ፈልግ

በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙት ስደተኞች ልባችንን በመክፈት፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙት ስደተኞች ልባችንን በመክፈት፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሚያንማር ሕዝብ ዕርዳታን እና ለስደተኞች ልብን መክፈት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሚያንማር ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ድምጻቸውን በማስተባበር በረሃብ እና በመጠለያ እጦት ለሚሰቃይ የሚያንማር ሕዝብ እርዳታ እንዲደርስለት ጠይቀው፣ በተባበሩት መንግሥታት አስተባባሪነት ትናንት ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በማስታወስ ለስደተኞች ልብን መክፈት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከቅዱስ ወንጌል አስተንትኖአቸው ቀጥለው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናኑ ጋር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። ቀጥለውም በአደባብዩ ለተገኙት ምዕምናን ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ንግግር አድርገዋል። በዚህ ንግግራቸው የሚያንማር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ባለፈው ሳምንት በሐዘን በመሞላት ለመላው ዓለም ማኅበረሰብ ያስተላለፉትን መልዕክት አስታውሰው፣ ብጹዓን ጳጳሳቱ በመዕክታቸው በአገሪቱ ውስጥ በተቀሰቀሰው አመጽ ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈላቅለው በረሃብ በመሰቃየት እየሞቱ መሆኑን በማሳሰብ፣ ለሕዝባቸው ምግብ እና ሌሎች ዕርዳታዎች የሚገቡባቸው መስመሮች እንዲከፈቱ፣ ዕርዳታው በአብያተ ክርስቲያናት፣ በገዳማት፣ በመስጊዶች እና በቤተመቅደሶችም በኩል ማስገባት እንዲቻል መለመናቸውን አስታውሰው፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ በከፍተኛ መከራ ውስጥ የሚገኘውን የሚያንማር ሕዝብ በጸሎታቸው በማሰብ ከጎኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፣ “በጋራ ለውጥን ማምጣት እንችላለን” በሚል መሪ ቃል ትናንት ሰኔ 13/2013 ዓ. ም የተከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞችን ቀን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸውም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙት ስደተኞች ልባችንን በመክፈት፣ ሐዘናቸውን እና ደስታቸውን መጋራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። አክለውም ድፍረትን የመቋቋም ችሎታ ከእነሱ እንማር ብለው፣ በዚህ መንገድ ይበልጥ ሰብዓዊነትን የተላበሰ ትልቅ ቤተሰብ መፍጠር እንችላለን ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ንግግራችውን ከመፈጸማቸው በፊት ከሮም እና አካባቢዋ እንዲሁም ከጣሊያን ውስጥ ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች እና ከተሞች ለመጡት ምዕመናን እና እንግዶች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። የላቲን አሜሪካ አገር ሕዝቦች መካከል አንዱ የሆነው የፔሩ ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ መገኘቱን የተመለከቱ ቅዱስነታቸው ሰላምታቸውን እንደዚሁ አቅርበው በጣሊያን ውስጥ ከተለያዩ ከተሞች የመጡ ካቶሊካዊ አስጎብኚዎች እና ስካውት ማህበራት አባላት፣ በጣሊያን ትምህርት ቤቶች በማስተማር ሥራ ለተሰማሩ ሴት መምህራን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ጣሊያን ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ የማኅበራት ተወካዮችን እና አባላት ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት በሙሉ መልካም ሰንበትን ተመኝተው፣ ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል። 

21 June 2021, 16:38

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >