ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ትህትና ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚያደርሰን መንገድ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በላቲን የአምልኮ ሥርዓት የቀን አቆጣጠር መሠረት እሑድ ነሐሴ 9/2013 ዓ. ም የተከበረውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰታ ክብረ በዓልን ከካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር አክብረዋል። ከሉቃ. 1: 39 – 56 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ባቀርቡበት ወቅት፣ በዕለቱ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገት እንድናስታውስ ማገዙን አስረድተዋል። ማርያም በእግዚአብሔር ደስታን ያገኘችው፣ በሉቃ. 1: 47-48 ላይ እንደ ተገለጸው፣ ዝቅተኛ አገልጋይቱን እርሷን እግዚአብሔር ስለተመለከታት መሆኑን አስረድተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎቻችን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነሐሴ 9/2013 ዓ. ም በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተነተን ያደረጉትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተው አቅርበነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! እንኳን አደረሳችሁ!

በእመቤታችን ማርያም ፍልሰታ መታሰቢያ ዕለት ከሉቃ. 1: 39 – 56 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍል የማርያምን የምስጋና ጸሎት በድጋሚ እንዲታወስ አድርጓል። ይህ የምስጋና ጸሎት ማርያም የእግዚአብሔር እናት መሆኗን የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ማርያምን ዝቅተኛ አገልጋይ አድርጎ የተመለከታት በመሆኑ ነው (ሉቃ. 1: 47-48) ።    

የማርያም ትልቁ ምስጢር ትህትና ነው። እግዚአብሔር የማርያምን ትህትና በትኩረት ተመልክቷል። የሰው ዓይን ሁል ጊዜ ክቡር እና ታላቅ የሆነውን በመፈለግ ስጋዊ ገጽታውን ይመለከታል። እግዚአብሔር ግን መልካም ልብን እና በትህትና የተሞላ ስብዕናን እንጂ እንደ ሰው ውጫዊ መልክን አያይም (1ኛ ሳሙ. 16:7)። የልብ ትሕትና እግዚአብሔርን ያማልዳል። ዛሬ የእመቤታችን ማርያም እረገት የተመለከትን እንደሆነ፣ ትህትና ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚመራ መንገድ መሆኑን እንናገራለን። “ትህትና” የሚለው ቃል ‘humus’ ከሚለው የላቲን ቃል የተወሰደ ሲሆን ‘ምድር’ ማለት ነው። በከፍታ ሥፍራ ወዳለው ሰማይ መድረስ፣ በዝቅታ ካለው ምድር ጋር ምን ያገናኘዋል? ኢየሱስም ስለዚሁ ሲያስተምር፥ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል (ሉቃ. 14:11)።

እግዚአብሔር ስጦታዎቻችንን ተመልክቶ ከፍ አያደርገንም ፣ በሀብታችን ወይም በሥራችን ከፍ አያደርገንም። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚያከብረን በትሕትናችን ነው። እግዚአብሔር ትሕትናን ይወዳል። ትሁታንን እና አገልጋዮችን ከፍ ያደርጋቸዋል። በእርግጥ ማርያምም ራሷን የምታየው እንደ አገልጋይ እንጂ ከዚህ የተለየ “ማዕረግ” ለመቀበል አልፈለገች፥ ‘እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ’ (ሉቃ. 1:38)። ስለራሷ ማንነት ምንም አልተናገረችም፤ ለራሷ ብላ ምንም አልፈለገችም። የጌታ አገልጋይ መሆንን ብቻ ነው የፈለገችው።

ወደ ልባችን ተመልሰን ራሳችንን እንጠይቅ! ‘ትሁታን ነን? በሰዎች ዘንድ እውቅናን ለማትርፍ የምንፈልግ ሰዎች ነን? ክብርን እንሻለን? ወይስ ሌሎችን ስለ ማገልገል እናስባለን?’ እንደ ማርያም ሌሎችን ማድመጥ እንዳለብን እንገነዘባለን ወይስ እኛ የምንናገረው ብቻ ተደማጭነት እንዲኖረው፣ የሌሎችን ትኩረት መሳብ እንፈልጋለን? እንደ ማርያም ዝምታን መምረጥ ወይስ ሁል ጊዜ ማውራትን እንፈልጋለን? ከጥላቻ እና ከማይጠቅም ክርክር መራቅን ወይስ ሁልጊዜ ንግግር በልጦ መታየትን እፈልጋለሁ? እነዚህን ጥያቄዎች ወስደን ‘ትሁታን ነን ወይ?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።

