ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በማጉረምረም ጊዜን ማጥፋት የክርስቲያን ተግባር አለመሆኑን ገለጹ
ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎቻችን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነሐሴ 23/2013 ዓ. ም በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተነተን ያደረጉትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተው አቅርበነዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
"ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
በዛሬው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ የሙሴ ሕግ መምህራን እና ፈሪሳውያን በኢየሱስ ክርስቶስ መገረማቸውን ይገልጻል። የተገረሙበት ምክንያትም ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ የሽማግሌዎችን ወግ ባለመጠበቅ፣ እጃቸውን ሳይታጠቡ እንጀራ ሲበሉ በማየታቸው ነበር። “ይህ የአሠራር መንገድ ሐይማኖታዊ ልማድን ይቃረናል” ብለው በማሰባቸው ነበር።
እኛም ብንሆን፣ ኢየሱስ እና ደቀ መዛሙርቱ የሽማግሌውችን ባሕል ለምን አላከበሩትም? ለምንስ ተቃወሙት? ብለን መጠየቅ እንችላለን። ከሁሉም በላይ ምግብ ከመመገብ በፊት እጅ መታጠብ መልካም ልማድ እንጂ መጥፎ የሚባል ባሕል አይደለም። ኢየሱስ ይህን ልማድ ያላከበረው ወይም ያልተከተለው ለምንድነው? ለኢየሱስ እጅግ አስፈላጊው እምነትን ማስቀደም ነበር። በቅዱስ ወንጌልም እምነት መቅደም እንዳለበት ተደጋግሞ ተጽፎ እናገኘዋለን። የሙሴ ሕግ መምህራን እና እኛም ብንሆን፣ ልባችንን እና እምነታችንን ደብቀን ውጫዊ ሥርዓቶችን ብቻ ከመፈጸም መቆጠብ እንዳለብን ቅዱስ ወንጌል ይናገራል። ብዙ ጊዜ እኛም ልባችንን ሳይሆን ውጫዊ ማንነታችንን አሳምረን መገኘትን እንወዳለን። የልባቸው ቆሻሻ ማጽዳት ሳይችሉ ቀርተው በውጫዊ ማንነት መልካም መስሎ መታየት መንፈሳዊነትን ለአደጋ ያጋልጣል። እግዚአብሔርን ከልባችን ሳይሆን ከአንገት በላይ የማምለክ ፈተና ሁል ጊዜ አለ። ነገር ግን ኢየሱስ ይህን ለመሰለ አምልኮ ዋጋን አይሰጥም። እርሱ ልብን የሚነካ እምነት እንጂ ለመታየት የሚቀርብ አምልኮን አይፈልግም።
በእርግጥ ለፈሪሳዊያን እና ለሙሴ ሕግ መምህራን ትልቅ እውነት ሲናገር፥ ‘ሰውን የሚያረክሰው ከሰው የሚወጣ ነገር እንጂ ከውጭ ወደ ሰው የሚገባውስ አያረክሰውም’ (ማር. 7:15) ብሏልና። ‘ሰውን የሚያረክሱት ከሰው ልብ የሚወጡት ነገሮች ናቸው’ (ማር. 7:21) ክፉ ነገሮች የሚወጡት ከሰው ልብ ውስጥ ነውና። ኢየሱስ ለፈሪሳዊያን እና ለሙሴ ሕግ መምህራን እንዲህ ብሎ መናገሩ በባሕላቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥን የሚያስከትል ንግግር ነበር። ምክንያቱም በዘመኑ አስተሳሰብ የተወሰኑ ምግቦች ወይም ውጫዊ ግንኙነቶች እንደ ርኩስ ተደርገው ይታሰቡ ነበር። ኢየሱስ እምነታቸውን፣ ባሕላቸውን ወይም አመለካከታቸውን ለውጦ፣ ‘ከውጭ የሚመጣው ጉዳት የለውም፣ ይልቁንም ጉዳት የሚያስከትለው ከውስጥ የሚወጣው ነው’ ብሎ ነገራቸው።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ይህ እኛንም ይመለከተናል። ብዙን ጊዜ ከክፉ ነገር የሚመጣው ከውጭ እንደሆነ እናስባለ፣ ክፉ ነገር፣ መጥፎ አመል ካላቸው፣ ለእኛ መልካም አመለካከት ከሌላቸው ሰዎች ወይም ከማኅበረሰባችን እንደሚመጣ እናስባብለን። በዚህም የተነሳ ለሚከሰቱብን ነገሮች በሙሉ ስንት ጊዜ ሌሎችን እንወቅሳለን? ስንት ጊዜ ማኅበረሰባችንን እና ዓለማችንን እንወቅሳለን? ሁል ጊዜ ስህተቱ የሌሎች እንደሆነ እናስባለን። ስህተቱ የሌሎች ሰዎች፣ የመንግሥት ወይም በአጋጣሚ የተከሰተ አድርገን እናስባለን። ችግሮች ከውጫዊ አካል እንደሚመጡ በማሰብ ሌሎችን ስንወቅስ እንታያለን። ጥፋትን በሌሎች ላይ ስንጭን ጊዜያችንን እንጨርሳለን። ሌሎችን እየወቀስን ጊዜን መጨረስ ጊዜን ማጥፋት ነው የሚሆንብን። በዚህ ምክንያት ስንቆጣ እና ስናማርር እግዚአብሔር ከልባችን እናርቀዋለን። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደተጠቀሱት እና ሁል ጊዜ ሌሎችን እንደሚወቅሱ ፣ ክርክር እንደሚፈጥሩ እና ኢየሱስን እንደማይቀበሉ ፈሪሳውያን እና የሙሴ ሕግ መምህራን እንሆናለን። ማጉረምረም መርዝ ነው። ወደ ቁጣ ይመራናል። ለእግዚአብሔር በር እንዲዘጋ ወደሚያደርግ ቂም እና ሀዘን ስለሚመራ፣ የሚያጉረመርም ሰው እውነተኛ መንፈሳዊ ሊሆን አይችልም።
እንደ ሕጻናት ሁል ጊዜ ሌሎችን ከመውቀስ ነጻ እንዲያደርገን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቅ። በማጉረምረም ብቻ ጊዜያችንን እንዳናጠፋ እግዚአብሔር ጸጋውን እንዲሰጠን እንለምነው። በማጉረምረም ጊዜን ማጥፋት የክርስቲያን ሰው ተግባር አይደለም። ኢየሱስ ልባችንን እና መላውን ዓለም እንድንመለከት ይጋብዘናል። ውስጣችንን ብንመለከት እንደ ዋዛ ቆጥረን ንቀን ያለፍናቸውን ነገሮች እናገኛቸዋለን። እግዚአብሔር ልባችንን እንዲያነጻልን ከለመንነው ፣ ዓለምን ንጹህ ማድረግ የምንጀምረው ያኔ ነው። ምክንያቱም ክፋትን ለማሸነፍ የምንችለው ልባችንን ስናጸዳ ነው። ልባችን የምናጸዳው ራስን ማሸነፍ ስንጀምር ነው። የመጀመሪያዎቹ የቤተክርስቲያን አባቶች፣ መነኮሳት፣ ‘የቅድስና መንገድ የቱ ነው?’ ተብለው ሲጠየቁ፥ ‘የመጀመሪያው እርምጃ ራስን መውቀስ ነው’ ይሉ ነበር። ስለዚህ ራሳችንን እንውቀስ። ይህ እንዲህ አረገኝ! ያ ደግሞ ጨክኖብኝ እንዲህ አረገኝ ከማለት በቀር፣ ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን በቀን ውስጥ ወይም በሳምንት ውስጥ እራሳችንን የምንወቅሰው? ራስን መውቀስ መማር ጥበብ ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ ከራስ አልፎ ለሌሎችም ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል።
ልቧን በማጽዳት ታሪክን የቀየረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ሌሎችን ከመውቀስ፣ በሁሉ ነገር ማጉረምረምን ትተን፣ ልባችንን ማጽዳት እንድንችል ትርዳን በማለት እንለምናታለን።”