ወዳጅነት በመነሳት እርስ በርሳችን መዋደድን እንማር። በነፃ እና ያለ ስሌት እንዋደድ። ፍቅር በነፃ እና ያለ ስሌት የተሰጠ ፣ ሰዎችን ተጠቅመን ለመጣል ሳይሆን፣ በነፃነት ፣ በልግስና ፣ በትልቅነት እንድናገለግል ይተሰጠን ነው።

ከልጅዋ ጋር ለመገናኘት እራሳችንን እንድንከፍት ጸጋን ትሰጠን ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር እጅግ ውብ የሆነውን የፍቅር ታሪክ ወደ ኖረቺው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንጸልይ።

01 August 2021, 10:07

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >