ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ካርዲናል ሞሴንጉዎን በጸሎታቸው አስታወሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ 2013 ዓ. ም ለመጀመሪያ ጊዜ በመሠረቱት እና ስምንት አባላት ባሉበት የካርዲናሎች መማክርት ውስጥ ብጹዕ ካርዲናል ሞሴንጉዎን አንዱ አድርገው መምረጣቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ሞሰንጉዎ በዚህ የአገልግሎት ደረጃ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በካርዲናሎች መማክርት ውስጥ ሃላፊነታቸውን በታማኝነት ያበረከቱ እና ለቤተክርስቲያን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖን ያበረከቱ እንደነበሩ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው አስታውሰዋል።
በኮንጎ የዕርቅ ውይይት ጉልህ ሚና ነበራቸው
የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ሞሴንጉዎ ፓሲኛ በዴሞክራሲያዊት ኮንጎ በተደረገው የሰላም እና ዕርቅ ውይይት ጉልህ ሚና የነበራቸው፣ የምዕመናንን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ሲያደረጉ የነበሩ፣ ከክህነት ሕይወት ጀምረው እምነትን ከአገሩ ሕዝብ ባሕል ጋር በማዛመድ ውጤታማ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲያበረክቱ የኖሩ እና የድሃውን ማኅበረሰብ ሕይወት ለመቀየር የተለያዩ አማራጮችን ሲያቀርቡ የነበሩ መሆናቸው ቅዱስነታቸው በሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሞሴንጉዎ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ሰላምን እና ፍትህን ለማምጣት በተደረጉት ውይይቶች ከፍተኛ አስተዋጽዖን ሲያበረክቱ የቆዩ፣ በአገሪቱ ውስጥ ሁለገብ ማኅበራዊ ዕድገትን ለማምጣት በትጋት የሰሩ፣ በቤተክርስቲያን ሕይወት ከፍተኛ ክብር የነበራቸው፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካው ዓለምም በአገራቸው ዕርቅን ለማምጣት በተደረጉ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ከፍተኛ አስተዋጽዖን ያበረከቱ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።
መንፈሳዊ እና ሊቅ ሐዋርያዊ አባት ነበሩ
ቅዱስነታቸው ለብጹዕ ካርዲናል ሞሰንጉዎ ቤተሰብ፣ ለኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ ለኢኖንጎ፣ ለኪሳንጋኒ እና ለኪንሻሳ ምዕመናን በሙሉ መጽናናትን ተመኝተው፣ የአገልግሎት ሥፍራን ሳይመርጡ ቤተክርስቲያንን በጥበብ እና በታማኝነት ሲያገለግሉ የነበሩ ሐዋርያዊ አባት የካርዲናል ሞሰንጉዎን ነፍስ እግዚአብሔር በመንግሥቱ ተቀብሎ ምህረቱን እንዲሰጥ በብርሃኑም እንዲያኖራት በጸሎታቸው ጠይቀዋል።