ማርያም ራሷን ዝቅ በማድረጓ ሰማያዊ ሥፍራን ተቀዳጀች። ወደዚህ የከፍታ ሥፍራ መድረስ ያቻለችበት ዋናው ምስጢር የራሷን ዝቅተኛነት በማወቋ እና የሚጠቅማትን ነገር ለይታ በማወቋ ነው። ራሳቸውን ከምንም ሳይቆጥሩ በእግዚአብሔር ብቻ የሚተማመኑት በሙሉ ሁሉን ነገር ያገኛሉ። ራሳቸውን ከሁሉ ነገር ነጻ የሚያደርጉት እግዚአብሔርን በማግኘት ሙሉ ይሆናሉ። ማርያምም በጸጋ ልትሞላ የቻለችው ትሁት በመሆኗ ነው (ሉቃ. 1:28)። ለእኛም ቢሆን ትህትና የመንፈሳዊ ጉዞ መነሻ፣ የእምነታችንም መጀመሪያ ሊሆን ይገባል። በመንፈስ ድሃ መሆን እና እግዚአብሔርን መፈለግ መሠረታዊ ነገር ነው። በራሳቸው ብቻ የሚመኩ ሰዎች ለእግዚአብሔር ቦታ የላቸውም። ብዙን ጊዜ በራሳችን እንመካለን። ነገር ግን ትሁታን ጌታ ታላላቅ ነገሮችን እንዲያደርግላቸው ይፈቅዳሉ (ሉቃ. 1:49)።

ዳንቴ የተባለ ጣሊያናዊ፣ ‘ምድረ-ገነት’ በሚል የግጥም ሥራው በቁ. 33-2 ላይ ‘ማርያም ከማንኛውም ፍጡር በላይ ትሁት እና ከፍ ያለች’ በማለት ይገልጻታል። በታሪክ ውስጥ ማርያም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ትሁት እና ከፍ ብላ እንደተገኘች፣ በነፍስና በአካል ወደ ሰማያት መውጣት እንደቻለች፣ ሕይወቷን ሙሉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በትህትና የኖረች መሆኗን ማሰብ እጅግ ደስ ይላል። በጸጋ የተሞላችባቸው ቀናት ያን ያህል አስገራሚ አልነበሩም። አንዱ ቀን በሌላው ቀን ላይ እየተደጋገመ ብዙውን ጊዜ ተመሳሳይ ያላቸው ናቸው። ውጫዊ ገጽታውን ስንመለከተው ምንም አዲስ ነገር የለውም። ነገር ግን እግዚአብሔር ዓይኖቹን በማርያም ላይ በማድረግ፣ ትህትናዋን እና ለጥሪው ያላትን ዝግጁነት፣ ልቧ በኃጢአት አለመበላሸቱን ተመልክቶ ያደንቃት ነበር።

ይህ ለእያንዳንዳችን ከፍተኛ ተስፋን፣ አድካሚ እና አስቸጋሪ የሆኑ ቀናትን ለሚያሳልፉት በሙሉ ተስፋን የሚሰጥ መልዕክት ነው። ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ወደዚህ አስደናቂ ግብ ለመድረስ የምትጓዙትን ሁሉ እንደሚጠራ ማርያም ታስታውሳችኋለች። ይህ መልዕክት ባማሩ ቃላት የታጀበ፣ መጨረሻውም መልካም የሆነ የሐሰት ማጽናኛ መልዕክት ሳይሆን፣ በእውነት ላይ የተመሠረተ፣ እመቤታችን ወደ ሰማይ ማረጓን የሚናገር እውነተኛ መልዕክት ነው። በመሆኑንም የእመቤታችንን ክብረ በዓል በፍቅር እንደተሞሉ ልጆች በመሆን እናክብር። አንድ ቀን በገነት ውስጥ ከእርሷ ጋር የምንሆንበትን ተስፋ በመያዝ በደስታ የተሞላ ትህትናዋን እናክብር!

እመቤታችን ማርያም በጉዟችን ከእኛ ጋር ሆና፣ ከምድራዊ ሕይወት ወደ ሰማያዊው ቤታችን በምናደገው ጉዞ መሪያችን እንድትሆነን የእርሷን እርዳታ በጸሎት እንለምን። የዚህ ጉዞ ምስጢር ትህትና መሆኑን እንድታስታውሰን በጸሎት እንጠይቃት። እመቤታችን ማርያም የምታስታውሰን ‘ትህትና’ የሚለው ቃል፣ በሰዎች መካከል ራስን ዝቅ ማድረግ እና አገልጋይነት የጉዞአችን ውጤት የሚገለጥበት ምስጢር መሆኑን መዘንጋት የለብንም"።

16 August 2021, 15:45