ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የወንጌል ምስክርነት ባልጠበቅነው አዲስ መንገድ እንድንጓዝ ይጠይቀናል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ሰኔ 16/2013 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ለተሰበሰቡት ምእመናን ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬው አስተምህሮአቸው የወንጌል ምስክርነት ባላሰብነው እና ባልጠበቅነው አዲስ መንገድ እንድንጓዝ ይጠይቀናል ብለዋል። ክቡራን እና ክቡራት አድማጮቻችን ከዚህ በመቀጠል ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በቫቲካን ውስጥ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በጸሎት ላይ በማትኮር ረጅም ጊዜን ከወሰደው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ አዲስ አርዕስትን እንጀምራለን። በዚህ አዲስ አርዕስት ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ባቀረባቸው አንዳንድ ጭብጦች ላይ ማስተንተን እፈልጋለሁ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላቲያ ሰዎች የላከው መልዕክት እጅግ አስፈላጊ እና ልናውቀው የሚገባን ወሳኝ መልዕክት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ አንዳንድ እርሱ በጥልቀት የተመለከታቸው ርዕሠ ጉዳዮች የቅዱስ ወንጌልን ውበት የሚያሳዩ ናቸው። በዚህ መልዕክቱ ሐዋርያው ጳውሎስ በሕይወት ዘመኑ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልገል እንዲወስን እና የሕይወት ለውጥ እንዲያደርግ የገፋፉት በርካታ ታሪኮችን በመግለጽ እንድናውቃቸው አግዞናል። እምነትን የተመለከቱ ከእነዚህም መካከል ነጻነት፣ ጸጋ እና ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚሉ ርዕሠ ጉዳዮችንም ተመልክቶአቸዋል። እነዚህ ርዕሠ ጉዳዮች በዘመናችንም በርካታ የቤተክርስቲያን ሕይወትን የሚዳስሱ ናቸው።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በላከው መልዕክቱ በቅድሚያ የሚጠቀሰው ቢያንስ ሁለት ጊዜ  ባደረጋቸው ጉብኝቶች በኩል ያበረከተው ከፍተኛ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በመልዕክቱ ክርስቲያኖች ብሎ ይናገር እንጂ በትክክል በየትኛው አካባቢ የሚኖሩ እና መልዕክቱንም መቼ እንደጻፈው የምናውቀው ነገር የለም። የገላቲያ ሰዎች ጥንታዊ የኬልቲክ ህዝብ እንደነበሩ፣ ከብዙ ልፋት በኋላ አናቶሊያ በምትባል፣ ዛሬ ቱርክ ተብላ የምትጠራ አገር ዋና ከተማ አንካራ የተቆረቆረችበት አካባቢ መሆኑን እናውቃለን።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ አካባቢው ለመጀመሪያ ጊዜ የምሥራቹን ቃል ለመስበክ ዕድል ያገኘበት እና ታሞ የቆየበት አካባቢ መሆኑን ይናገራል (ገላ. 4:13)። ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ እንደሚያሳየው ሐዋርያው ወደ አካባቢው ያደረገውን ጉብኝት ይበልጥ ከመንፈሳዊ ተነሳሽነት ጋር ያዛምደዋል። በሐዋ. 16:6 ላይ እንደምናገኘው፣ ጳውሎስ እና ሲላስ በእስያ ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለከለከላቸው በፍርግያ እና በገላትያ አገር አድርገው አለፉ ይለናል።

እነዚህ ሁለት መረጃዎች እርስ በእርስ የሚጋጩ አይደሉም። የወንጌል ምስክርነት እቅድ የሚፈጸመው ሁል ጊዜ በእኛ ፍላጎት እና እቅዶች ላይ የሚመረኮዝ ሳይሆን ሌሎች ያልታሰቡ መንገዶችን ለመከተል እራሳችንን ማዘጋጀት እና ፈቃደኝነትን ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ በማይደክመው የወንጌል አገልግሎት ወቅት በገላቲያ የተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የሚኖሩ ትናንሽ ማኅበረሰቦችን ማግኘት እንደቻለ እንረዳለን።

ሌላው ማወቅ ያለብን ሐዋርያው ጳውሎስ በአገልግሎት ወቅቱ አንድ ያስተዋለው ነገር ቢኖር በገላትያ ውስጥ በመሠረታቸው ቤተክርስቶያኖች እምነት እንዳይጠነክር የሚያደርግ ከፍተኛ እንቅፋት መኖሩን ነው። ከክርስቲያኖቹ መካከል አንዳንዶቹ ከአይሁድ እምነት የመጡ ስለነበር፣ የሚዘሯቸው ጽንሰ-ሐሳቦች የሐዋርያውን ትምህርት የሚቃረኑ ብቻ ሳይሆን እርሱን እስከ ማንቋሸሽ ድረስ የሚሄዱ ነበር።

