Vatican News
በአፍጋኒስታን የሚካሄደውን አመጽ እና ጦርነት በአፍጋኒስታን የሚካሄደውን አመጽ እና ጦርነት   (Public Domain)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የአፍጋኒስታንን ሕዝብ በጸሎት እና በጾም ማስታወስ እንደሚገባ አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሁድ ነሐሴ 23/2013 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው፣ በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም ክርስቲያኖች በሙሉ በጸሎት እና በጾም እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል። ባለፉት ቀናት ውስጥ በተፈጸሙ የጦር መሣሪያ ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን እናቶች እና ሕጻናት አስታውሰው፣ ለተጎጂዎች የሚላከው ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ተማጽነዋል። በተፋላሚዎች መካከል የሚደረግ ውይይትም፣ አንድነትን፣ ሰላምን እና የወንድማማችነትን ሕይወት እንዲያስገኝ ክርስቲያኖች በጸሎት እና በጾም እንዲተባበሩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአፍጋኒስታን የሚካሄደውን አመጽ እና ጦርነት በቅርብ የሚከታተሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ነሐሴ 20/2013 ዓ. ም. በካቡል አውሮፕላን ጣቢያ በተፈጸመው የጦር መሣሪያ ጥቃት ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ የንጹሐን ዜጎች ሕይወት መጥፋት እጅግ ያሳዘናቸው መሆኑ ገልጸዋል። በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡት በሙሉ የሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ምሕረት ለምነው፣ የሕይወት ዋስትናን ፈልገው ዕርዳትን ለሚጠይቁት በሙሉ የእግዚአብሔርን ጥበቃ ተመኝተው፣ በአፍጋኒስታን ውስጥ በተነሳው አመጽ እና ጦርነት ምክንያት መከራ ውስጥ ለሚገኙት ዕርዳታን በማቅረብ ላይ ለሚገኙት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለጦርነቱ ተጎጂዎች የሚላክ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ተማጽነው፣ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የሚገኘው የአፍጋኒስታን ሕዝብ መዘንጋት የለበትም ብለዋል። ክርስቲያን እንደመሆናችን፣ ይህን በመሰለ መከራ ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ መርዳት እንደሚያስፈልግ የቤተክርስቲያን ታሪክ ያስተምረናል ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ክርስቲያኖች በያሉበት በጸሎት እና በጾም በመተባበር የእግዚአብሔርን ምሕረት እና ይቅርታ እንዲለምኑ አደራ ብለዋል። 

አፍጋኒስታን በከፍተኛ የጥቃት አደጋ ውስጥ ትገኛለች

የአሜሪካን ወታደሮች አፍጋኒስታንን ለቅቀው ለመውጣት በሚጣደፉበት በአሁኑ ጊዜ አፍጋኒስታን በከፍተኛ የጥቃት አደጋ ውስጥ መገኘቷ ታውቋል። የአሸባሪዎች ጥቃት ሊደርስበት እንደሚችል የሰጋው፣ በካቡል የሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ዜጎቹ ከካቡል አውሮፕላን ጣቢያ እንዲርቁ አሳስቦ፣ ከ24 እስከ 36 ሰዓት ባለው ጊዜ መካካል በማንኛውም ሰዓት ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል የአሜሪካው ፕሬዚደንት ክቡር ጆ ባይደን ማሳሰባቸው ታውቋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም የጦር ኃይላቸው በአፍጋኒስታን ውስጥ በሚፋለመው የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች ላይ ባካሄደው ጥቃት ሁለት ታጣቂዎችን መግደሉን አስታውቀዋል።

የጣሊያን እና የብሪታንያ አውሮፕላን መስመር ተዘግቷል

በአፍጋኒስታን ሕዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት በመፈጸም ላይ የሚገኙት የታሊባን ታጣቂዎች፣ የአሜሪካ መንግሥት ወታደሮች የካቡል አውሮፕላን ጣቢያን ለቅቀው ሲወጡ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር መዘጋጀታቸው ታውቋል። የታሊባን ታጣቂዎች አፍጋኒስታንን ለቅቀው ለመውጣት የሚፈልጉ አፍጋኒስታዊያንን ለጊዜው ማገዳቸው ታውቋል። የጣሊያን እና የብሪታኒያ ወታደሮች ይገለገሉባቸው የነበሩ የአውሮፕላን በረራ መስመሮች ከሃያ ዓመታት በኋላ መዘጋታቸው ታውቋል። በሚቀጥለው ሳምንት፣ ወደ ፊት አፍጋኒስታን የሚመራ መንግሥት የቱ እንደሆነ የታሊባን ታጣቂዎች ይፋ እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ባግላንን ጨምሮ በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ በሚገኝ ፓንሺር ግዛት ውስጥ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ታውቋል።

የሕፃናት ማስጠንቀቂያ፥ 300 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለው ያለ ዕርዳታ ቀርተዋል

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” በአፍጋኒስታን ውስጥ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ 300 ሺህ ሕጻናት መኖራቸውን አስታውቆ፣ እነዚህ ሕጻናት ያለ ዕርዳታ መቅረት እንደሌለባቸው አሳስቧል። የታሊባን ታጣቂዎች የተለያዩ አካባቢዎችን መቆጣጠር ከጀመሩበት ዕለት አንስቶ በርካታ ሕጻናት መኖሪያ አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲፈናቀሉ መገደዳቸውን “ዩኒሴፍ” አስታውቆ፣ በአፍጋኒስታን ውስጥ ዕድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች የሚሆናቸው አንድ ሚሊዮን ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት እንደሚሰቃዩ እና ለሕይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል። የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ አክሎም ከአራት ሚሊዮን አዳጊ ሕጻናት መካከል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሴቶች መሆናቸውን አስታውቆ፣ ባሁኑ ጊዜ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ መገደዳቸውን አስረድቷል። በአፍጋኒስታን ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ አስተባባሪ ድርጅት በመግለጫው እ. አ. አ 2021 ዓ. ም. በአገሪቱ ንጹሐን ዘጎች ላይ ከፍተኛ ችግር የደረሰበት ዓመት መሆኑን አስታውቆ፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ቁጥራቸው ከምን ጊዘም በላይ መጨመሩን አስረድቷል።

30 August 2021, 16:49

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >