በሕንድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት በሕንድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እጅግ ለተጠቁት አገራት ዕርዳታን ለገሱ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በዘጠኝ አገራት በሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴዎች ጽሕፈት ቤቶች በኩል በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እጅግ ለተጎዱት ዘጠኝ አገራት የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በዕርዳታ መለገሳቸውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየስኪ አስታውቀዋል። እስካሁን በዓለማችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ 177 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ታውቋል። በወረርሽኙ እጅግ የተጎዱ አገራት ከላቲን አሜሪካ እስከ መላው ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካን አቋርጦ ሶርያን እና ፓፓ ኒዩ ጊኒን መድረሱ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወረርሽኙ በዓለማችን ከገባ ጊዜ ወዲህ በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ህክምና መስጫ መሣሪያ እጥረት ምክንያት ዜጎቻቸው በከፍተኛ ስቃይ ለሚገኙባቸው አገራት ዕርዳታን ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማደግ ላይ ባሉ ድሃ አገሮች ውስጥ በአዲስ መልክ በመስፋፋት ብዙዎችን በተለይም በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙትን ለሞት እየዳረጋቸው መሆኑን አሳስቦ፣ የክትባቱ ዘመቻ በሀብታም ሀገሮች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየስኪ፣ ሐሙስ ሰኔ 10/2013 ዓ. ም በጽሕፈት ቤታቸው በኩል በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተጎዱት አገራት የሚሆኑ 38 የንጹሕ አየር መተንፈሻ መሣሪያዎችን እና ተጨማሪ የሕክምና መገልገያዎችን መላካቸው ታውቋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እጅግ ከተጠቁት አገራት መካከል ብራዚል እና ሕንድ በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ሲሆን እስካሁን በሁለቱ አገራት ውስጥ በወረርሽኙ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 50 ሚሊዮን መድረሱ ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ለእነዚህ አገራት ለእያንዳንዳቸው ስድስት፣ ስድስት የንጹሕ አየር መተንፈሻ መሣሪያዎችን በሚያዝያ ወር ውስጥ የላከ ሲሆን፣ ለላቲን አሜሪካ አገራት ለአርጄንቲና እና ለኮሎምቢያ ለእያንዳንዳቸው አምስት፣ አምስት የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን መላኩ ታውቋል። ከዚም በተጨማሪ 4 ለቺሊ እና ደቡብ አፍሪካ፣ 3 ለቦሊቪያ እና ሶርያ፣ በመጨረሻም 2 የንጹሕ አየር መተንፈሻ መሣሪያዎች በፓፓ ኒዩ ጊኒ ለሚገኙት ሆስፒታሎች መላኩ ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እነዚህን የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች በአገራቱ ወደሚገኙ የሕክምና መስጫ ተቋማት እንዲደርስ ያደረገው በአገራቱ በሚገኙ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤቶች በኩል መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ አስታውቀው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የወረርሽኙ አዳዲስ ተግዳሮቶች

በዓለማችን ውስጥ ወረርሽኙን ለመቀንስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ቢገኝም እስካሁን ሊቆጣጠሩት ያልተቻለ መሆኑ ታውቋል። ወረርሽኙ ሕንድን በመሰሉ አገሮች በአዲስ መልክ እየተስፋፋ መምጣቱ ሲነገር፣ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በወርሽኙ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ ሲሆን ይህ ቁጥር ካለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ጀመሮ ከተመዘገቡት ቁጥሮች መካከል  ከፍተኛው መሆኑ ሲታወቅ፣ በእንግሊዝ ውስጥ በወረርሽኙ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ተመልክቷል። የወረርሽኙ መቋቋሚያ ክትባቶች ተሰርተው እየታደሉ ቢሆንም ሞትን መከላከል ያልተቻል መሆኑ ታውቋል።

በቅርቡ በሩሲያ፣ ሞስኮ ከተማ ውስጥ በወረርሽኙ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በቀን 453 መድረሱ ሲነገር፣ ይህ ቁጥር ከመጋቢት ወር ወዲህ ከተመዘገበው የሟች ቁጥር ከፍተኛው መሆኑ ታውቋል። በአውሮፓ ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በማስመልከት አገራት የሚያቀርቡት ሪፖርቶች እንዳለ ሆኖ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ቢሮ እንዳመለከተው፣ የወረርሽኙን መዛመት በተመለከተ ከፍተኛ መሻሻል መኖሩን ገልጾ፣ በጣሊያን ውስጥ ከደቡብ ክፍላተ አገራት በስተቀር በመካከለኛው እና ሰሜን ክፍላተ አገራት ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን አስታውቋል። በመካከለኛው እና ምሥራቅ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ወረርሽኙ የቀነሰ መሆኑን የወረርሽኙ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ቢሮ አስታውቆ፣ በሆላንድ፣ ስዊድን እና ስፔን ውስጥ ለውጥ አለመታየቱን አስረድቷል። የጣሊያን መንግሥት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ማርዮ ድራጊ፣ ከመጭው ሐምሌ ወር አንስቶ በጣሊያን ውስጥ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚያስችል ፈቃድ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

19 June 2021, 16:34