ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙ ሕሙማን ጠይቀዋል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙ ሕሙማን ጠይቀዋል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የቀዶ ጥገና ሕክምና ዕርዳታ ጊዜያቸውን ፈጽመው በማገገም ላይ መሆናቸው ተገለጸ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከውጤታማ የቀዶ ጥገና ሕክምና በኋላ በእነዚህ ቀናት ውስጥ የሕክምና ቴራፒን በመውሰድ ላይ መሆናቸው ታውቋል። የሕክምና ቴራፒ ጊዜን እስከሚፈጽሙ ድረስ በሆስፒታሉ የሚቆዩ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በሆስፒታሉ በሚያደርጉት የማገገሚያ ጊዜ በላቲን አሜሪካ አህጉር የአርጄንቲና እግር ኳስ ቡድን በተቀዳጀው የአሸናፊነት ውጤት እና በአውሮፓ አህጉርም የጣሊያን እግር ኳስ ቡድን በተቀዳጀው የአሸናፊነት ውጤት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፉት ቀናት ውስጥ መልካም ውጤቶች የታዩባቸውን የሕክምና ዕርዳታን ሲከታተሉ የቆዩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከተደረገላቸው የቀዶ ጥገና ሕክምና በኋላ አሁን የሕክምና ቴራፒን በመከታተል ላይ መሆናቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀዋል። አክለውም የጀመሩት የሕክምና ቴራፒ በመልካም እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቅዱስነታቸው ከሕመማቸው እያገገሙ እና ዕረፍት እያገኙ  በሆስፒታል የሚቆዩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።       

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ሐምሌ 4/2013 ዓ. ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ የእኩለ ቀን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ በሆስፒታሉ የሕክምና ዕርዳታን በመከታተል ላይ የሚገኙ አንዳንድ ሕሙማን እየዞሩ መጠየቃቸውን አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በሚገኙበት አሥረኛው ፎቅ ላይ ከሚገኙ ሕሙማን ጋር ሆነው በተዘጋጀላቸው መናፈሻ ዕረፍት ማድረጋቸውን እና ከሆስፒታሉ ሐኪሞች ጋር መተዋወቃቸውን የመግለጫ ክፍሉ ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በየዕለቱ የሚያቀርቡትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በተዘጋጀላቸው ጸሎት ቤት  ውስጥ ከተወሰኑ የሆስፒታሉ አባላት ጋር በየዕለቱ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አቶ ማቴዎ ብሩኒ ገልጸዋል።        

ቅዱስነታቸው በላቲን አሜሪካ አህጉር የአርጄንቲና እግር ኳስ ቡድን የአሸናፊነት ውጤት እና በአውሮፓ አህጉርም እንዲሁ የጣሊያን እግር ኳስ ቡድን የአሸናፊነት ውጤት በማስታወስ፣ የስፖርትን እሴት እና በስፖርት ጨዋታዎች ጊዜ የሚገኝ የአሸናፊነት ይሁን የሽንፈት ውጤት በጸጋ መቀበል እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተስፋን ሳይቆርጡ በእምነት እና በተስፋ ለማሸነፍ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ከዚህ በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሁን የሚገኙበት የጤና ሁኔታ እጅግ መልካም እንደሆነ፣ በመደበኛው የምግብ ሰዓት የሚቀርብላቸውን ቀላል ምግቦችን መውሰድ መጀመራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። ዕለታዊ የሕክምና ዕርዳታዎችም መልካም ውጤቶች እያሳዩ እንደሆነ፣ በተጨማሪ በማረፊያ ክፍላቸው አካባቢ መንቀሳቀስ መጀመራቸውን፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን እያነበቡ ያለ ሕመም መልካም የዕረፍት ጊዜን በማሳለፍ ላይ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። በተዘጋጀላቸው የግል ጸሎት ቤት ተገኝተው በየዕለቱ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን የሚያቀርቡ መሆኑን ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

13 July 2021, 14:52