ከዚህ የምንረዳው ራስን ብቸኛ የእውነት ባለቤት አድርጎ ማቅረብ እና ስም ማጥፋት እንዲሁም የሌሎችን ሥራ አቅሎ መመልከት ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነበረ መሆኑን ነው። እነዚህ የጳውሎስ ተቃዋሚዎች አሕዛብ እንኳ ሳይቀሩ መገረዝ እና በሙሴ ሕግ መሠረት መኖር እንዳለባቸው ይከራከሩ ነበር። ይህ ደግሞ የገላትያ ሰዎች የራሳቸውን ማንነት እና ባሕል ትተው በአይሁድ ልማዶች እና ደንቦች እንዲተዳደሩ ይገደዳሉ ማለት ነው። በዚህ ብቻ አያበቃም። እነዚያ ተቃዋሚዎች ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ አለመሆኑን እና ወንጌልን የመስበክ ስልጣን እንደሌለው ይከራከሩ ነበር።

በዚህ ዓይነት ሁኔታ የገላትያ ሰዎች ከፍተኛ ችግር ያጋጠማቸው መሆኑን ይገነዘባሉ። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ነበረባቸው? የጳውሎስን ስብከት መስማት እና መከተል ወይስ የተቃዋሚዎችን አዲስ ስብከት ማድመጥ? በገላትያ ሰዎች ልብ ውስጥ የገባውን የጥርጣሬ መንፈስ መገመት ቀላል ነው። ለእነርሱ ፣ ኢየሱስን በማወቅ በሞቱ እና በትንሳኤው በተከናወነው የድነት ሥራ ማመን በእውነት የአዲስ ሕይወት ጅምር ነበር።

ምንም እንኳን ታሪካቸው ለሮማ ንጉሠ ነገሥት የተገዙ መሆናቸውን ቢገልጽም ቢያንስ ከብዙ የጭካኔ ተግባር እና ከባርነት ሕይወት ጋር የተሳሰረ ቢሆንም በመጨረሻ ነፃ እንዲወጡ የሚያስችላቸውን መንገድ ጀምረዋል። ስለሆነም ከአዲሶቹ ሰባኪዎች ትችት ጋር በመጋፈጡ ፣ ጠባያቸውን አሳምረው ማንን ማዳመጥ እንዳለባቸው እርግጠኛ ሆነዋል ማለት ነው። በአጭሩ ያጋጠማቸውን ችግር ለማለፍ ብዙ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ይህ ሁኔታ ዛሬ በርካታ ክርስቲያኖችን ከሚያጋጥም ልምድ የራቀ አይደለም። በእርግጥ በዘመናችንም በተለይም ዘመናዊ የመገናኛ መንገዶች በተመቻቹበት፣ እራሳቸውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቀዳሚ የወንጌል መስካሪዎች እና በተሻለ መንገድ ለክርስቲያኖች “እውነትን ጠብቀው የሚያቆዩ” እንደሆኑ አድረገው የሚያሳዩ  ሰዎች ብዙ ናቸው። እነዚህ ሰዎች እውነተኛው ክርስትና እነርሱ የተጣበቁበት ፣ ብዙውን ጊዜ ከቀደሙት አንዳንድ ቅርሶች ጋር የሚዛመድ መሆኑን በመግለጽ ለዛሬው የእምነት መዳከም መፍትሄው ወደ ኋላ መመለስ እንደሆነ አጥብቀው ያረጋግጣሉ።

ዛሬም ቢሆን ፣ ካለፉት ወጎች መካከል በተወሰኑት በመመራት እራስን የመዝጋት ፈተና አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች የላከው መልዕክት የትኛውን ጎዳና መከተል እንዳለብን ያስተምረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ያመለከተን ጎዳና ለእኛ ሲል ተሰቅሎ የሞተው እና ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ነጻ የሚያድረገን አዲስ ጎዳና ነው። በትህትና እና በወንድማማችነት ሕይወት የተገኘ የወንጌል አገልግሎት መንገድ ነው። መንፈስ ቅዱስ በዘመናት ሁሉ በቤተክርስቲያን ውስጥ እንደሚሠራ በእርግጠኝነት እና በየዋህነት የምንመሰክርበት የታዛዥነት መንገድ ነው።”

23 June 2021, 16:30