ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ “ካለን ከጥቂቱም፣ ምንም ከሌላቸው ሰዎች ጋር መካፈልን አንዘንጋ”!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ ሐምሌ 18/2013 ዓ. ም በላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር መሠረት ከዮሐ. 6፡1-15 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማቅረባቸው በፊት ባቀረቡት አስተምህሮአቸው፣ ካለን ነገር ለሌሎች ስናካፈል ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ደስ እንደሚሰኝ አስረድተው “ያለን ነገር ጥቂት ቢሆንም ምንም ከሌላቸው ሰዎች ጋር መካፈልን መዘንጋት የለብንም!” ብለዋል።

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎቻችን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሐምሌ 18/2013 ዓ. ም በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተነተን ያደረጉትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተው አቅርበነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የእሑድ ዕለት መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት ከዮሐ. 6:1-15 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ሊሰሙት የመጡ አምስት ሺህ ያህል ሰዎችን በጥቂት ዳቦ እና ዓሣዎች ብቻ መመገብ  መቻሉን ይተርክልናል። ይህን ተዓምር ስንሰማ እጅግ እንገረማለን። ኢየሱስ ይህን ተዓምር የሰራው ዳቦን እና ዓሣን እራሱ አዘጋጅቶ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ ያመጡለትን በመውሰድ ነው። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ፣ አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣዎችን የያዘ አንድ ልጅ መኖሩን ይረዳል። ነገር ግን አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ሰዎችን በበቂ ሁኔታ ሊመግብ አይችልም። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በዚህ ጥቂት ምግብ በሥፍራው የነበሩትን በሙሉ በበቂው ሁኔታ መመገብ እንደሚችል ያውቅ ነበር።

አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣዎች ይዞ በተገኘው ልጅ ቦታ ራሳችንን እናስቀምጥ። ደቀ መዛሙርቱ ይህ ልጅ የያዛቸውን አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ በሥፍራው ከነበሩ አምስት ሺህ ሰዎች ጋር እንዲካፈል በማለት ጠየቁት። ጥያቄያቸው አግባብነት ያለው ሊመስለን ይችላል። ነገር ግን ለራሱ ብሎ ያመጣውን ትንሽ ስንቅ ከሌሎች ጋር እንዲካፈል መጠየቅ ለምን አስፈለገ? ልጁ የያዘው ምግብ በሥፍራው ለነበሩ በርካታ ሰዎች እንደማይበቃ እየታወቀ ከእጁ መውሰድ ለምን አስፈለገ? በሰብዓዊ አስተሳሰብ ብንወስደው ይህ ተግባር ተገቢ አይደለም። እንደ እግዚአብሔር ፍላጎት ግን ትክክል ነው። ማንም ሳያስገድደው በግል ፍላጎቱ በእጁ የያዘውን ስንቅ በስጦታ መልክ ላቀረበው ልጅ ምስጋና ይግባውና ኢየሱስም በዚህ ስጦታ አማካይነት በሥፍራው የነበሩ በርካታ ሰዎችን አንድ በአንድ ሊመግብ ችሏል። ይህ ለእኛ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ያለንን ጥቂት ነገር ይዘን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ስንቀርብ እርሱ ብዙ ሊያደርግልን እንደሚችል ያረጋግጥልናል። በመሆኑም ‘ወደ ኢየሱስ ዘንድ ምን ይዤ ልቅረብ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎት የምንጠይቀውን ነገር እጅግ ርብዝቶ ሊሰጠን ይችላል። ለሌሎች የምናበረክተውን የቸርነት ሥራ፣ በችግር እና በመከራ ወቅት የእርሱን ምሕረት ስንለምን መልስ ሊሆነን ይችላል። ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይዘን በምንቀርበው ትንሽ ነገር እርሱ ተዓምራትን ሊያደርግ ይችላል። በነጻ ፍላጎት ተነሳስተን በምናቀርብለት ትናንሽ ነገሮች በኩል እግዚአብሔር ተዓምራትን ማድረግ ይፈልጋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች፣ ከአብርሐም እና ከቅድስት ድንግል ማርያም ጀምሮ እስከ ቸሩ ልጅ ድረስ የተጠቀሱት ታሪኮች የበታችነትን እና የልግስናን ምስጢር ጉልህ ያደርጉልናል። ይህ ልግስና እኛ ከምናውቀው እና ከለመድነው ልግስና ፍጹም የተለየ ነው። እኛ ባለን ነገር ላይ የበለጠ መጨመርን እንፈልጋለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ካለን ቀንሰን ለሌላቸው እንድንሰጥ ይጠይቀናል። ያገኘው ነገር ጥቂት ቢሆን እንኳ በማባዛት ለሌላቸው መስጠትን ይፈልጋል። እኛም ያለንን ነገር ከሌላቸው ሰዎች ጋር ስንካፈል ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ደስ ይለዋል። በዮሐ. 6:11 ፣ በማቴ. 14:19 ፣ በማር. 6:41 ፣ በሉቃ. 9:16 ኢየሱስ ክርስቶስ አምስት ሺህ ሰዎችን በጥቂት ዳቦ እና ዓሣ እንደመገበ በሚገልጽ ታሪክ ውስጥ ‘ማባዛት’ የሚል ቃል አለተጻፈም። ነገር ግን ‘መቁረስ’ ፣ ‘መስጠት’ እና ‘ማደል’ የሚሉ ቃላት ተጸፍው እናገኛቸዋለን። የእግዚአብሔር እውነተኛ ተዓምር ዳቦን እና ዓሣን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመካፈል የሚገኝ ደስታ እንጂ በማባዛት አለመሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ያለንን ከሌሎች ጋር ለመካፈል እንሞክር።

ዛሬም ቢሆን በማኅበረሰባችን መካከል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከሌለ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለው ቁሳዊ ምርት ችግሮችን ሊያስወግድ አይችልም። ይህን በምንልበት ጊዜ በተለይም የበርካታ ሕጻናት ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ረሃብ በቅድሚያ የሚጠቀስ ነው። በዓለማችን ውስጥ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ፣ ቁጥራቸው ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት በየቀኑ እንደሚሞቱ ይነገራል። ይህ ችግር ጎልቶ በሚታይበት ባሁኑ ወቅት ያለንን ነገር ከሌሎች ጋር መጋራት እንዳለብን ኢየሱስ ክርስቶስ ይጋብዘናል። ያለን ሃብት እና እውቀት ትንሽ ቢሆንም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በማቅረብ ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር መጋራት ይኖርብናል። ከሌሎች ጋር በመጋራት የምናጣው ነገር የለም። ይህን ካደረግን ባለን ላይ እግዚአብሔር አብዝቶ ይሰጠናል። ‘ያለን አይበቃም’ ብሎ ከማሰብ ይልቅ የፍቅርን፣ የቸርነትን እና ሌሎችን የማገልገል አስፈላጊነት መረዳት ያስፈልጋል።

የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ራሷን ዝግጁ አድርጋ የተገኘች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እኛም ለእግዚአብሔር ጥሪ ልባችንን ከፍተን ሌሎችን ማገልገል የምንችልበትን ጸጋ እንድናገኝ ትርዳን"።

25 July 2021, 13:55